Wednesday, August 27, 2014

Know the New Year/ አዲስ ዓመቱን ይወቁ

Know the New Year/አዲስ ዓመቱን ይወቁ

የአዲሱ ዓመት መጠሪያና ዕለት

የዘመኑን ወንጌላዊ ወይም ዓዲሱ ዓመት በየትኛው ወንጌላዊ ስም የሚሰየም መሆኑን ለማወቅ የሚፈለግበዎ ቀላል የመደመርና የማካፈል እውቀት ብቻ ነው።
ስለዚህ አዲስ ዓመት ከአራቱ ወንጌላውያን (ማቴዎስ፤ማርቆስ፤ሉቃስ፤ እና ዮሐንስ) ውስጥ በየትኛው እንደሚሰየም ወይም ዘመኑን የሚረከበው ወንጌላዊ ማን እንደ ሆነ ለማወቅ ሁለት ነገሮችን ደምረው ለ 4 (አራቱ ወንጌላውያን) ያካፍሉ።
ከሁሉም በፊት የሚከተሉትን ስሞች ያስታውሱ
ዓመተ ዓለም፡ ዓመተ ዓለም የሚባለው ከክርስቶስ በፊትና ከክርስቶስ በኋላ ያሉት ዘመናት ተደምረው የሚሰጡት ውጤት ወይም ዘመን ነው።
ከክርስቶስ በፊት የነበረው ዘመን በእምነቻችን መሠረት
5500 ዘመን (ዓመታት) ነው፡፡ ይህም ዓመተ ፍዳ፤ ዓመተኵነኔ ይባላል።
ከክርስቶስ በኋላ ያለው ዘመን (ዓመተ ምሕረት ወይም የድኅነት ዘመን) ሲባል በዚህ ዓመት እንደ አገራችን አቆጣጠር 2006 ፤ እንደ ፈረንጆቹ ደግሞ 2014 ዓመት ወይም ዓመታት መሆኑ ነው።
5500+2006=7506 ይሆናል። ይህ ዓመተ ዓለም ይባላል።
ዓመተ ዓለም ወይም 7506 ሲካፈል ለ 4(አራቱ ወንጌላውያን) ማለትም 7506 4 ለ4 (አራቱ ወንጌላውያን) ተካፍሎ የሚቀረው ትርፍ ቁጥር
1 ከሆነ አዲሱ ዘመን የማቴዎስ
2 ከሆነ የማርቆስ
3 ከሆነ የሉቃስ
0 ወይም ምንም ሳይተርፍ ከተካፈለ ዮሐንስ ነው ማለት ነው።
የወንጌላውያንን መጠሪያ ቁጥር ወይም ቅደም ተከተላቸውን ማወቅ ከፈለጉ መጽሐፍ ቅዱሰዎን ይግለጡ። መጀመሪያ የሚያገኙት ወንጌል(መጽሐፍ) ማን እንደሆነ ይመልከቱ ማለትም መጀመሪያ ለሚያገኙት ወንጌላዊ 1 ቁጥርን ይስጡ፤ ሁለተኛ ለሚያገኙት 2 ቁጥርን፤ ሦስተኛ ለሚያገኙት 3 ቁጥርን፤ አራተኛ ለሚያገኙት 4 ቍጥርን ይስጡ። ስለዚህ ቅደም ተከተላቸውን አወቁ ማለት ነው። ይህ ቅደም ተከተላቸው መጠሪያ ወይም መለያ ስማቸው ነው።
ዓመተ ዓለሙ ለ4 ስለሚካፈል 4 ቀሪ ሊሆን አይችልም በመሆኑም ያለምንም ቀሪ ከተካፈለ 4 እንደ ቀረዎ ወይም ያለምንም ቀሪ ተካፈለ ማለት 0 ቀሪ ማለት ነው። በዚህ ጊዜ ዘመኑ ዮሐንስ ነው ማለት ነው።
አዲስ ዓመት ወይም መስከረም አንድ ቀን ከሳሙንቱ ዕለታት በየትኛው ቀን ወይም ዕለት እንደሚውል ለማወቅ የሚከተሉትን ስሌቶች ይሥሩ።
ዓመተ ዓለም (ከክርስቶስ በፊትና ከክርስቶስ በኋላ ያለው ዘመን) ማለትም 5500+ዓመተ ምሕረት ማለት ነው ሲደመር ወንጌላዊውን ለማግኘት ለአራት አካፍለው ያገኙትን ውጤት ቀሪውን ሳይጨምር ማለት ነው ደምረው ለ7 ማለትም ለሰባቱ ዕለታት ያካፍሉ። ለሰባት ተካፍሎ የሚቀረውን ቀሪ ቁጥር እንደ ሚከተለው ይመድቡ ወይም ይስጡ ወይም ይሰይሙ። ቀሪው
1 ከሆነ ማክሰኞ ማለት ነው
2 ከሆነ ረቡዕ
3 ከሆነ ሐሙስ
4 ከሆነ ዓርብ
5 ከሆነ ቅዳሜ
6 ከሆነ እሁድ
ምንም ቀሪ ከሌለ ወይም ዜሮ (0) ከሆነ ሰኞ ማለት ነው ።
