Sunday, May 16, 2021

የመጻሕፍት ትርጓሜ፡ አራተኛው የቤተ ክህነት ትምህርት ክፍል

የመጻሕፍት ትርጓሜ፥ አራተኛው የቤተ ክህነት የትምህርት ክፍል

የመጻሕፍት ትርጓሜ የሚባለው አራተኛው ክፍል ሲሆን በውስጡ አራት አበይት ክፍሎችን የያዘ ነው፡ እነሱም 
  • የብሉያት = 46 መጻሕፍት
  • የሐዲሳት = 35 መጻሕፍት
  • የሊቃውንት = 3 መጻሕፍት 
  • የመጽሐፈ መነኮሳት = 3 ክፍሎች ያሉት አንድ መጽሐፍ ትርጓሜ ዎች ናቸው፡
መጻሕፍት ለመግዛት የሚከተለውን ራሱ መጽሐፉን ይጫኑ ወደ አማዞን ይወስደዎታል፡ ከአማዞን መግዛት ካልቻሉ በ+1 703 254 6601 ይደውሉ በአድራሻዎ ይላክለዎታል

የትርጓሜ መጻሕፍት

ትርጓሜ መጻሕፍት የሚባለው የትምህርት ክፍል ከስያሜው እንደምንረዳው የቅዱሳት መጻሕፍትን ተደራራቢ ትርጉም እና ምሥጢር በማመሥጠርና በማራቀቅ ታሪካዊ ምንጫቸውንና ማስተላለፍ የሚፈልጉትን መንፈሳዊ መልእክት በመረዳት ማስረዳት ነው፤ የትርጓሜ መጻሕፍት ትምህርትን መማር የሚችለው የቅኔ ትምህርትን የተማረ ተማሪ ብቻ ነው።

ትርጓሜ መጻሕፍት የሚባለው የትምህርት ክፍል በአራት አበይት ክፍሎች ይከፈላል፤ እነሱም ከዚህ በታች በተራ በቅደም ተከተል የተጠቀሱት ናቸው።

1.  መጻሕፍተ ብሉያት - 46ቱ የበሉይ ኪዳን መጻሕፍት

2.  መጻሕፍተ ሐዲሳት - 35ቱ የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት

3.  መጻሕፍተ ሊቃውንት - ሐይማኖተ አበው፣ ፍትሐ ነገሥት፣ አቡሻክር (ባህረ ሐሳብ)

4.  መጻሕፍተ መነኮሳት - ማርይሳቅ፣ ፊልክስዮስ፣ አረጋዊ መንፈሳዊ

በነዚህ የትምህርት ደረጃዎች ሁሉ መምህራኑ የእምነትን የገብረ ገብነትን እና የትህትናን ባጭሩ የመልካም ሥነ ምግባርን ትምህርት ያስተምራሉ። እነዚህም

·        ፈሪሀ እግዚአብሔርን- እግዚአብሔርን መፍራት

·        ኀፊረ ገጽን - ታላላቆችን ማክበርና በአክብሮት መፍራት

·        አትሕቶ ርእስን - በታላላቆች ፊት በትህትና ራስን ዝቅ አንገትን ደፋ ማድረግ

·        ገቢረ ሠናይ - መልካም ነገርን መሥራት ወይም ማድረግ ወዘተ ናቸው።

·        ምንጭ፡ “ትዝታዬ” መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ

የመጻሕፍትን ትርጓሜ ትምህርት የጀመሩት ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት እንደሆኑ የመጻሕፍት ትርጓሜ ሊቃውንት ይተርካሉ።

 

ልዑል አምላክ ማስተዋሉን ያድለን

ከአውደ ጥናት ዘግእዝ


Saturday, May 1, 2021

ስለ ክርስቶስ ሥጋዌና ሰሙነ ሕማማት ሳምንት 52 ጥያቄዎችና መልሶቻቸው

 52 ጥያቄዎችና መልሶቻቸው በክርስቶስ ሥጋዌና የመጨረሻዎቹ ሳምንታት የመከራ ጉዞ አንዲሁም የትንሣኤ ድል




ሰላም ጤና ይስጥልኝ ከአውደ ጥናት ነው፣ ዛሬ ወቅቱን መሠረት በማድረግ በክርስቶስ ሥጋዌና ከሰሙነ ሕማማት እስከ 50ኛው ቀን ድረስ ያሉትን ክስተቶች አልፈን አልፈን በጥያቄ መልክ እንመለከታቸዋለን ተከታተሉ።

