Tuesday, December 23, 2014

Wishes

Merry Christmas And Happy Gregorian New Year
መልካም የልደት በአል እና የግሪጎርያን አዲስ ዓመት



“ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን፤
ሰላምም በምድር፣ ለሰውም በጎ ፈቃድ አሉ”
“Glory to God in the highest,
And on earth peace, ...
መልካም የልደት በአልና ደስታን የተመላ
የጎርጎርዮሳውያን አዲስ ዓመት እንዲሆንላችሁ፤
ልኡል እግዚአብሔር የወገኖቻችንንና የሁላችንንም
ሕይወት እንዲባርክ የዘወትር ምኞቴ ነው።
I wish you a Merry Christmas
And Happiest Gregorian New Year
May ALMIGHTY God Bless your life
And the life of your loved one!
See More

Sunday, December 21, 2014

Information about Awde Tinat

Good News!


Awde Tinat is now on Appstore please download and learn everything in on app
go to the following link to download
http://apps.appmakr.com/awdetinat

Friday, December 19, 2014

ግእዝ ክፍል 19

Learn Geez Language Part 19/የግእዝ ትምህርት ክፍል 19

ባለፈው ትምህርታችን በክፍል 18 ማለት ነው የቅኔ ተማሪዎች በመምህራቸው የተዘረፈላቸውን ቅኔ እየመላለሱ ሲያጠኑ አይታችሁ ወይም ተመልክታችሁ ነበር ። በዛሬው በክፍል 19 ደግሞ መምህሩ የተቀኙትን ቅኔ ለተማሪዎቻቸው ሲፈቱላቸው ወይም ሲተረጉሙላቸው እንደምታዩና እኔም በትርጉሙ ላይ ባብራርያ እንደ ምሰጣችሁ ቃል ገብቼላችሁ ነበር ። ስለዚህ በገባሁት ቃል መሠረት ይዠላችሁ ቀርቤያለሁ ማለት ነው።
ዛሬ የምታዩት ቅኔ ጉባዔ ቃና ይባላል። የመጀመሪያው የቅኔ ክፍል ነው። ይህ የመጀመሪያ የሆነው የቅኔ ክፍል ሁለት ቤቶች አሉት ። ማለትም ቅኔ እንደሚታወቀው  የሚቀርበው በግጥም መልክ ሲሆን በሰምና  በወርቅ ወይም በሁለት ወይም ከሁለት በላይ በሆኑ ምሥጢራዊ ትርጉሞች የተቀነባበረ ነው። ይህ ማለት ተደራራቢ አባባል አለው ማለት ነው። ዛሬ የምናየው ሁለት ስንኝ ያለውን ቅኔ ወይም ግጥም ነው።ለዚህም ነው ሁለት ቤት ያለው ማለት ሁለት ስንኝ ያለው ማለት ነው።
 በአሁኑ ደረጃችን የምናተኩረው በቅኔው ሕግና በሰምና ወርቁ ላይ ሳይሆን የግእዝን ቋንቋ በማጥናቱ ላይ ነው ።
አንድ ተማሪ እያነበበ መምህሩ ደግሞ ትርጉሙንና ሰምና ወርቁን ሲያብራሩ፤ ጥያቄም እየጠየቁ ተማሪዎቹ ማለት ነው ሲከራከሩ ታያላችሁ እኔ የማነብላችሁም ያንኑ ቅኔ ነው ነገር ግን በደንብ ላይሰማችሁና ግልጽ ላይሆንላችሁ ስለሚችል የበለጠ ላስረዳችሁ ስለፈለግሁ ብቻ ነው። መልካም ትምህርት!


ጉባዔ  ቃና
1.    ኃያል ስምኦን ዘጽጌ ድንግል ጸገየ
2.     70 (ሰብአ) እደወ አምጣነ ገንጰለ ማየ። ይኸ ነው ቅኔው፤፡
በድንግል አበባ ያበበ የሆነ ስምኦን ኃይለኛ ነው
(ምክንያቱም) ሰባ ሰዎችን ወደውኃ ገልብጦ ጥሏልና (ገልብጧልና)
የእያንዳንዱ ቃል ትርጉምና የሥራ ድርሻ
ኃያል = ኃይለኛ ማለት ነው
 የስምኦን ቅጽል (ገላጭ) አድጀክቲብ ሆኖ 
ግን ውእቱ የቢባለውን አንቀጽ በውስጡ በማስገኘት
 የዐረፍተ ነገሩ ማሠሪያ አንቀጽ ሆኗል።
በዚህ ሙያው ( ኃያል ውእቱን መርምሮ ማሠሪያ ተብሎ ይጠራል)
ስምኦን = ስም ሲሆን ሙያው የዐረፍተ ነገሩ ወይም የቅኔው ባለቤት
= “የ” ማለት ሲሆን አገባብ  ሆኖ ጸገየ የሚለውን ግሥ እንዳያስር ይጠብቃል
ጸጌ = አበባ ማለት ነውስም ሲሆን “በ”  የሚል አገባብ የወጣበት ነው
ወይም “በ” ን ያስገኘ ነው ( አገባብ የወጣበት ይባላ)
ድንግል = የተፈጥሮ ለውጥ ያልታየባት ወይም ያልታየበት፤ ጥብቅ፤ እንደ ተፈተረ ያለ፤
 (በክብረ ንጽሕያ ያለ) ወዘተ ማለት ሲሆን የሥራ ድርሻው ወይም
 በዚህ አረፍተ ነገር ላይ ያለው ሙያ የጽጌ ዘርፍ ይባላል
 (ሁለት ቃላት ሲናበቡ መጨረሻ ላይ የሚገኘው ቃል ከኋላው ላለው ቃል ዘርፍ ይባላል።
ለምሳሌ ቤተ ክርስቲያን ስንል ክርስቲያን የሚለው ቃል የቤት ዘርፍ ይባላል።
ጸገየ  ግሥ ነው ነገር ግን በአንድ ቅኔ ላይ ሁለት ግሥ ማሰር ስለማይችል በ “ዘ”
 ተጠብቋል ወይ  አበበ አበባ አወጣ በማለት እንዳያሥር ተከልክሏል



