Friday, May 15, 2015

ግእዝ ክፍል 24

የግእዝ ትምህርት ክፍል 24


ሰላም ለሁላችሁ ይሁን እንኳን ለብርሃነ ትንሣኤው አደረሳችሁ

ባለፈው በክፍል 23 ትምህርታችን “አውደ ጥናት” ስለምትባል አንዲት እናት በግእዝ ቋንቋ አጭር ታሪክን ጽፌላችሁ ነበር። ይህ ክፍል ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ በግእዝ ቋንቋ ብቻ የተዘጋጀ ነበር። ይህንንም ያደረግሁት ልምምድ እንድታደርጉ እንደ መመሪያ እንዲሆናችሁ በማሰብ ነው።
ዛሬ በክፍል 24 ትምህርታችን ደግሞ ትርጉሙንና ተጨማሪ ማብራርያን  እነግራችኋለሁ(የክፍል 23ን ማለት ነው)። እያንዳንዳችሁም የራሳችሁን ታሪክ ለመጻፍ ሞክሩ።
አንድ ታሪክ ለመጻፍ እንደሚታወቀው ሦስት ነገሮች ወይም ክፍሎች መኖር አለባቸው። እነዚህም
1.      መግቢያ
2.     ዋና ታሪክ እና
3.     መዝጊያ ወይም ማጠቃለያ ያስፈልገዋል። ይህ ማለት ስለ ምን መናገር እንደ ፈለግን ለአድማጮቻችን  እንናገራለን (ይህ መግቢያ ይባላል)

መናገር የምንፈልገውን ፍሬ ሐሣብ በዝርዝር እንናገራለን (ይህ ዋና ታሪክ ወይም የጽሁፉ ዋና ክፍል ይባላል)
እንደ ገና የተናገርነውን ታሪክ ባጭሩ ፍሬ ሐሳቦችን ብቻ ለአድማጮቻችን  እንነግራቸዋለን (ይህ ማጠቃለያ ይባላል)

በሌላ አገላለጽ መግቢያው ቀድመው ስለሚሰጠው ታሪክ እንዲያስቡና ምን ዓይነት መልእክትና ፍሬ ሐሳብ እንደሚኖረው ለመገመትና በተገቢው መልኩ ለመከታተል እንዲችሉ ይረዳቸዋል።

ዋናው ንግግር ታሪኩን በልዩ ልዩ ማስረጃና ድጋፍ ማስተማር ማለት ነው ስለዚህ አድማጮቹ ፍሬ ሐሣቡን እስከ ማስረጃው አዳመጡ።
ማጠቃለያው ደግሞ ከሰሙት ታሪክ መካከል ባጭሩ ፍሬ ሐሳቦችን ብቻ ጨምቆ ወይም አጣርቶ በማውጣት ስለሚነገር ከረጅሙ ንግግር ውስጥ ፍሬ ሐሳቦችን ቶሎ ማስታዎስ እንዲችሉ ይረዳቸዋል።

እነዚህ ሦስት ነገሮች የአንድ ታሪክ አካላት ናቸው። የአጻጻፍ ስልታቸው ግን ሊለያይ ወይም ሊያጥርና ሊረዝም ይችላል።
በዛሬው ትምህርታችን ግን ባጭር አጠቃቀም ብቻ እናያለን።

ከዚህ በላይ ያለው አገላለጽ ብዙጊዜ  ለመጻሕፍት (መጽሐፍ ስንጽፍ) ለሌሎችን ጥናታዊ ጽሁፎችን ስናዘጋጅ ለመሳሰሉት የምንጠቀምበት ነው። ከተቻለ ለማነኛውም ንግግር በዚህ ዓይነት ምልኩ ማቅረቡ ይመረጣል ። ካልሆነ ግን