 መጻሕፍቶቼን ለመግዛት ከዚህ በታች ያለውን ራሱ መጽሐፉን ይጫኑ ወደ አማዞን ይወስደዎታል፣ ከዚያ በኍላ የሚፈልጉትን መጽሐፍ መምረጥ ይችላሉ፡ ወይም በ+1 703 254 6601 ደውለው ያነጋግሩኝ በአድራሻዎ ይላክለዎታል። I am directing you to Amazon market place.


1.   ሥጋዌ ማለት ምን ማለት ነው? ሰው መሆን

2.   የአምላክ ወይም የእግዚአብሔር ቃል የሥጋዌ ስሞች የትኞቹ ናቸው? አማኑኤል፣ ክርስቶስ፣ ኢየሱስ፣ መድኃኔ ዓለም

3.   ክርስቶስ ለመጀመሪያ ጊዜ  ከሆሳዕና ዕሁድ እስከ ትንሣኤ ዕሁድ ድረስ የተደረገውን ታሪክ ያሳለፈው ወይም ጥንተ ዕለታት የሚባሉት ቀናት በየትኛው ወርና በየትኛው ቀን ነበር የዋሉት?

ወሩ፡ መጋቢት ሲሆን ቀኑ ደግሞ ከመጋቢት 22 እስከ መጋቢት 29 ድረስ ነበር ዓመተ ምህረቱ 34 ዓመተ ዓ/ም አካባቢ ነው?

4.   አምላክ ለምን ሥጋን ለበሰ መከራንስ ለምን ተቀበለ ለምንስ ተሰቀለ?

አጭሩ መልስ ስለሚወደን እና በአዳምና በሔዋን አለመታዘዝ ምክንያት የተፈረደብን የዘላለም ሞት በፍጡራን ሊወገድ ስለማይችል ንፁሐ ባሕርይ የሆነው አምላክ ሞታችንን በሞቱ ለማስወገድ ነው

“ወበእንተ ኃጣውኢነ ውእቱ ተሰቅለ ዲበ እፀመስቀል፡ በሥጋሁ ከመያውፅአነ እምኃጣውኢነ ወበጽድቁ ያሕይወነ” (ስለ ኃጢአታችን በመስቀል ላይ ተሰቀለ፣ በእርሱ ጽድቅም እኛን ሕያዋን አደረገን 1ኛ ጴጥ 2፡24)

5.   ሕማማት፤ ሰሙነ ሕማማት፣ ማለት ምን ማለት ነው፡ የሕማማት ሳምንት፤ ሕማም ሕመም፣ ሥቃይ መከራ ማለት ሲሆን ሕማማት ማለት በብዙ ነው። ስለዚህ በክርስቶስ ላይ የደረሱትን የሥቃይ እና የመከራ ዓይነቶች ለመጥቀስ ነው።

6.   ከደብረ ዘይት ተራራ አጠገብ ወደሚገኙት ወደ ቤተ ፋጌና ወደ ቢታንያ ሁለት ደቀ መዛሙርትን ማንም ሰው ያልተቀመጠበት የአህያ ውርንጫ ታሥሮ እንደሚያገኙና ፈትተው እንዲያመጡት ሲያዛቸው ከተጠየቁ ምን እንዲሉ አዘዛቸው? “ጌታ ይፈልገዋል በሏቸው”

7.   በሆሳዕና ዕለት ክርስቶስ ከቢታንያ ወደ ኢየሩሳሌም የሄደው በምን ነበር? ከዚያ በፊት ማንም ሰው ባልተቀመጠበት በአህያ ውርንጫ