70 = በቁሙ ቁጥር ነው ሙያው የእደው ቅጽል ነው
እደወ (እደው) = ወንዶች ማለት ሲሆን
ሙያው የገንጰለ ተሳቢ ነው ዳይሬክት ኦብጀክት ይባላል
አምጣነ = እና ወይን “ና” ማለት ሲሆን አብይ አበባብ ነው
ገንጰለ = ገለበጠ ማለት ሲሆን በሙያው እንዳያሥር አምጣነ ከልክሎታል።
 አምጣነ የውደቀበት ተብሎም ይጠራል (በዚህ ዐረፍተ ነገር ላይ)
ማየ (ማይ) = ውሀ ማለት ሲሆን “ወደ” የሚል አገባብን ያስገኘ ነው።
ስለዚህ አገባብ የወጣበት ይባላል።

Tuesday, December 9, 2014

ግእዝ ክፍል18

በዚህ ቪዲዮ የምትሰሟቸውና የምታዩዋቸው ተማሪዎች በዳግማዊ ምኒልክ መታሰቢያ የመምህራንና ቀሳውስት ማሰልጠኛ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ውስጥ የሚገኙ የቅኔ ተማሪዎች ሲሆኑ የቅኔው መምህር የዘረፉትን ቅኔ በቃላቸው ለመያዝ እየቀጸሉ ወይም እያጠኑ ነው የምታዩዋቸው።
ይህ የአጠናን ዘዴ በቅኔ ቤት ወይም በመንፈሳዊ ትምህርት ቤት አነጋገር ወይም ቋንቋ ቅጸላ ይባላል። ስለዚህ እየቀጸሉ ነው ሲባል እያጠኑ ነው ማለት ነው።
እያጠኑ ወይም እየቀጸሉ ያሉት መምህሩ የዘረፉላቸውን ቅኔ ነው። መዝረፍ ወይም ዘረፋ ማለት ደግሞ በቅኔ ቤት ቋንቋ ያለ ምንም ዝግጅት ወይም በቂ የዝግጅት ጊዜ በድንገት ሐሳብን አመንጭቶ ድርሰትን መድረስ ወይም በግጥም መልክ የተቀነባበረ  ተደራራቢ ትርጉምን የሚሰጥ ሥነጽሁፍን መፍጠር ማለት ነው።
ከዚህ ቅጸላ ወይም ጥናት በኋላ መምህሩ የዘረፈውን ቅኔ ወይም የደረሰውን ድርሰት በቃላቸው ሸምድደው ይይዛሉ ለዚህም ነው እየመላለሱ የሚያጠኑት።
ትርጉሙንም እርስ በርሳቸው እየተረዳዱ ለመተርጎም ይሞክራሉ፤ አገባቦችንና የቃላቱን አቀማመጥ በቅኔ ትምህርት ሕግ መሠረት የተቀመጡ መሆናቸውን ይመረምራሉ፤ ያልገባቸውንና ስህተት ነው ብለው የሚገምቱት ቃል ወይም አገባብ ካለም ለመጠየቅ ይዘጋጃሉ።
እናንተም ይህንን ቅኔ በቃላችሁ በመያዝ ወደ አማርኛ ለመተርጎም ሞክሩ ። በእያንዳንዱ ቃልና አገባብም ምርምር አድርጉ።
በሚቀጥለው ትምህርት ደግሞ መምህሩ የዘረፉትን ቅኔ አንድ ተማሪ በቃሉ እያነበበ መምህሩ ሲተረጉሙ እንሰማለን።

Wednesday, December 3, 2014

ግእዝ ክፍል 18 የክ. 17 ማብራርያ

የግእዝ ቋንቋ ትምህርት ክፍል 18



ይህ ትምህርት  የክፍል 18 ትርጎምና ማብራርያ ነው።
በዚህ ዝግጅቴ
ሁለት የተለያዩ ትርጉሞችን በመጠቀም ክፍል 18ን ለማብራራት እሞክራለሁ ። በንቃትና በትጋት እንድንከታተል እግዚአብሔር ማስተዋሉን ያድለን። አሜን!
1ኛው የትርጉም ዓይነት “የቃል በቃል ወይም የቃላትና የአገባብ ትርጉም” በቅደም ተከተላቸው የሚለው ሲሆን ይህ ትርጉም በቀላሉ “የቃላት ትርጉም” ሊባል ይችላል።
2ኛው የትርጉም ዓይነት “የዐረፍተ ነገር እና የይዘት ትርጉም” የሚለው የአተረጓጎም ዓይነት ደግሞ “የይዘት ትርጉም” ልንለው እንችላለን።
ይህ አተረጓጎም የቃላቱን መሠረታዊ ትርጉም ሳይለቅ አቀማመጣቸውን ሊቀይር ይችላል፤ ለአማርኛ አነጋገር ተስማሚ የሆነ የቋንቋ ውበትን በመጨመር አስተካክሎ የመፍታት ወይም የመተርጎም መንገድ ነው።
ይህ አተረጓጎም የትርጉም ባለሙያዎች የሚጠቀሙበት ትክክለኛ የአተረጓጎም መንገድ ነው። ይህ ማለት የቋንቋ ችሎታችን እያደገ በሄደ ቁጥር አንድን ቋንቋ ስንተረጉም ማለትም ለምሳሌ ከግሪክኛ ወደ አማርኛ መተርጎም ብንፈልግ የግሪከኛውን ትክክለኛ ትርጉም ሳንለቅ ለአማርኛ ተናጋሪዎች የሚገባና የአማርኛን ቋንቋ ስልት የተከተለ አድርገን ካልተረጎምነው ለሚያነቡት ሰዎች ግልጽ አይሆንም። ማለት ነው።
ከዚህ ቀጥለን በእግዚአብሔርበአዳም እና በሔዋን መካከል የተደረገውን ውይይት እና በእባብም ላይ ጭምር የተነገሩትን ርግማኖች እንሰማለን። በዚህ ጽሁፍ ላይ የገለጽኳቸው በዘፍጥረት መጽሐፍ በምዕራፍ 3 ከቁጥር 9 ጀምሮ እስከ 17 የተገለጹትን ቢሆንም ሙሉ በሙሉ ሳይሆን አሳጥሬ ለመከታተል የሚያመች አድርጌ ነው ያቀረብኩት ሙሉውን ማየት ከፈለጋችሁ የግእዙን መጽሐፍ ቅዱስ መመልከት ትችላላችሁ።
አንድ ትኩረት ልታደርጉበት የሚገባችሁ ነገር ቢኖር “የቃል በቃል ወይም የቃላትና የአገባብ ትርጉም” በቅደም ተከተላቸው በሚለው ትርጉም ስር ትርጉማቸውን የምገልጸው ከመስማት አልፋችሁ ተጨማሪ ምርምርን ወይም ፍለጋን በሚጠይቅ መልኩ ነው ።
ለምሳሌ፦ “አይቴ ሀሎከ አዳም?” የሚለውን ዐረፍተ ነገር ወይም ጥያቄ የምተረጉመው
·       አይቴ=የት
·       ሀሎከ= አለህ(ነህ)
·       አዳም=ሰም ወይም በቁሙ አዳም ማለት ነው እያልኩ ሳይሆን
·       የት
·       አለህ(ነህ)
·       በቁሙ(አዳም)
በማለት በዚህ መልኩ ነው።
 ስለዚህ “አለህ ወይም ነህ” የሚለው የአማርኛ ትርጉም የሚናገረው ስለየትኛው የግእዝ ቃል ነው? የሚለውን ለማወቅ የምትጠቀሙት መንገድ በቅደም ተከተሉ ብቻ ነው። ለምሳሌ ነህ የሚለው በ2ኛ ተራቁጥር(ቁጥርም ባይኖር ቅደም ተከተሉን ስናይ ማለት ነው) ስለሆነ  ከግእዙ ዐ/ነገር በ2ኛ ተራቁጥር ላይ የሚገኘው “ሀሎከ” የሚለው ቃል ስለሆነ ነህ የሚለው ትርጉም የ”ሀሎከ” ነው ማለት ነው።
ለጊዜው ትርጉም የማይሰጥና ግራ የሚያጋባ መስሎ ሊታያችሁ ይችላል የተወሰነ ጥረት ካደረጋችሁ በኋላ ግን ይገባችኋል እውቀትም የበለጠ ትጨምራላችሁ። ስለዚህ አሁን ቀጥታ ወደ ዋናው ክፍል በመግባት መተርጎም እንጀምራለን።