በመልካም ምኞት ወይም በሰላምታ መጀመርና መደምደም እንችላለን / ለምሳሌ እንደምን አደራችሁ በማለት የንግግራችንን ርእስ ብቻ በመጥቀስ እንጀምራለን; ስንጨርስም ለሰሚወቻችን መልካም ምኞትን በመመኝት መልካም አዳር በማለት በመሳሰሉት የእምነት ጉባኤ ከሆነ (እግዚአብሔር ለመስማት የተዘጋጀን ያድርገን፤ የሰማነውን በልቡናችን ይጻፍልን በማለት መጀመርና መጨረስ እንችላለን ።


አሁን የክፍል 23ን መግቢያ፤ ዋና ፍሬ ሐሣብና ፤ ማጠቃለያ እንመልከት
መግቢያ
ሰላም ለክሙ አኃውየ ወአኃትየ አርድእተ ልሳነ ግእዝ ኩልክሙ። (ይህ ሰላምታ ነው)

ዮምሰ ፈቀድኩ ከመ እምሀርክሙ ልሳነ ግእዝ በልሳነ ግእዝ ባህቲቱ። ወእስእለክሙ ከመ ትስምኡ ወታጽምኡ በእዝነ ልቡናክሙ፤ ወትነጽሩ በዐይነ ልቡናክሙ። ኅበ ዜና አሐቲ ብእሲት ዘእዜንወክሙ ድኅረ ሰለስቱ ቅጽበታት።
 ዮም በእሥራ ወሰለስቱ ክፍለ ትምህርትነ እዜንወክሙ በይነ አሐቲ ብእሲት ዘስማ አውደ ጥናት። (መመሪያ)

(ሰላም ለክሙ/ለክን/ለኪ/ለከ (አንድ ወንድ ካለ ብዙ ሴቶች ቢኖሩም በወንዶች አንቀጽ ነው የሚጠራው)

(ዮም፤ ናሁ
እነግረክሙ፤
እዜንወክሙ፤

እዜንወክሙ በይነ አሐቲ ብእሲት ዘስማ አውደ ጥናት።

(ዮም እነግረክሙ፤እዜንወክሙ፤
እዜንወክሙ በይነ አሐቲ ብእሲት።


ዋናው ታሪክ
ቅድመ ሰለስቱ ዓመታት
 እንዘ አሀውር በፍንወት ረከብኩ እቤርተ ዕድሜ ብእሲተ ዘስማ አውደ ጥናት፤ ወስመ ጥምቀታ ወለተ ማርያም። ወይእቲሰ እምነ ነገደ ኢትዮጵያ። ወብእሲት ነበበተኒ ከመ ወለደት ብዙኃነ ደቂቀ እለ ይነብሩ ዝርዋነ በውስተ ኵሉ ዓለም ወሰአለተኒ ከመ እምሀር ላቲ ደቂቃ ልሳነ ግእዝ ወቅኔ ወአነኒ እቤላ ኦሆ።
ማጠቃለያ/መዝጊያ
ተፈጸመ ዜና ሕይወታ ለብእሲት

ናሁ እጤይቀክሙ ሐምስተ ጥያቄያተ እለ ወጽኡ እምነ ዜናሃ ለብእሲት ዘዜነውኩክሙ በዛቲ ዕለት

(ይህ ክፍል ሊረዝም ይችል ነበር። ማጠቃለያ ሲባል በዋናው ታሪክ ውስጥ የተጻፉትን በአጭሩ እንደ ገና መግለጽ ነው። ከዚህ ላይ ግን ታሪኩ ማለቁን በመናገር እና ከታሪኩ ውስጥ ጥያቄዎችን በማውጣትና በመጠየቅ ይጨርሳል። በመሆኑም በተዛዋሪ መንገድ ማጠቃለያ ተሰጠ ማለት ነው።