አንድ ቍጥር ለማክሰኞ የተሰጠበት ምክንያት ወይም ማክሰኞ በአንደኛ ተራ ቋጥር የተቀመጠበት ምክንያት ወይም የሳምንቱ መጀመሪያ ማክሰኞ የሆነበት ምክንያት በሥነ ስሌት ትምህርት ማክሰኞ “ጥንተ ቀመር” ይባላል። ጥንተ ቀመር ማለት ሥሌት ወይም ቆጠራ፤ አቆጣጠር ወዘተ ማለት ነው። ስለዚህ ጥንተ ቀመር ሲባል የሥሌት መጀመሪያ ማለት ነው። ሥነ ሥሌት ወይም ቆጠራ የተጀመረው በዕለተ ማክሰኞ ነው ተብሎ ስለሚታመን ማክሰኖ በሥነ ሥሌት ትምህርት የቀኖች መጀመሪያ ነው።
ከዚህ ቀጥለን ቍጥሮችን ብቻ በምሳሌነት በቀላሉ እናያለን። ከዚህ በላይ የተዘረዘረውን ሁሉ ማወቅ አይጠበቅባችሁም ብቻ የሚከተሉትን ቁጥሮች በትክክል መደመርና ማካፈል ቀሪውን ለሚገባው ወንጌላዊና ዕለት መስጠት ብቻ ነው።
1፡ ዓመተ ዓለም፡ ማለት 5500+ ዓመተ ምሕረት ማለት ነው ለምሳሌ ዓሁን ያለንበት ዓመተ ምሕረት እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር 2006 ዓ/ም እንደ ፈረንጆቹ ደግሞ 2014 ዓ/ም ነው። ስለዚህ ዓመተ ዓለም ሲባል 5500+2006 =7506 ወይም 5500+2014 = 75014 ይሆናል።
የሚቀጥለውን ወይም የ2007ን ለማወቅ የራሱን ማለትም ማወቅ የምንፈልገውን ዘመን ማለትም የሁለትሺ ሰባትን(2007ን) ወንጌላዊ ወይም የሚውልበትን ዕለት ማወቅ ስለምንፈልግ የ2007ን ዘመን መጠቀም አለብን ። የ2006ን ማወቅ የምንፈልግ ከሆነም ራሱን 2006 መጠቀም አለብን።
አሁን ምሳሌውን በጥንቃቄ እንመልከት ምሳሌያችን የ2006ን ወንጌላዊና የዋለበትን ዕለት ለማወቅ ስለሆነ የምንጠቀመው ራሱን የ2006ን ዘመን ነው።
ምሳሌ 1፡ የ2006 ዓ/ም ወንጌላዊ ማነው?
5500+2006=7506 4=1876 ደርሶ 2(ሁለት) ይቀራል።
ሰለዚህ የ2006 ዓ/ም ወንጌላዊ ማርቆስ  ነበር ወይም ነው ማለት ነው።
ምሳሌ2፡ የ2006 ዓ/ም አዲስ ዓመት የዋለበት እለት ወይም ቀን ማን ነበር?
7506+1876=9381 7=1340 ደርሶ 2(ሁለት) ይቀራል። ስለዚህ የ2006 ዓ/ም አዲስ ዓመት የዋለበት እለት ወይም ቀን ረቡዕ ነበር ማለት ነው።
ዓመተ ፍዳ + ዓመተ ዓ/ም ወጤቱን ለ4 በማካፈል ወንጌላዊውን ያገኛሉ።
ዓመተ ዓለሙን እና ዓመተ ዓለሙ ለ4 ተካፍሎ የተገኘውን ውጤት ደምረው ለ7 በማካፈል የዓዲሱን ዓመት መጀመሪያ ቀን ያውቃሉ ። (ዓመተ ፍዳ+ ዓመተ ምሕረት ሲካፈል ለ4 = ወንጌላዊ። ዓመተ ዓለም + ለ4 ተካፍሎ የተገኘው ውጤት ሲካፈል ለ7 = የዓዲስ አመት መጀመሪያ ቀን) ይሆናል።
አሁን የ2007ን ወንጌላዊና የሚውልበትን ዕለት ማግኘት የ እናንተ ድርሻ ይሆናል።
5500+2006=7506÷4=1876 ደርሲ ቀሪ 2 = 2ኛው ወንጌላዊ
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ዓመተ ዓለም= 5500+ ዓመተ ምህረት (5500+2007=7507)
7507(ዓመተ ዓለም) ÷4 = 1876 ተካፍሎ ቀሪ 3 ይሆናል ስለዚህ ሦስተኛው ወንጌል
 የዘመኑ ወንጌላዊ ነው ማለት ነው።
ዓመተ ዓለም (7507)+1876 = 9383÷7=1340 ደርሶ 3 ይቀራል በሥነ ስሌት ትምህርት ከሳምንቱ 3ኛው ቀን ሐሙስ ስለሆነ የ2007 ዓ/ም አዲስ ዓመት ሐሙስ ይውላል፡
ዘመኑ ሉቃስ ዕለቱ ሐሙስ
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Tuesday, August 5, 2014