እግዚአብሔር፣ አዳም፤ ሔዋን፤ እና እባብ እግዚአብሔር ይቤሎ ለአዳም፡= እግዚአብሔር አዳምን አለው
“.. አይቴ ሀሎከ አዳም.. ?
የቃል በቃል ወይም የቃላትና የአገባብ ትርጉም በቅደም ተከተላቸው፦
የት፤ አለህ (ነህ) ፤ አዳም (በቁሙ ስም)
 የዐረፍተ ነገር እና የይዘት ትርጉም፦
 “አዳም ሆይ የትነህ”? “ሆይ” የሚለው ቃል በዐረፍተነገሩ ላይ ባይኖርም ለቅርብ ወይም ለሁለተኛ መደብ የምንጠቀመው ተጨማሪ የቋንቋ ውበት ነው።
አዳም ይቤሎ ለእግዚአብሔር፡=አዳም እግዚአብሔርን አለው
“.. ሰማዕኩ ቃለከ እንዘ ታንሶሱ ውስተ ገነት ወፈራህኩ እስመ ዕራቅየ አነ ወተኀባእኩ.. ”
የቃል በቃል ወይም የቃላትና የአገባብ ትርጉም በቅደም ተከተላቸው፦
ሰማሁ፤ ቃልህን፤ ስ፤ስትመላለስ፤ ውስጥ፤ ገነት፤ ፈራሁም፤ ሰለ፤(እና) እራቁቴን፤ እኔ፤ ተሸሸግሁ፤
የዐረፍተ ነገር እና የይዘት ትርጉም፦
 “በገነት ውስጥ ስትመላለስ ሰማሁ፤ እራቁቴን ስለሆንኩም ፍራሁና ተደበቅሁ ወይም (ተሸሸግሁ)
እግዚአብሔር ይቤሎ ለአዳም፡=እግዚአብሔር አዳምን አለው
“.. መኑ አይድዐከ ከመ ዕራቅከ አንተ እም ዕፅኑ ዘአዘዝኩከ ከመ ኢትብላዕ እምኔሁ በላእከ?.. ”
የቃል በቃል ወይም የቃላትና የአገባብ ትርጉም በቅደም ተከተላቸው፦
ማን፤ ነገረህ፤ እንደ፤ እራቁትህን፤ አንተ (በቁሙ)፤ተክል፤(እንጨት፤ዛፍ፤) የ፤ ያዘዝኩህን፤ እንደ እንዳትበላ፤ ከሱ፤ በላህን?
የዐረፍተ ነገር እና የይዘት ትርጉም፦
እራቁትህን መሆንህን ማን ነገረህ? እንዳትበላ ካዘዝኩህ ከዚያ ፍሬ በላህን?
አዳም ይቤሎ ለእግዚአብሔር፡= አዳም እግዚአብሔርን አለው
“.. ብዕሲት እንተ ወሀብከኒ ምስሌየ ትንበር ይእቲ ወሀበተኒ ወበላእኩ-” *”ዘ” ስለሚለው አገባብ በሌላ ክፍል እንማረዋለን።

