ሕዝብ፡ ማለት ምን ማለት ነው? አማርኛ ነው? ወይስ ግእዝ?
ሕዝብ፡ ማለት
ምን ማለት ነው? አማርኛ ነው? ወይስ ግእዝ?
Watch video
Watch video
ሰላም ጤና ይስጥልኝ ከአውደ ጥናት ዘግእዝ ነው
ዛሬ “ሕዝብ” በሚለው የግእዝ ቃል ላይ ያተኮረ አጭር
ትንታኔን ይዠላችሁ ቀርቤያለሁ ተከታተሉ። አስተያየት፤ ተጨማሪ፤ ወይም ጥያቄ ካላችሁ Learngeez@outlook.com
በሚለው የአውደ ጥናት ዘግእዝ ኢሜይል መላክ ትችላላችሁ። የግእዝና እና የአማርኛ ቋንቋን በተመለከተ ከአውደ ጥናት የሚተላለፉትን
የትምህርት ዓይነቶች መከታተል ከፈለጋችሁ ሰብስክራይብ
ልሣነ ግእዝ የሚለውን መጽሐፍ
ለመግዛት ይህንን ይጫኑ ማድረግንም አትርሱ።
ይህንን አጭር ማብራርያ የጻፍኩበት ምክንያት ባለፈው እንደ ዓለም አቀፉ አቆጣጠር ግንቦት 9 ቀን
2019 ዓ/ም “ዕለታዊ” በተሰኘው በኢሳት ESAT Satellite TV ፕሮግራም በተላለፈው ዝግጅት የዝግጅት አቅራቢዎቹ “ሕዝብ” በሚለው ቃል ላይ ከተለመደው ትንታኒያቸው ለየትና ረዘም ያለጊዜን ወስደው
ያደረጉትን ውይይት መነሻ በማድረግ እኔም በበኩሌ በመጻሕፍት እና በሊቃውንቱ በጽሁፍ ላይ ሰፍሮ የሚገኘውን መረጃ ለነሱም እንደ
ተጨማሪ ይሆናቸው ዘንድ ለማካፈል በማሰብ ነው።
በዚህ አጋጣሚ በበኩሌ በተጠቀሰው ቃል ላይ የሰጡት ትንታኔ በቋንቋው ይዘት ላይ ጠለቅ ያለ ችሎታ
እንዳላቸው የሚያሳይ እንደሆነ ተረድቻለሁ፤ አድናቆቴንም ሳልገልጥ አላልፍም። ግሩም ነው።
“ሕዝብ” የሚለው ቃሉ የግእዝ ቃል ሲሆን በአማርኛም እንዳለ በቁሙ “ሕዝብ” እየተባለ ይጠራል። ምክንያቱም
በጣም ብዙ የግእዝ ቋንቋ ቃላት በአማርኛም እንዳሉ ሳይለወጡ አገልግሎት ይሰጣሉ። ለምሳሌ እንደ ፍቅር፤ ሕግ፤ ፍትሕ፤ ሰላም፤ ሐገር፤ ብሔር፤ ቤተ መንግሥት፤
ቤተ ክህነት፤ ሕገ መንግሥት፤ ፍትሐ ብሔር ወዘ ተርፈ የመሳሰሉት ሁሉ የግእዝ ቃላትና ኃረጎች ናቸው። ሆኖም ግን ለ2ቱም ቋንቋዎች
ያገለግላሉ፤ የግእዝን ቋንቋ የሚያውቁ ያውቋቸዋል የማያውቁ ደግሞ ፍፁም አማርኛ እንደሆኑ ይቆጥሯቸዋል።
“ሕዝብ” የሚለው ቃልም እንዲሁ በአማርኛም ተለምዶ ይልቁንም እንደ አማርኛ ተቆጥሮ ግእዝ መሆኑ ራሱ
በአብዛኛው የቋንቋው ተጠቃሚ የሚታወቅ አይመስልም። በግእዝ ቋንቋነቱ ስንጠቀምበት በአማርኛ ከምንጠቀመው አጠቃቀም ብዙ ባይርቅም
ለየት ያለ ባሕርይ አለው ልዩነቱ በመጠኑ እንመለከታለን።
·
የቃሉ ዓይነት “ነባር ስም” ይባላል።
የግእዝ ቃላት በሁለት ይከፈላሉ ነባርና ዘር፤ ስለዚህ “ሕዝብ” ነባር ነው።
·
የቃሉ ይዘት “ውስጠ ብዙ” ይባላል። ማለትም
ብዙ ሰዎች እንደማለት ነው።
ከዚህ ላይ አቶ ተወልደ
የተናገረውን ታላቅና መሠረታዊ ነጥብ መጥቀስ ይገባል።
“በአንድ ብልቃጥ ወይም
ብርጭቆ ውስጥ ያለ ስኳር ስኳሮች አትለውም ስኳር ነው የምትለው” በማለት ሕዝብ የሚለውን ቃል ውስጠ ብዙነት አሳይቷል።
እንደ ተባለው በአንድ
