Tuesday, December 9, 2014

ግእዝ ክፍል18

በዚህ ቪዲዮ የምትሰሟቸውና የምታዩዋቸው ተማሪዎች በዳግማዊ ምኒልክ መታሰቢያ የመምህራንና ቀሳውስት ማሰልጠኛ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ውስጥ የሚገኙ የቅኔ ተማሪዎች ሲሆኑ የቅኔው መምህር የዘረፉትን ቅኔ በቃላቸው ለመያዝ እየቀጸሉ ወይም እያጠኑ ነው የምታዩዋቸው።
ይህ የአጠናን ዘዴ በቅኔ ቤት ወይም በመንፈሳዊ ትምህርት ቤት አነጋገር ወይም ቋንቋ ቅጸላ ይባላል። ስለዚህ እየቀጸሉ ነው ሲባል እያጠኑ ነው ማለት ነው።
እያጠኑ ወይም እየቀጸሉ ያሉት መምህሩ የዘረፉላቸውን ቅኔ ነው። መዝረፍ ወይም ዘረፋ ማለት ደግሞ በቅኔ ቤት ቋንቋ ያለ ምንም ዝግጅት ወይም በቂ የዝግጅት ጊዜ በድንገት ሐሳብን አመንጭቶ ድርሰትን መድረስ ወይም በግጥም መልክ የተቀነባበረ  ተደራራቢ ትርጉምን የሚሰጥ ሥነጽሁፍን መፍጠር ማለት ነው።
ከዚህ ቅጸላ ወይም ጥናት በኋላ መምህሩ የዘረፈውን ቅኔ ወይም የደረሰውን ድርሰት በቃላቸው ሸምድደው ይይዛሉ ለዚህም ነው እየመላለሱ የሚያጠኑት።
ትርጉሙንም እርስ በርሳቸው እየተረዳዱ ለመተርጎም ይሞክራሉ፤ አገባቦችንና የቃላቱን አቀማመጥ በቅኔ ትምህርት ሕግ መሠረት የተቀመጡ መሆናቸውን ይመረምራሉ፤ ያልገባቸውንና ስህተት ነው ብለው የሚገምቱት ቃል ወይም አገባብ ካለም ለመጠየቅ ይዘጋጃሉ።
እናንተም ይህንን ቅኔ በቃላችሁ በመያዝ ወደ አማርኛ ለመተርጎም ሞክሩ ። በእያንዳንዱ ቃልና አገባብም ምርምር አድርጉ።
በሚቀጥለው ትምህርት ደግሞ መምህሩ የዘረፉትን ቅኔ አንድ ተማሪ በቃሉ እያነበበ መምህሩ ሲተረጉሙ እንሰማለን።

No comments:

Post a Comment