የቃል በቃል ወይም የቃላትና የአገባብ ትርጉም በቅደም ተከተላቸው፦
ሴት፤ አንተ(በቁሙ) የሰጠኸኝ፤ ከእኔጋር፤ ትኖርዘንድ፤ እሷ፤ ሰጠቺኝ፤ ም፤ በላሁ(በላሁም)
የዐረፍተ ነገር እና የይዘት ትርጉም፦
ከእኔ ጋር ትኖር ዘንድ የሰጠኸኝ ሴት እሷ ሰጠቺኝና በላሁ(ሰጠቺኝ በላሁም)
እግዚአብሔር ይቤላ ለሔዋን፡=እግዚአብሔር ሔዋንን አላት
“.. ለምንት ገበርኪ ዘንተ?.. ”
የቃል በቃል ወይም የቃላትና የአገባብ ትርጉም በቅደም ተከተላቸው፦
ለምን፤ አደረግሽ ፤ ይህንን
የዐረፍተ ነገር እና የይዘት ትርጉም፦
ለምን ይህንን አደረግሽ?
ብእሲት (ሔዋን) ትቤሎ ለእግዚአብሔር፡=ሔዋን (ሴትዮዋ) እግዚአብሔርን አለችው
“.. አርዌ ምድር አስፈጠተኒ ወበላእኩ.. ”
የቃል በቃል ወይም የቃላትና የአገባብ ትርጉም በቅደም ተከተላቸው፦
አውሬ(እባብ) ምድር(መሬት) አሳሳተቺኝ፤ ም፤ በላሁ(በላሁም)
የዐረፍተ ነገር እና የይዘት ትርጉም፦
የምድር አውሬ(እባብ) አሳሳተቺኝ በላሁም፡
እግዚአብሔር ይቤሎ ለአርዌ ምድር፡=እግዚአብሔር እባብን(የምድር አውሬን) አለው
“.. እስመ ገበርኮ ለዝንቱ ግብር ርጉመ ኩን እምኵሉ እንስሳ ወእምኵሉ አራዊተ ምድር ወበ እንግድዓከ ሑር ወመሬተ ብላዕ..”
የቃል በቃል ወይም የቃላትና የአገባብ ትርጉም በቅደም ተከተላቸው፦
እና(ስለ)፤ አደረግኸው፤ ይህንን፤ ሥራ፤ የተረገምክ፤ ሁን፤ ከ፤ ሁሉ(ከሁሉ)፤ እንስሳ፤ ም፤ከ፤ሁሉ(ከሁሉም) አውሬዎች፤ የምድር፤ በ፤ በደረትህ(በሆድህ) ሂድ፤ ም፤ መሬትን፤ ብላ፤
የዐረፍተ ነገር እና የይዘት ትርጉም፦
ይህንን ሥራ ሠርተተኸዋልና ከእንስሳት ሁሉ፤ ከምድር አራዊት ሁሉ (ተለይተህ) የተረገምክ ሁን፤ በሆድህም(በደረትህም) ሂድ፤ አፈርንም ብላ..
እግዚአብሔር ይቤላ ለሔዋን(ለብእሲት)፡= እግዚአብሔር ሔዋንን(ሴትዮዋን) አላት
“.. አብዝኆ(ብዙኃ) አበዝኆ ለኀዘንኪ ወለሥቃይኪ ወበጻዕር ለዲ..”
የቃል በቃል ወይም የቃላትና የአገባብ ትርጉም በቅደም ተከተላቸው፦
ማብዛትን፤ አበዛዋለሁ፤ኃዘንሺን፤ ም፤ ሥቃይሺን፤ በጭንቅም፤ ውለጂ
የዐረፍተ ነገር እና የይዘት ትርጉም፦
ኃዘንሺንና ስቃይሺን አበዛዋለሁ በጭንቅም ትወልጃለሽ፤(ውለጂ)
እግዚአብሔር ይቤሎ ለአዳም፡=እግዚአብሔር አዳምን አለው
“.. እስመ ሰማዕከ ቃለ ብእሲትከ ወበላዕከ እም ውእቱ ዕፅ ባሕቲቱ ዘአዘዝኩከ ከመ ኢትብላዕ ርግምተ ትኩን ምድር…”
የቃል በቃል ወይም የቃላትና የአገባብ ትርጉም በቅደም ተከተላቸው፦
እና፤ ሰማህ፤ ቃልን፤ ሚስትህ፤ በላህም፤ ከ፤ እሱ፤ ተክል(ፍሬ) ብቻውን፤ የ፤አዘዝኩህን፤ እንደ፤ አትብላ፤ የተረገመች፤ ትሁን፤ ምድር(መሬት)
የዐረፍተ ነገር እና የይዘት ትርጉም፦
የሚስትህን ቃል ሰምተህ እንዳትበላ ካዘዝኩህ ከዚያ ተክል(ፍሬ) በልተሃልና መሬት በአንተ ምክንያት የተረገመች ትሁን(ከአንተ የተነሣ)


Saturday, November 1, 2014

ግእዝ ክፍል 16 የ15 ማብራርያ

Part 16 Details for part 15 /ክፍል 16 ማብራርያ ለክፍል 15


የግእዝ ቋንቋ ትምህርት ክፍል 16 ትርጉምና ማብራርያ ለግእዝ ቋንቋ ትምህርት ክፍል 15 ውይይት ወይም ጥያቄና መልስ በወይዘሮ ሶፍያና በአንድ ካህን መካከል።  ማስተዋሉን ያድለን።

ተስእሎት ወአውሥዖት/ጥያቀና መልስ /ውይይት

ለግእዝ ትምህርት ክፍል 15 ውይይት

ወ/ሮ ሶፍያ፡
እፎ ሐደርከ አቡየ?
አማርኛ፡
እንደ ምን አደርክ/አደሩ/አባቴ?
(እፎ የመጠየቂያ ቃል ነው “እንዴት እንደ ምን? ማለት ነው።) ሐደርከ፡ የሁለተኛ መደብ ተባ እታይ አንድ ወይም ነጠላ ግሥ ነው “አደርክ” ማለት ነው። “አቡየ” አባቴ ማለት ነው። “አብ” አባት ሲሆነ “የ” የእኔ ማለት ነው።
       

ካህን፡
እግዚአብሔር ይሰባህ እፎ ሐደርኪ ሶፍያ?
አማርኛ፡
እግዚአብሔር ይመስገን እንደ ምን አደርሽ ሶፍያ?
እግዚእ
አብ
ሔር
ይሰባህ ለሦስተኛ መደብ ተባእታይ ፆታ ነጠላ ግስ ነው።
ሐደርኪ፡ ለሁለተኛ መደብ አንስታይ ፆታ ነጠላ ግሥ ነው፡

ወ/ሮ ሶፍያ፡
እግዚአብሔር ይሰባህ። ባርከኒ አቡየ!

አማርኛ፡
እግዚአብሔር ይመስገን ባርከኝ አባቴ/ባርኩኝ አባቴ(በግእዝ ቋንቋ አንቱታ የለም)
ባርከኒ፡ የሁለተኛ መደብ ነጠላ ግሥ ለተባእታይ ፆታ ሲሆን ትእዛዝ አንቀጽ ይባላል።

ካህን፡
እግዚአብሔር ይባርኪ ወያብርህ ገጾ ላእሌኪ፡

አማርኛ፡
እግዚአብሔር ይባርክሽ ፊቱንም ያብራልሽ/ፊቱንም ወደአንቺ ይመልስ

ይባርኪ፡ ለሁለተኛ መደብ ለአንስታይ ፆታ ሲሆን ምርቃት ነው
ወ/ሮ ሶፍያ፡
ፍትሐኒ አቡየ! አስተስሪ ኃጢአትየ

አማርኛ፡
ይፍቱኝ አባቴ ኃጢአቴን አስተስርይልን/ይቅር በል

ካህን
እግዚአብሔር ይፍታህ/ ይፍታህኪ/እግዚአብሔር ያስተስሪ ለኪ ኃጢአተኪ

አማርኛ፡
እግዚአብሔር ይፍታሽ/ኃጢአትሽን ይቅር ይበል

ወ/ሮ ሶፍያ፡

አሜን፡ /ይኩነኒ በከመ ትቤለኒ

አማርኛ፡
ይሁን ይደረግ/እንዳልከው ይህንልኝ

ካህን፡
እፎ ውእቶሙ(ሀለዉ) ደቂቅኪ ሶፍያ?