8.    በሆሳዕና ሕዝቡ ክርስቶስን የተቀበለው ወይም ያጀበው ምን ይዞ ነው? ምን እያለስ ያመሰግን ነበር? የዘንባባ ዝንጣፊ፣ ሆሳዕና በአርያም ለወልደ ዳዊት፤ እንዲሁም “በጌታ ስም የሚመጣ ንጉሥ የተባረከ ነው በሰማይ ሰላም በአርያምም ክብር አሉ”

9.   ክርስቶስ እንዲያዝና በመስቀል ላይ ተሰቅሎ እንዲሞት ጸሐፍትና ፈሪሳውያን በስብሰባቸው የወሰኑት መቸ ነበር? መጋቢት 25 ቀን ረቡዕ ነበር (ረቡዕ ከ7ቱ አጽዋማት ገብቶ እንዲጾም የተደረገውም ይህንኑ ለማሰብ ነው)

10.  በዕለተ ሐሙስ ክርስቶስ የፋሲካን ራት እንዲያዘጋጁለት የላካቸው ሁለቱ ሐዋርያት የትኖቹ ናቸው? ቅዱስ ጴጥሮስና ቅዱስ ዮሐንስ

11.  ክርስቶስ በጌቴሴማኒ በሚጸልይ ጊዜ ሐዋርያት ምን ሢሰሩ ነበር? ተኝተው ነበር

12.  በመጨረሻው የጌታ ራት የነበሩት ደቀመዛሙርት ስንት ናቸው፡ 12

13.  ሐሙስ ማታ ክርስቶስ ለያንዳንዱ ሐዋርያ ያደረገው አስደናቂ የትሕትና ሥራ ምን ነበር? እግር ማጠብ

14.  በመጨረሻው የጌታ ራት ሐሙስ ማታ ለሐዋርያት ምን ሰጣቸው ምንስ አላቸው?

ይህ ስለ ብዙዎች የሚሰጠው ቅዱስ ሥጋዬ ነው

ይህ ለብዙዎች የሚፈሰው ደሜ ነው

15.  “ጌታ ሆይ ወደ ወኅኒም ወደ ሞትም ከአንተ ጋር ለመሄድ የተዘጋጀሁ ነኝ” አለው፤ እርሱ ግን እንዳታውቀኝ ሦስት ጊዜ እስክትክደኝ ድረስ ዛሬ ዶሮ አይጮኽም አለው” በዚህ ዐረፍተ ነገር ላይ የሚነጋገሩት ማን እና ማን ናቸው? መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እና ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ ናቸው

16.  ለይሁዳ ገንዘብ በመስጠት ክርስቶስን እንዲያስይዝ ያደረገው  ሊቀካህናት ማን ይባላል? ቀያፋ

17.  በክርስቶስ ምትክ ከእሥራት የተፈታው ወንጀለኛ ማን ነበር? በርባን

18.  ክርስቶስ የተሰቀለው መቼና በስንት ሰዓት ነበር? መጋቢት 27 ቀን ዓርብ ከቀኑ 6 ሰዓት

19.   “አቤቱ በመንግሥትህ አስበኝ” ያለው ማነው? ከክርስቶስ በስተቀኝ በኩል ተሰቅሎ የነበረው ሽፍታ

20.  በመስቀል ላይ ሆኖ የተናገራቸው 7 ዐረፍተ ነገራት የትኞቹ ናቸው

·          አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው

·          እውነት እውነት እልሃለሁ ዛሬ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ

·          አንቺ ሴት እነሆ ልጅሽ፤ እናትህ እነኋት

·          አምላኬ አምላኬ ስለምን ተውከኝ

·          ተጠማሁ

·          ሁሉም ተፈጸመ

·          አባት ሆይ ነፍሴን በጅህ አደራ እሰጣለሁ

21.   ዓርብ ዘጠኝ ሰዓት ነፍሱ ከሥጋው በተለየች ጊዜ በሰማይና በምድር የታዩት 7 ተአምራት የትኞቹ ነበሩ?