ግእዝ ክፍል 25

የግእዝ ትምህርት ክፍል 25


በዛሬው በክፍል 25 ትምህርታችን ስለ አንቀጽና አጠቃቀሙ እንማራለን
አንቀጽ፡ ማለት በዚህ ትምህርታችን መሠረት ማሠሪያ፤ ማለት ነው። ማሠርያ አንቀጽ፤ ግሥ፤ በመባልም ይጠራል።
ማሠርያ፦ ማለት ደግሞ የአነጋገር ወይም የንግግር በሌላ አባባል የዐረፍተ ነገር ማጠቃለያ፤ ማቆሚያ፤ መቋጫ፤ ወይም ማሠርያ፤ ማለት ነው። በእንግሊዘኛው (verb) ቨርብ የሚባለው ነው። አንድ ዐረፍተ ነገር ዐረፍተ ነገር ተብሎ ሊጠራ የሚችለው ቢያንስ አንድ ማሠሪያ አንቀጽና አንድ ባለቤት ሲኖሩት ብቻ ነው።

የግስ ዓይነቶች እንደየ ዐረፍተ ነገሩ ወይም የዐረፍተ ነገሩ ባለቤት በብዙ ሊከፈሉ ይችላሉ። ለዛሬው ግን 4 ዓይነት የአነጋገር ክፍሎችን ወይም ጊዜያትን እንማራለን። እነዚህም
1.      ዘወትር ለሚደረግ ድርጊት(present sentences)

2.     በመደረግ ላይ ወይም በሂደት ላይ ላለ ድርጊት (present continue sentence )
3.     ላለፈ ድርጊት እና (past)
4.     ለትንቢታዊ ወይም ወደ ፊት ለሚደረግ እቅድ (future sentence) የምንጠቀምባቸው የግሥ ዓይነቶች ናቸው።
ስለዚህ አንድ አንቀጽ ከዚህ በላይ ለተገለጹትና ለሌሎችም የክንውን ዓይነቶች ሊያገለግል ወይም ሊጠቅም ይችላል። በሌላ አባባል አንድ አንቀጽ እንደ ድርጊቶቹ የአፈጻጸም ጊዜያት ይለዋወጣል ወይም ከመጀመሪያው፤ ከመጨረሻው የሚገኙ ሆሄያትን በመለወጥ፤ አዲስ ሆሄን በመጨመር፤ እንዲሁም አገባቦችን በመጠቀም ለልዩ ልዩ የንግግር ስልት ይወላል።
የተጠቀሱትን በዐረፍተ ነገር እያስገባን አንድ በአንድ እናያለን። ለዚህ ትምህርታችን “ቀደሰ” ፤“ሰብሐ”፤ “ሆረ” ፤ “ቆመ”፤“ቆርበ(ቆረበ)”፤ “ተንሥአ”፤ “በከየ”፤ “መጽአ” ፤ “ነበረ” የሚሉትን ግሦች እንጠቀማለን።

አንቀጽ፦ ለአንድ ወይም ለነጠላ ሲሆን ሲበዛ “አናቅጽ” ይሆናል። አናቅጽ ተብለው የሚጠሩ 6 ሲሆኑ 4ቱ አበይት 2ቱ ደግሞ ንዑሳን አናቅጽ ይባላሉ። (ሁለቱ ንዑሳን አናቅጽ እንደ አንድ ሊቆጠሩ ይችላሉ)

4ቱ አበት አናቅጽ (main verbs) የቢባሉት

1.      ሃላፊ(ቀዳማይ ተብሎም ይጠራል መጀመሪያ ማለት ነው) ይህኸም  ቀደሰ = አመሰገነ የሚለው ነው።
2.      ትንቢት(ካልአይ ተብሎም ይጠራል ሁለተኛ ማለት ነው) ይህኸም ይቄድስ = ያመሰግናል የሚለው ነው።  (ይህ አንቀጽ ዘወትር ለሚደረግ ተደጋጋሚ ድርጊትም ያገለግላል)
3.      ዘንድ (ሳልሳይ ተብሎም ይጠራል ሦስተኛ ማለት ነው) ይህኸም ይቀድስ =  ያመሰግን ዘንድ የሚለው ነው።  (ዘንድ አንቀጽ ከሁሉም ከሃላፊ፤ከትንቢት፤ ከትእዛዝም አናቅጽ ጋር ያገለግላል)
4.     ትእዛዝ (ራብአይ ተብሎም ይጠራል አራተኛ ማለት ነው) ይህኸም ይቀድስ = ያመስግን የሚለው ነው።  1ኛ፤2ኛ/3ኛ/4ኛ የተባሉበት ምክንያት በአቀማመጥ ወይም በግሥ ርባታ ቅደም ተከተላቸው ስለሆነ ነው።