አማርኛ፡
ልጆችሽ እንዴት ናቸው ሶፍያ?

ወ/ሮ ሶፍያ፡
እግዚአብሔር ይሰባህ (ወውእቶሙ) ሰላመ ሐለዉ

አማርኛ፡
እግዚአብሔር ይመስገን ደህና ናቸው/ደህና አሉ

ካህን፡
ሶፍያ, ለምንት ኢመጽኡ  (ደቂቅኪ) ኅበ ቤተ ክርስቲያን ምስሌኪ?

አማርኛ፡
ሶፍያ፣ ልጆችሽ ለምን ወደ ቤተ ክርስቲያን ካንቺ ጋር አልመጡም?

ወ/ሮ ሶፍያ፡
አቡየ, አነ ፈተውኩ ከመ አምጽኦሙ ምስሌየ አላ ኢክህሉ ከመ ይትነሥኡ እምነ ንዋሞሙ፡

አማርኛ፡
አባቴ፣ ልጆቼን ከእኔ ጋር ወደ ቤተክርስቲያን እንዲመጡ /አመጣቸው ዘንድ ወድጀ ነበር፤ ነገር ግን ከእንቅልፋቸው ሊነሱ አልቻሉም።

ካህን:
ሶፍያ, ኢይደልወኪኑ ትንሥእዮሙ ለደቂቅኪ ኅበ ቤተ እግዚአብሔር?

አማርኛ፡
ሶፍያ፤ ወደ እግዚአብሔር ቤት ይዘሻቸው ትመጪ ዘንድ ይገባሽ አልነበረምን?

ወ/ሮ ሶፍያ፡
 አአምር አቡየ; አላ ውእቶሙ ኢፈቀዱ ከመ ይምፅኡ (ኢፈቀዱ ይምፅኡ) ኅበ ቤተ ክርስቲያን ምስሌየ

አማርኛ፡
አውቃለሁ አባቴ፤ ነገር ግን እነሱ ከእኔ ጋር ወደ ቤተ ክርስቲያን ይመጡ ዘንድ አልወደዱም።
ካህን፡
ወአነ አአምር!
ሰላመ እግዚአብሔር የሀሉ ምስሌኪ ወሑሪ በሰላም
አማርኛ፡
እኔም አውቃለሁ! የእግዚአብሔር ሰላም ከአንቺ ጋር ይሁን በሰላም ሂጂ/በሰላም ግቢ።
ወ/ሮ ሶፍያ:
አሜን አቡየ!
ወአንተሰ እቱ ኀበ ቤትከ በሰላም
አማርኛ፡
አሜን/ይሁን ይደረግ አባቴ፤ አንተም በሰላም ወደ ቤትህ ግባ።

Friday, October 3, 2014

ግእዝ ክፍል 15

"Learn Geez Language/የግእዝ ቋንቋ ትምህርት Part 15 


የግእዝ ቋንቋ ትምህርት ክፍል 15 ውይይት ወይም ጥያቄና መልስ በወይዘሮ ሶፍያና በአንድ ካህን መካከል። እንግሊዘኛ ለሚፈልግ በእንግሊዘኛም አዘጋጅቸላችኋለሁ ጽሁፍን መመልከት ትችላላችሁ ማለት ነው። ማስተዋሉን ያድለን።

ተስእሎት ወአውሥዖት/ጥያቀና መልስ /ውይይት
Questions and Answers or Dialogues

የግእዝ ትምህርት ክፍል 15 ውይይት
Geez: lessons part 15 Dialogues (በግእዝ፤ በእንግሊዘኛ እና በአማርኛ)

Sofia፡/ሶፍ
እፎ ሐደርከ አቡየ?

Good Morning Father?

አማርኛ፡
እንደ ምን አደርክ/አደሩ/አባቴ?

ካህን፡Clergy/Pries:
እግዚአብሔር ይሰባህ እፎ ሐደርኪ ሶፍያ?

Thanks to God! Good Morning Sofia!

አማርኛ፡
እግዚአብሔር ይመስገን እንደ ምን አደርሽ ሶፍያ?

ሶፍያ/Sofia፡
እግዚአብሔር ይሰባህ። ባርከኒ አቡየ!

 Thanks to God bless me my Father

አማርኛ፡
እግዚአብሔር ይመስገን ባርከኝ አባቴ/ባርኩኝ አባቴ(በግእዝ ቋንቋ አንቱታ የለም)

ካህን/ Clergy/Pries፡
እግዚአብሔር ይባርኪ ወያብርህ ገጾ ላእሌኪ፡

 God (The Lord) bless you and make his face shine on you

አማርኛ፡
እግዚአብሔር ይባርክሽ ፊቱንም ያብራልሽ/ፊቱንም ወደአንቺ ይመልስ

ሶፍያ/Sofia፡
ፍትሐኒ አቡየ! አስተስሪ ኃጢአትየ
My Father, Please forgive my sin

አማርኛ፡
ይፍቱኝ አባቴ ኃጢአቴን አስተስርይልን/ይቅር በል

ካህን/Clergy/Pries
እግዚአብሔር ይፍታህ/ ይፍታህኪ/እግዚአብሔር ያስተስሪ ለኪ ኃጢአተኪ

 God (the Lord God) forgive your sin

አማርኛ፡
እግዚአብሔር ይፍታሽ/ኃጢአትሽን ይቅር ይበል

Sofia፡/ሶፍያ

አሜን፡ /ይኩነኒ በከመ ትቤለኒ

Amen

አማርኛ፡
ይሁን ይደረግ/እንዳልከው ይህንልኝ

ካህን/ Clergy/Pries፡
እፎ ውእቶሙ(ሀለዉ) ደቂቅኪ ሶፍያ?

How are your children Sofia?

አማርኛ፡
ልጆችሽ እንዴት ናቸው ሶፍያ?