·          ጸሐይ ጨለመች

·          ጨረቃ ደም ሆነች

·          ከዋክብር ወደምድር ረገፉ

·          መቃብራት ተከፈቱ

·          ሙታን ተነሡ

·          የቤተ መቅደስ መጋረጃዎች ለሁለት ተከፈሉ

·          ምድር ተነዋወጠች አለቶችም ተሰነጣጠቁ

22.   ከዚህ በላይ የተጠቀሱትን ተአምራት ካዩ በኋል ብዙዎቹ ምን አሉ? ይህስ እውነትም የእግዚአብሔር ልጅ ነበረ አሉ፤

23.  የክርስቶስን ቅዱስ ሥጋ ከጲላጦስ አስፈቅደው በጌቴ ሴማኒ የቀበሩት ሁለቱ ሰዎች ማም ማን ይባላሉ? ዮሴፍና ኒቆዲሞስ

24.  ትንሣኤ ማለት ምን ማለት ነው?

መነሣት ማለት  ሲሆን አንድ ነፍስና ሥጋው ከተለያዩ በኋላ እንደ ገና ነፍስ ካስገኛት ከእግዚአብሔር ሥጋ ደግሞ ከተገኘበት ከመሬት ወይም ከመቃብር ተመልሰው  ተዋሕደው በሕይወት ሲነሱ ነው ትንሣኤ የሚባለው፤ ስለዚህ ለመነሳት መሞት አለ

25.  የክርስቶስ ትንሣኤ ለኛ የሚሰጠው መልእክት ምንድነው?

አምላካችን ክርስቶስ ሞትን ድል አድርጎ እንደተነሣ ሁሉ እኛም ከሞተ ሥጋ በኋላ ተነሥተን የአምላካችንን መንግሥ እንወርሳለን

26.  ክርስቶስ የተነሳበት ዕለት የትኛው ነው? ምን ተብሎስ ይጠራል?

ዕሁድ፣ ሰንበተ ክርስቲያን ይባላል (የክርስቲያን የክርስቶሳዊ በአል)

27.  በክርስቶስ መቃብር ላይ ታትሞ የነበረውን ድንጋይ ያነሳውና በመቃብሩ ኣጠገብ ተቀምጦ የነበረው ማነው? መልአክ

28.  “ እንደተናገረ ተነሥቷልና በዚህ የለም፣ የተኛበትን ስፍራ ኑና እዩ ፈጥናችሁም ሂዱና ከሙታን ተነሣ እንሆም ወደ ገሊላ ይቀድማችኋል በዚያም ታዩታላችሁ ብላችሁ ለደቀመዛሙርቱ ንገሯቸው..” ያለው ማነው? ለማንስ ነው የተናገረው?

ተናጋሪው የጌታ መልአክ ሲሆን የተናገረው ለመግደላዊት ማርያምና ለማርያም ባውፍልያ ወይም የያዕቆብ እናት ማርያም ነበር

29.  ክርስቶስ ከሞት ሲነሣ፡ መቃብሩ ባዶ መሆኑን ያየው የመጀመሪያው ሰው ማነው? መግደላዊት ማርያም ናት

30.  ባዶ ወደ ሆነው መቃብር ለማየት ቀድሞ የገባው የመጀመሪያው ሰው  ማነው፡ ቅዱስ ጴጥሮስ

31.  ክርስቶስ ከተነሣ በኋላ ቅዱሳን ሐዋርያትን ለማየት ሲሄድ ከሐዋርያት ጋር ያልነበረው ሐዋርያ፡ የትኛው ነው? ሐዋርያው ቶማስ

32.  ክርስቶስ ከሞት የተነሣው፡ መቼ ነው? የሳምንቱ የመጀመሪያ ቀን በሆነው በዕለተ ዕሁድ መንፈቀ ሌሊት ነው

33.  ክርስቶስ ከተነሣ በኋላ ከማረጉ በፊት በምድር ላይ የቆየባቸው ቀናት ስንት ናቸው? 40 ቀናት ነው

34.  ክርስቶስ ከሞት ከተነሣ በኋላ ለሐዋርያት የታየበት ባሕር ምን ተብሎ ይጠራል? የጥብርያዶስ ባሕር ይባላል

35.  ክርስቶስ በሐዋርያት መካከል ተገኝቶ የተናገረው ለሥነ ፍጥረት ሁሉ ወሳኝ የሆነ አንድ ዐ/ነገር ምን ነበር? ፡ ሰላም ለናንተ ይሁን አላቸው