ዘንድ እና ትእዛዝ አናቅጽ የሚባሉት ወይም የመጨረሻዎቹ (ሳልሳይና ራብአይ) በአጠቃቀምና በትርጉም ማለትም ወደ አማርኛ ስንተረጉማቸው እና በዐረፍተ ነገር ውስጥ ስናስገባቸው ካልሆነ በስተቀር ወይም “ህገወጥ” በሆኑ ግሦች ካልሆነ፤ በሆሄም፤ በድምጽም አንድ አይነት ናቸው።(በመሠረታዊው ግሥ ማለትም በሦስተኛ መደብ በአንድ ወንድ ብቻ)

ንዑሳን የሚባሉት አናቅጽ
ቀድሶ -ቀድሶት= ትርጉማቸው ማመስገን ማለት ነው። ሁለቱም ዓንድ ዓይነት ትርጉም ሲኖራቸው በሆሄ ግን ይለያያሉ።
·         ቀድሶ
·         ቀድሶት
የሚባሉት ሲሆኑ ትርጉማቸውም አንድ ነው ሲገሰሡም አብረው ተያይዘው ይጠራሉ። በዐረፍተ ነገር ሲገቡ ግን ተለያይተው ይገባሉ ። ተዘውትሮ የተለመደ ባልሆነ ልዩ ዓይነት አጠቃቀም ካልሆነ በስተቀር ንዑሳን አናቅጽ ማሠሪያ አናቅጽ ሳይሆኑ እንደ ስም የሚያገለግሉ ናቸው።

ምሳሌ_1
ገብረ ኢየሱስ ሆረ ኀበ ብሔሩ ቅድመ አሐዱ ወርኅ። (ቅድመ የሚለው አገባብ ያለፈ ጊዜን ይጠቁማል ትርጉሙ በፊት ቀድሞ ማለት ነው)
የሐውር ኀበ ብሔረ ብእሲቱ ድኅረ ሰለስቱ ዕለታት። ወውእቱሰ ኢፈቀደ ይሁር ኀበ ብሔረ ብእሲቱ አላ፣ ይቤ አቡሁ ይሁር! (ዘንድ አንቀጽ ተጨማሪ ሌላ አንቀጽን ስለሚጠቀም በዚህ ምሳሌም “ኢፈቀድ” የሚለውን ተጠቅሟል)።

ትርጉም፡ = ገብረ ኢየሱስ ወይም የኢየሱስ አገልጋይ ከአንድ ወር በፊት ወደ አገሩ ሄዷል፤ ከሦስት ቀናት በኋላ ደግሞ ወደ ሚስቱ አገር ይሄዳል፤ እሱ ግን ይሄድ ዘንድ (ወደ ሚስቱ አገር) አልወደድም፤(አልወደደም ነበር) ነገር ግን አባቱ ይሂድ! አለ (እንዲሄድ አዘዘው)