አገር የሚኖሩ፤ በአንድ ባሕል፤ በአንድ ቋንቋ፤ በአንድ ሕገ መንግሥት አንድ ለሆኑ ብዙ ሰዎች የሚሰጥ ስያሜ ነው።
ማለትም በአንድነት አቅፎ
በያዛቸው አንድ ጠርሙስ ውስጥ ተጠቃለዋል ማለት ነው። ስለዚህ የሚጠሩት በአንድነት ስያሜያቸው ነው። በሌላ አባባል ውሕደታቸው ወይም
አንድነታቸው ነው እነሱን ተክቶ የሚጠራው። አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ በዚሁ ቃል ላይ የሰጡትን ትንታኔ መጨረሻ ላይ እገልጸዋለሁ።
·
ሕዝብ የሚለው ቃል በግእዝ ቋንቋ አልፎ አልፎ “አሕዛብ” በማለትም ሲበዛ ይገኛል።
ግን “ሕዝብ” ራሱ ብዙነትን የሚገልጽ ስለሆነ “አሕዛብ” የሚለውን
ሊቃውንቱ “የብዙ ብዙ” ይሉታል። ከብዙም ያለፈ ለማለት ነው። ምክንያቱም ብዙውን ነገር እንደገና አሁንም ካበዛነው የብዙ ብዙ ሆነ
ማለት ነው።
በግእዝ መዝገበ ቃላት መሠረት “ሕዝብ” = በቁሙ በአማርኛም ሕዝብ ይባላል። እንዲሁም ወገን ተብሎም ይተረጎማል።
ቃሉ እንደ ተነጋገርነው ውስጠ ብዙ ይባላል ወይም ነው። ስለዚህ፣ ለአንድ፤ ለብዙ፤ ለወንድ፤ ለሴት፤
ለሁሉም ይሆናል። ማለትም ለአንድም ለብዙም ለሴትም ለወንድም ያገለግላል።
ሌላው
ሕዝባዊ ሕዝባውያን፤
ሕዝባዊት ሕዝባውያት በመባልም ተገልጾ ይገኛል። በዚህ አገላለጽ ወገንነትን የሚገልጽ ቅጽል ሲሆን በቁሙ የሕዝብ ወይም የምእመናን
ወገን፤አካል ወዘተ ማለት ነው።
ሌላው ሥልጣነ ክህነት የሌለው ካህን ያልሆነ ምእመን ወይም ምእመናን ማለትም
ነው። ይህንን አገላለጽ በተለይ በቅኔ ቤት አዘውትረን የምንጠቀምበት ሲሆን አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌም በመዝገበ ቃላት መጽሐፋቸው
ገልጸውታል። ሕዝብ አገር ማለትም ይሆናል።
“ሕዝብ” የሚለው ቃል በግእዝ ቋንቋ ጥቅም ላይ ሲውል፤
የብዙና የነጠላ የሁለቱንም
ግስ ወይም አንቀጽ (ቨርብ) ይወስዳል። ማለትም በብዙ ቁጥርም በነጠላ ቁጥርም እንገለገልበታለን። በዚህ መሠረት ከአማርኛው አጠቃቀም
ይለያል ማለት ነው።
ምሳሌ1. በነጠላ ሲያገለግል
1. “ሕዝብ
ዘይነብር ውስተ ጽልመት ርእየ ብርሃነ ዓቢየ” ኢሳ. 9፡2 = የአማርኛ ትርጉሙ በጨለማ ውስጥ የኖረ ወይም የሚኖር ሕዝብ
ብርሃንን ዐየ ማለት ነው።
ከዚህ
ላይ የአንድን ነጠላ ቃል አንቀጽ ይውሰድ እንጅ ነቢዩ የሚገልጸው በጥቅሉ የሰውን ዘር ወይም ሰብአዊ ፍጡርን ስለሆነ ውስጠ ብዙ
የሚያሰኘው ይህ ነው። ምክንያቱም በአዳምና በሔዋን አለመታዘዝ ምክንያት በጨለማ ይኖር የነበረውና በክርስቶስ ልደት ብርሃንን ያየ
ሰብአዊ ፍጡር ሁሉ ነው።
ምሳሌ 2. በብዙ ቍጥር ሲያገለግል
2. “እስመ አበሱ ሕዝብከ
ዘአውጻእከ እምድረ ግብጽ” ዘፀ. 32፡7 በአማርኛ = ከግብጽ ምድር ያወጣሃቸው ሕዝብህ (ወገኖችህ ሰዎችህ)
በድለዋልና፤ ማለት ነው። “አበሱ” የሚለው ግስ ወይም ቨርብ ለብዙ የሚሆን ግስ ነው። በመሆኑም በግእዝ ያለው ልዩነት የብዙ ቝጥርን
ግስ በመጠቀሙ ነው።