36.  ክርስቶስ በስንተኛው ቀን ሞትን ድል አድርጎ ተነሣ? በ3ኛው ቀን

37.  ክርስቶስ ከተነሣ በኋላ በተዋሕዶ የከበረው ሞትን ድል አድርጎ የተነሣው ራሱ ክርስቶስ እንደሆነ ነገር ግን መንፈስ አለመሆኑን ለማረጋገጥ ከሐዋርያት ጋር የበላው ምን ነበር? አሣ ነበር

38.  ክርስቶስ ወደ ሰማይ ያረገው በየትኛው ቦታ ነበር፡ በቢታንያ

39.  ክርስቶስ ወደሰማይ ያረገው በተነሣ በስንተኛው ቀን ነበር፡ በ40ኛው ቀን

40.  ክርስቶስ መንፈስ ቅዱስ ወደ ሐዋርያት ይመጣል በማለት ለሐዋርያት ተስፋ የሰጣቸው መቼና በተነሣ በስንተኛው ቀን ነበር? ወዴትስ እየሔደ ነበር?

·         ሐሙስ ቀን፣

·         በ40ኛው ቀን፣

·         ወደ ሰማይ እያረገ ነበር 

41.  መስቀሉን እንዲሸከም የታዘዘው ሰው ማን ይባላል? ስምኦን

42.   ኤሎሄ፣ ኤሎሄ ላማ ሰበቅታኒ ማለትምን ማለት ነው፡? አምላኬ ሆይ ለምን ተውከኝ ማለት ነው

43.  በይሁዳ አእምሮ ወይም ልቡና የገባው ምን ነበር? ሰይጣን (“ሰይጣንም ከአሥራ ሁለቱ ቍጥር አንዱ በነበረው የአስቆሮቱ በሚባለው በይሁዳ ገባ፣ ሄዶም እንዴት አሳልፎ እንዲሰጣቸው ከካህናት አለቆችና ከመቅደስ አዛዦች ጋር ተነጋገረ..” ሉቃስ 22፡1

44.  ይሁዳ ክርስቶስን በስንት ብር ሸጠው በ30

45.  ይሁዳ ክርስቶስን አሳልፎ ለመስጠት እንደምልክት የተጠቀመው ምንን ነበር? በመሳም

46.  ክርስቶስ የሞት ፍርድ እንደተፈረደበት ሲያውቅ ይሁዳ ምን አደረገ? ራሱን አጠፋ

47.  ክርስቶስ የተሰቀለው በየትና ከማን ጋር ነበር? በቀራንዮ፣ ከሁለት ሺፍቶች ጋር

48.  በክርስቶስ የሞት ፍርድ አልጠየቅም ለማለት ጲላጦስ ምን አደረገ? “ከዚህ ጻድቅ ሰው ድም ንፁህ ነኝ እናንተ ግን ተጠንቀቁ በማለት “እጁን ታጠበ”

49.  ክርስቶስ በተሰቀለበት መስቀል ላይ የተጻፈው ሃይለ ቃል ምን የሚል ነበር? “ክርስቶስ የአይሁድ ንጉሳቸው”

50.  በክርስቶስ ራስ ላይ ያደረጉበት አክሊል ምን ዓይነት ነበር? “የእሾህ አክሊል”

51.  ክርስቶስ ደቀመዛሙርቱን በኢየሩሳሌም በአንድነት ሆነው እንዲጠብቁ ያዛዘዛቸው፡ ለምን ነበር? መንፈስ ቅዱስን ተቀብለው ኃይልን እስከሚያገኙ

52.  ቅዱሳን ሐዋርያት በርስቶስ ትእዛዝ መሠረት በኢየሩሳሌም መንፈስቅዱስን ከተቀበሉ በኋላ ምን ተገለጸላቸው? ወንጌልን የሚይስተምሩበት የዓለማት ቋንቋ

 ቪድዮውን ለመስማት የሚከተለውን ሊንክ ይጫኑ፡ https://youtu.be/2yBl0hHAcFw

ልዑል አምላክ ማስተዋሉን ያድለን

ከአውደ ጥናት