Sofia፡/ሶፍያ
እግዚአብሔር ይሰባህ (ወውእቶሙ) ሰላመ ሐለዉ

 Thanks to God they are fine

አማርኛ፡
እግዚአብሔር ይመስገን ደህና ናቸው/ደህና አሉ

ካህን/Clergy/ Priest;

ሶፍያ, ለምንት ኢመጽኡ  (ደቂቅኪ) ኅበ ቤተ ክርስቲያን ምስሌኪ?

Sofia; Why they did not come with you to the church?

አማርኛ፡
ሶፍያ፣ ልጆችሽ ለምን ወደ ቤተ ክርስቲያን ካንቺ ጋር አልመጡም?

Sofia/ሶፍያ፡
አቡየ, አነ ፈተውኩ ከመ አምጽኦሙ ምስሌየ አላ ኢክህሉ ከመ ይትነሥኡ እምነ ንዋሞሙ፡

My Father, I would like them to come with me, but, they could not walkup!

አማርኛ፡
አባቴ፣ ልጆቼን ከእኔ ጋር ወደ ቤተክርስቲይና እንዲመጡ /አመጣቸው ዘንድ ወድጀ ነበር፤ ነገር ግን ከእንቅልፋቸው ሊነሱ አልቻሉም።

ካህን/Priest:
ሶፍያ, ኢይደልወኪኑ ትንሥእዮሙ ለደቂቅኪ ኅበ ቤተ እግዚአብሔር?

 Sofia, shouldn’t bring your kids to the temple of God?

አማርኛ፡
ሶፍያ፤ ወደ እግዚአብሔር ቤት ይዘሻቸው ትመጪ ዘንድ ይገባሽ አልነበረም?

ሶፍያ/Sofia፡
 አአምር አቡየ; አላ ውእቶሙ ኢፈቀዱ ከመ ይምፅኡ (ኢፈቀዱ ይምፅኡ) ኅበ ቤተ ክርስቲያን ምስሌየ

 I know my father but they did not want to come with me to the church.

አማርኛ፡
አውቃለሁ አባቴ፤ ነገር ግን እነሱ ከእኔ ጋር ወደ ቤተ ክርስቲያን ይመጡ ዘንድ አልወደዱም።

ካህን፡/Priest
ወአነ አአምር!
ሰላመ እግዚአብሔር የሀሉ ምስሌኪ ወሑሪ በሰላም
I know too! The Peace of God May Be with You ! Go(walk)  in Peace!

አማርኛ፡
እኔም አውቃለሁ! የ እግዚአብሔር ሰላም ከአንቺ ጋር ይሁን በሰላም ሂጂ/በሰላም ግቢ።

ሶፍያ/Sofia:
አሜን አቡየ!
ወአንተሰ እቱ ኀበ ቤትከ በሰላም
Amen my father, to you too!
አማርኛ፡
አሜን/ይሁን ይደረግ አባቴ፤ አንተም በሰላም ወደ ቤትህ ግባ።




Sunday, September 21, 2014

"More Blessed"

"More Blessed"

“ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብፁዕ ነው” የሐዋርያት ሥራ 20፡35
"It is more blessed to give
than to receive". Acts 20:35


Wednesday, September 10, 2014

Happy Ethiopian New Year of 2007


Happy Ethiopian New 



Year of 2007! የዘመናት ባለቤት ል ዑል እግዚአብሔር እንኳን እንኳን ከዘመነ ማርቆስ ወደ ዘመነ ሉቃስ በሰላም አሸጋገራችሁ

በዚህ ምድር ላይ ጊዜን ማግኘት ማለት የጀመሩትን ሥራ ለመጨረስና ያቀዱትን ጀምሮ በስኬት ለመጨረስ የበለጠ ጠንክሮ ለመሥራት ነው። እግዚአብሔር ቸር በመሆኑ ጊዜውን ለሁላችንም በነጻ አድሎን ከዘመን ወደ ዘመን አሽጋግሮናል። ማለትም ተጨማሪ ጊዜን አግኝተናል። የተሰጠንን ጊዜ እንዴት መጠቀመ እንዳለብና ማወቅና በጥቅም ላይ ማዋልም የያንዳንዳችን ድርሻ ብቻ ነው። “ጊዜ ጥሬ ገንዘብ ነው” ይባላል! ነገር ግን ወደ ጥሬ ገንዘብ ሊለውጠው የሚችል ጠንካራና ታማኝ ሠራተኛ ሲያገኝ ብቻ ነው። በመሆኑም ጊዜን ካገኘን ዘንድ እንወቅበት!! የዘመናት ባለቤት እግዚአብሔር የሰጠንን ጊዜ እንድናፈራበት ይርዳን።

To have an extra time on earth means, getting more chance to complete the work We already started or to start working harder to achieve our goal: so now we have gotten that extra time to use it. Knowing what to do with it is our job, your job, my job, and everyone’s job. “time is money” only if we make it money. Let make it happen!

May God bless you and your entire family!
watch video


Monday, September 8, 2014

Female and Traditional Poetry/Geez

ሴቷ ባለቅኔ

የግእዝ ቋንቋ ትምህርታችን በወቅቱ እንደ ተለመደው ባለመተላለፉ በጣም ይቅርታ እላለሁ ። ያልተላለፈበት ምክንያት ማኅበረ አጋፒ ወይም የፍቅር ኅብረት የሚባል ወላጅ አልባ ሕጻናትን የምናሳድግበት ማኅበር ወይም ድርጅት አለ እና 6ኛ ዓመቱን የሚያከብርበት ጊዜ ስለነበረ ዓመታዊ ሪፖርትን ለማዘጋጀት ባጠቃላይ በአሉን ለማዘጋጀት ጊዜ መውሰድ ስለነበረብኝ ነው እና ለበጎ ነው ማለቴ ነው። በዚህ አጋጣሚ ወደዚሁ ሕይወትን የማዳን ወላጅ ከማጣታቸውም ሌላ በርኃብ የሚሰቃዩ ሕጻናትን የመርዳት ሥራ መሣተፍ የምትፈልጉ ካላችሁ በኢሜይል ልታነጋግሩኝ እንደምትችሉ ላሳስባችሁ እወዳለሁ።
ባለፈው ትምህርታችን በሁለት ክፍሎች ወይም ሰዎች መካከል የሚደረግ የግእዝ ውይይት እንደማቀርብላችሁ ቃል ገብቸ ነበረ ሆኖም ግን ሌላ አዲስና ማራኪ ዝግጅት ስላገኘሁ አሁኑኑ ቢቀርብ መልካም ነው ብየ በማሰብ ውይይቱን ለሚቀጥለው አስተላልፊዋለሁ