ምሳሌ 2 በአጭር አገላለጽ
ካህን ቀደሰ (ትማልም)
ይህ ዐረፍተ ነገር ያለፈ ነው
ካህን ይቄድስ (ጌሰመ)
ይህ ዐረፍተ ነገር ትንቢታዊ ነው (ወደፊት የሚሆን)
ካህን ይቀድስ ቆመ (ከመ ይቀድስ ቆመ)
ይህም ሃላፊ ነው ግን ማሳየት የተፈለገው ዘንድ አንቀጽን ነው ስለዚህ ዘድ አንቀጽ ግዴታ ሌላ ተጨማሪ አንቀጽን ይፈልጋል።
ገብረ ማርያም፣ ይቀድስ !
ይህ ትዕዛዝ መስጫ ወይም ትእዛዝ አንቀጽ ነው። ለምሳሌ፦
1.      ቀድስ (አመስግን)!
2.     ንአ (ና)!
3.     ሑር (ሂድ)!
4.     ተንሥእ (ተነሥ)!
5.     ንበር (ተቀመጥ)!
እንደ ማለት ሲሆን  ገብረ ማርያም ይቀድስ የሚለው ከዚህ በላይ ከተጠቀሱት 5 ትእዛዝ አናቅጽ የሚለየው ለሦስተኛ መደብ ስለሆነ በተዘዋዋሪ ወይም በመልእክት የሚታዘዝ በመሆኑ ነው። ከዚህ በላይ የተዘረዘሩት 5ቱ ግን ቀጥታ ፊት ለፊት ከአንደኛ መደብ ለሁለተኛ መደብ የሚሰጡ ትእዛዛት ስለሆኑ ነው።

ምሳሌ 3፦የትንቢትና ዘንድ አናቅጽ ተጨማሪ አገልግሎት
ይቄድስ፦ ይህ መሠረታዊ አገልግሎቱ ትንቢታዊ ሲሆን ተዘውትሮ ለሚደረግ ድርጊትም ይሆናል
 (አገባቦችን በመጠቀምም ሆነ ብቻውን)

·         ካህን ይቄድስ ኵለሔ(ኵለሔ ይቄድስ) = ካህን (ቄስ፣ዲያቆን፤ ጳጳስ) ሁልጊዜ ያመሰግናል (ይቀድሳል)
·         ስብአ ለእለትየ እሴብሐከ = ( ሰባት ጊዜ በቀን አመሰግንሃለሁ። መዝሙር 119፡164)
·         ውእቱ ይበኪ ከመ ሕጻን

ይቀድስ፦ ይህ መሠረታዊ አገልግሎቱ ዘንድ አንቀጽ ሲሆን ሌላ ሁለተኛ አንቀጽን በመጠቀም ከሃላፊ፤ከትንቢት፤ እና ከትእዛዝ ድርጊቶችም ጋር ያገለግላል።

ውእቱ/ካህን
መጽአ ይቀድስ፤ = እሱ(ካህኑ) ያመሰግን (ይቀድስ) ዘንድ መጣ። ይህ ዐረፍተ ነገር ሃላፊ ነው።
ቀደሰ  ይቍረብ = እሱ(ካህኑ) ይቆርብ ዘንድ ቀደሰ። ይህም ዐረፍተ ነገር ሃላፊ ነው።
ይቄድስ ይቍረብ = እሱ(ካህኑ) ይቆርብ ዘንድ ይቀድሳል። ይህ ዐረፍተ ነገር ዘወትር የሚደረግ እና ትንቢትም ሊሆን ይችላል።
ይቀድስ ይቍረብ = እሱ(ካህኑ) ይቆርብ ዘንድ ይቀድስ። ይህ ዐረፍተ ነገር ትእዛዝ ነው።
ይሐውር ይብላእ = እሱ(ካህኑ) ይበላ ዘንድ ይሄዳል። ይህ ዐረፍተ ነገር ትንቢትም፤ ዘወትር የሚደረግም ሊሆን ይችላል።
ይሁር ይብላእ = እሱ(ካህኑ) ይበላ ዘንድ ይሂድ። ይህ ዐረፍተ ነገር ትእዛዝ ነው።
በሚቀጥሉት ተከታታይ ክፍሎች እያንዳንዱን ግሥ በሰፊው እናያለን