እኔ ለማስርጃ ያህል እነዚህን አቀረብኩ እንጅ ቃሉ በብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች በአንድም በብዙም ቍጥር በስፋት ተጠቅሶ
ይገኛል። አሁን በአማርኛ ደግሞ እንይ።
“ሕዝብ” የሚለው ቃል በአማርኛ ቋንቋ ጥቅም ላይ ሲውል፤
እንደተነጋገርነው
ቃሉ ሳይለወጥ በአማርኛ ቋንቋ ስንጠቀምበት ግን ከግእዙ የሚለይበት መለያ አለው። ይህም በአማርኛ ሕዝብ የሚለው ቃል የብዙ ቁጥር
ግስን ወይም አንቀጽን (ቨርብን) አይወስድም።
በመሆኑም በአማርኛ “ሕዝብ መጣ” ይባላል እንጅ
“ሕዝብ መጡ” አይባልም። ስለዚህ ከግእዙ አማርኛው ለየት ያለ አጠቃቀም አለው
ማለት ነው። ሌላው ብዙ ሕዝብ መጣ ስንል ያለምንም የፆታ ልዩነት ብዙ ሴቶችን ወይም ብዙ ወንዶችንም ሁሉ የሚወክል አነጋገር ነው።
ቃሉ
በአማርኛ የብዙ ቍጥር ግስን (ቨርብን) አይውሰድ እንጂ የብዙ ቍጥር ቅጽልን (አድጀክቲብን) ግን ይወስዳል ። እንደሚከተለው
ማለት ነው ።
“ብዙ ሕዝብ” ይላል። ስለዚህ “ብዙ”
ከአንድ በላይ የሆነ ነገርን የሚገልጽ ቅጽል ወይም ገላጭ(አድጀክቲብ) ነው። “ብዙ” የሚለው ቃል ከላይ እንደተገለጠው በጠርሙሱ
ውስጥ ያሉትን ይገልጻል እንጅ ጠርሙሱን አይገልጽም። ስለዚህ አሁንም ውስጠ ብዙ፤ በጥቅል የሚነገር የወል ስም መሆኑን ነው የሚያሳየው።
“ሰው” እንደሚለው ቃል ማለት ነው። “ሰው”
ወይም “ብዙ ሰው ወይም ሰው መጣ” እንጂ “ብዙ ሰው ወይም “ሰው መጡ” አይባልም።
ቃሉ
የሚያሳየው መሠረታዊ ነጥብ ግን በአንድ ሕብረት ውስጥ ያሉ አንድ ባደረጋቸው የሕብረት
ትስሥር ውስጥ በአንድነት የተዋሐዱ ወይም የተጠቃለሉ ብዝኃነታቸውን አንድነታቸው ያጠቃለለው ብዙ ሰዎችን ነው።
አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ በመዝበ ቃላት መጽሐፋቸው ገጽ 439 ላይ ሰፋ አድርገው እንደሚከተለው አብራርተውታል።
ሕዝብ፡ ብዙ ሕዝብ፤
ሕዝብ በቁሙ ወገን፤ ነገድ፤ የተሰበሰበ ብዙ ሰው፤ ጉባኤ፤ ሸንጎ ማለት ነው፡ ካሉ በኋላ
“የአንዲት አገር የአንዲት ከተማ ወይም የአንድ ብሔር የአንድ መንግሥት ሰው፤ ቋንቋውና ሕጉ አንድ
የሆነ በአንድ ሕግ የሚኖር” ማለት ነው ይላሉ።
በሕገ መንግሥቱ የተጠቀሰውን ትርጉም የሚይዘው ይህ ትንታኔ ሳይሆን አይቀርም ብየ አምናለሁ።
ይህንን ርእስ ወይም ቃል በተመለከተ የበለጠ ማብራርያ ከፈለጋችሁ
የሚከተሉትን የመጻሕፍት ጥቅሶችና መዝገበ ቃላት መመልከት ትችላላችሁ
·
ዘፀ. 32፡6
·
ኢሳ. 18፡2
·
ሚክ. 4፡7
·
ዘፍ. 12፡2
·
ዘዳ. 32፡6
·
መሳ. 21፡3
·
የኪዳነ ወልድ ክፍሌ መዝገበ ቃላት ገጽ439፤ እንዲሁም
·
የአማርኛ መዝገበ ቃላት ገጽ እና
·
“መጽሔተ አእምሮ ብሔራዊ ቋንቋ ዘኢትዮጵያ”ን በ “ሐ” ፊደል ስር የሳድስ ነባርን ተመልከቱ።
ልዑል አምላክ ማስተዋሉን
ያድለን
ከአውደ ጥናት ዘግእዝ
No comments:
Post a Comment