በመሆኑም ዛሬ በዚህ የግእዝ ቋንቋ ትምህርታችን እጅግ አስደናቂ እንግዳን ይዠላችሁ ቀርቤያለሁ በሐገራችን ተዘውትሮ የተለመደ ባይሆንም ከወይዘሮ ገላነሽ ጀምሮ እውቅ የቅኔ ባለሙያዎች የሆኑ ሴቶች እንደ ነገሩ ታሪካቸውን እናነባለን። አሁንም በዘመናቺን ቅኔ የተማሩ ሴቶችን ማየት እንደሰማይ የራቀ እንደ ትረት የሚወራ ቢሆንም መኖራቸው ግን እውን ነው።

ከሁሉም በላይ አሁን ያለንበት ዘመን ግን እንኳን ቅኔ የሚያውቁ ሴቶ ይቅርና ግእዝን የሚያውቁ ወይም የሚማሩ ወንዶች እንደ ልብ የማይገኙበት ጊዜ እየሆነ ነው። በዚህም ምክንያት ያውም በአሜሪካ ውስጥ የግእዝን ቋንቋ፤ ቅኔን ከነዜማልኩ እና ከነታሪካዊ አመጣጡ ተንትና የምታስረዳ ሴት ባለ ቅኔን ማየት እንደ ተአምር የሚቆጠር ነው።

የዛሬዋ እንግዳቺን ባለትዳርና የልጆች እናት ስትሆን የምትኖረውም በሰሜን አሜሪካ ውስጥ ነው።
ይህቺ እኅት የግእዝን ቋንቋ አጣርታ የምታውቅ ስትሆን ቋንቋውን ብቻ አይደለም የቅኔ ምሁር ናት፤ከዚያም አልፋ ቅኔውን እስከ ዜማው አሳምራ ተምራለቺ።

የዚች ባለቅኔ እኅታችን የግእዝን ቋንቋ በምናጠናበት በዚህ በአውደ ጥናት መድረክ መቅረብ ለብዙዎቻችሁ በተለይ ለሴቶች እኅቶቻችን እጅግ ታላቅ መልእክት ያለውና ለትምህርት የሚያነሣሳ  ማነኛውም ትምህርት የፆታ ልዩነት የማይገድበው መሆኑን የሚያሳይ መልካም አርአያ የሚሆን ነው ብየ አምናለሁ። መልካም ግንዛቤ ።ሌሎችም እንዲያዩት ማድረግን እና አስተያየታችሁን እና አድናቆታችሁን መጻፍን አትርሱ

Wednesday, August 27, 2014

Know the New Year/ አዲስ ዓመቱን ይወቁ

Know the New Year/አዲስ ዓመቱን ይወቁ

የአዲሱ ዓመት መጠሪያና ዕለት

የዘመኑን ወንጌላዊ ወይም ዓዲሱ ዓመት በየትኛው ወንጌላዊ ስም የሚሰየም መሆኑን ለማወቅ የሚፈለግበዎ ቀላል የመደመርና የማካፈል እውቀት ብቻ ነው።
ስለዚህ አዲስ ዓመት ከአራቱ ወንጌላውያን (ማቴዎስ፤ማርቆስ፤ሉቃስ፤ እና ዮሐንስ) ውስጥ በየትኛው እንደሚሰየም ወይም ዘመኑን የሚረከበው ወንጌላዊ ማን እንደ ሆነ ለማወቅ ሁለት ነገሮችን ደምረው ለ 4 (አራቱ ወንጌላውያን) ያካፍሉ።
ከሁሉም በፊት የሚከተሉትን ስሞች ያስታውሱ
ዓመተ ዓለም፡ ዓመተ ዓለም የሚባለው ከክርስቶስ በፊትና ከክርስቶስ በኋላ ያሉት ዘመናት ተደምረው የሚሰጡት ውጤት ወይም ዘመን ነው።
ከክርስቶስ በፊት የነበረው ዘመን በእምነቻችን መሠረት
5500 ዘመን (ዓመታት) ነው፡፡ ይህም ዓመተ ፍዳ፤ ዓመተኵነኔ ይባላል።
ከክርስቶስ በኋላ ያለው ዘመን (ዓመተ ምሕረት ወይም የድኅነት ዘመን) ሲባል በዚህ ዓመት እንደ አገራችን አቆጣጠር 2006 ፤ እንደ ፈረንጆቹ ደግሞ 2014 ዓመት ወይም ዓመታት መሆኑ ነው።
5500+2006=7506 ይሆናል። ይህ ዓመተ ዓለም ይባላል።
ዓመተ ዓለም ወይም 7506 ሲካፈል ለ 4(አራቱ ወንጌላውያን) ማለትም 7506 4 ለ4 (አራቱ ወንጌላውያን) ተካፍሎ የሚቀረው ትርፍ ቁጥር
1 ከሆነ አዲሱ ዘመን የማቴዎስ
2 ከሆነ የማርቆስ
3 ከሆነ የሉቃስ
0 ወይም ምንም ሳይተርፍ ከተካፈለ ዮሐንስ ነው ማለት ነው።
የወንጌላውያንን መጠሪያ ቁጥር ወይም ቅደም ተከተላቸውን ማወቅ ከፈለጉ መጽሐፍ ቅዱሰዎን ይግለጡ። መጀመሪያ የሚያገኙት ወንጌል(መጽሐፍ) ማን እንደሆነ ይመልከቱ ማለትም መጀመሪያ ለሚያገኙት ወንጌላዊ 1 ቁጥርን ይስጡ፤ ሁለተኛ ለሚያገኙት 2 ቁጥርን፤ ሦስተኛ ለሚያገኙት 3 ቁጥርን፤ አራተኛ ለሚያገኙት 4 ቍጥርን ይስጡ። ስለዚህ ቅደም ተከተላቸውን አወቁ ማለት ነው። ይህ ቅደም ተከተላቸው መጠሪያ ወይም መለያ ስማቸው ነው።
ዓመተ ዓለሙ ለ4 ስለሚካፈል 4 ቀሪ ሊሆን አይችልም በመሆኑም ያለምንም ቀሪ ከተካፈለ 4 እንደ ቀረዎ ወይም ያለምንም ቀሪ ተካፈለ ማለት 0 ቀሪ ማለት ነው። በዚህ ጊዜ ዘመኑ ዮሐንስ ነው ማለት ነው።
አዲስ ዓመት ወይም መስከረም አንድ ቀን ከሳሙንቱ ዕለታት በየትኛው ቀን ወይም ዕለት እንደሚውል ለማወቅ የሚከተሉትን ስሌቶች ይሥሩ።
ዓመተ ዓለም (ከክርስቶስ በፊትና ከክርስቶስ በኋላ ያለው ዘመን) ማለትም 5500+ዓመተ ምሕረት ማለት ነው ሲደመር ወንጌላዊውን ለማግኘት ለአራት አካፍለው ያገኙትን ውጤት ቀሪውን ሳይጨምር ማለት ነው ደምረው ለ7 ማለትም ለሰባቱ ዕለታት ያካፍሉ። ለሰባት ተካፍሎ የሚቀረውን ቀሪ ቁጥር እንደ ሚከተለው ይመድቡ ወይም ይስጡ ወይም ይሰይሙ። ቀሪው
1 ከሆነ ማክሰኞ ማለት ነው
2 ከሆነ ረቡዕ
3 ከሆነ ሐሙስ
4 ከሆነ ዓርብ
5 ከሆነ ቅዳሜ
6 ከሆነ እሁድ
ምንም ቀሪ ከሌለ ወይም ዜሮ (0) ከሆነ ሰኞ ማለት ነው ።
አንድ ቍጥር ለማክሰኞ የተሰጠበት ምክንያት ወይም ማክሰኞ በአንደኛ ተራ ቋጥር የተቀመጠበት ምክንያት ወይም የሳምንቱ መጀመሪያ ማክሰኞ የሆነበት ምክንያት በሥነ ስሌት ትምህርት ማክሰኞ “ጥንተ ቀመር” ይባላል። ጥንተ ቀመር ማለት ሥሌት ወይም ቆጠራ፤ አቆጣጠር ወዘተ ማለት ነው። ስለዚህ ጥንተ ቀመር ሲባል የሥሌት መጀመሪያ ማለት ነው። ሥነ ሥሌት ወይም ቆጠራ የተጀመረው በዕለተ ማክሰኞ ነው ተብሎ ስለሚታመን ማክሰኖ በሥነ ሥሌት ትምህርት የቀኖች መጀመሪያ ነው።
ከዚህ ቀጥለን ቍጥሮችን ብቻ በምሳሌነት በቀላሉ እናያለን። ከዚህ በላይ የተዘረዘረውን ሁሉ ማወቅ አይጠበቅባችሁም ብቻ የሚከተሉትን ቁጥሮች በትክክል መደመርና ማካፈል ቀሪውን ለሚገባው ወንጌላዊና ዕለት መስጠት ብቻ ነው።
1፡ ዓመተ ዓለም፡ ማለት 5500+ ዓመተ ምሕረት ማለት ነው ለምሳሌ ዓሁን ያለንበት ዓመተ ምሕረት እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር 2006 ዓ/ም እንደ ፈረንጆቹ ደግሞ 2014 ዓ/ም ነው። ስለዚህ ዓመተ ዓለም ሲባል 5500+2006 =7506 ወይም 5500+2014 = 75014 ይሆናል።
የሚቀጥለውን ወይም የ2007ን ለማወቅ የራሱን ማለትም ማወቅ የምንፈልገውን ዘመን ማለትም የሁለትሺ ሰባትን(2007ን) ወንጌላዊ ወይም የሚውልበትን ዕለት ማወቅ ስለምንፈልግ የ2007ን ዘመን መጠቀም አለብን ። የ2006ን ማወቅ የምንፈልግ ከሆነም ራሱን 2006 መጠቀም አለብን።
አሁን ምሳሌውን በጥንቃቄ እንመልከት ምሳሌያችን የ2006ን ወንጌላዊና የዋለበትን ዕለት ለማወቅ ስለሆነ የምንጠቀመው ራሱን የ2006ን ዘመን ነው።
ምሳሌ 1፡ የ2006 ዓ/ም ወንጌላዊ ማነው?
5500+2006=7506 4=1876 ደርሶ 2(ሁለት) ይቀራል።
ሰለዚህ የ2006 ዓ/ም ወንጌላዊ ማርቆስ  ነበር ወይም ነው ማለት ነው።
ምሳሌ2፡ የ2006 ዓ/ም አዲስ ዓመት የዋለበት እለት ወይም ቀን ማን ነበር?
7506+1876=9381 7=1340 ደርሶ 2(ሁለት) ይቀራል። ስለዚህ የ2006 ዓ/ም አዲስ ዓመት የዋለበት እለት ወይም ቀን ረቡዕ ነበር ማለት ነው።
ዓመተ ፍዳ + ዓመተ ዓ/ም ወጤቱን ለ4 በማካፈል ወንጌላዊውን ያገኛሉ።
ዓመተ ዓለሙን እና ዓመተ ዓለሙ ለ4 ተካፍሎ የተገኘውን ውጤት ደምረው ለ7 በማካፈል የዓዲሱን ዓመት መጀመሪያ ቀን ያውቃሉ ። (ዓመተ ፍዳ+ ዓመተ ምሕረት ሲካፈል ለ4 = ወንጌላዊ። ዓመተ ዓለም + ለ4 ተካፍሎ የተገኘው ውጤት ሲካፈል ለ7 = የዓዲስ አመት መጀመሪያ ቀን) ይሆናል።
አሁን የ2007ን ወንጌላዊና የሚውልበትን ዕለት ማግኘት የ እናንተ ድርሻ ይሆናል።
5500+2006=7506÷4=1876 ደርሲ ቀሪ 2 = 2ኛው ወንጌላዊ
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ዓመተ ዓለም= 5500+ ዓመተ ምህረት (5500+2007=7507)
7507(ዓመተ ዓለም) ÷4 = 1876 ተካፍሎ ቀሪ 3 ይሆናል ስለዚህ ሦስተኛው ወንጌል
 የዘመኑ ወንጌላዊ ነው ማለት ነው።
ዓመተ ዓለም (7507)+1876 = 9383÷7=1340 ደርሶ 3 ይቀራል በሥነ ስሌት ትምህርት ከሳምንቱ 3ኛው ቀን ሐሙስ ስለሆነ የ2007 ዓ/ም አዲስ ዓመት ሐሙስ ይውላል፡
ዘመኑ ሉቃስ ዕለቱ ሐሙስ
ወስብሐት ለእግዚአብሔር