Part 13

Learn Geez Language part 13

በዛሬው በክፍል አሥራ ሦስት ትምህርታችን ባለፈው በክፍል አሥር ትምህርታችን ቃል በገባሁላችሁ መሠረት በግእዝ ቋንቋ ሁለት ጽሁፎችን አቅርቤ እያንዳንዳችሁ ወደ አማርኛ ለመተርጎም እንድትሞክሩና ከፈተናው መልስ በኋላ ትርጉማቸውን እንደምተረጉምላችሁ ተነጋግረን ነበር። ስለዚህ ሁላችሁም ሞክራችሁ እንደ ሚሆን ሙሉ ተስፋ አለኝ።

ዛሬ ከተለመደው ጊዜ ዘግየት ብዬ ነው ትምህርቱን ያዘጋጀሁት እስከ ዛሬ በየ15 ቀናት አርብ ወይም ቅዳሜ ነበር የግእዝን ትምህርት የማስተላልፈው ሆኖም ግን በሥራ ጥበት ምክንያት በሦስ ቀናት ዘግይቷል። ቢሆንም ዋናው ቁም ነገር ግን የሚተላለፈውን በተላለፈበት ቀን አንድ ጊዜ ብቻ አዳምጦ ወይም አንቦ ማለፉ ላይ ሳይሆን እየደጋገሙ ማጥናቱና በተለያዩ አጋጣሚዎች ልምምድ ማድረጉ ስለሆነ በመካከል ሰፋ ያለ የጊዜ ክፍተት መኖሩ ይጠቅማል እንጂ አይጎዳም ብዬ አምናለሁ።

በመሆኑም ዛሬ ሁለቱን (2) የግእዝ ደብዳቤዎች ወይም ጽሁፎች ወደ አማርኛ እተረጉምላችኋለሁ። በንግግራችን መሠረት ቀድማችሁ ለመተርጎም የሞከራችሁ ሰዎች ከሙከራችሁ ጋር እኔ የምሰጠውን ትርጉም አነጻጽሩ። የሚስተካከለውን አስተካክሉ ወይም አርሙ። ያልገባችሁን በጥያቄ መልክ ብታቀርቡልኝ ማብራርያ ልሰጣችሁ እችላለሁ።

ለመተርጎም ያልሞከራችሁም ካላችሁ አሁንም መሞከሩ አይከፋም ። ምክንያቱም ካልሞከርን በምንም ተአምር በመስማት ብቻ ማወቅ አንችልም ። ይህ የሥርዓተ ትምህርት የማይታበል ሐቅ ነው።

አሁን ለመከታተል ያመቻችሁ ዘንድ በከፊል በከፊል ዐረፍተ ነገራቱን እየከፋፈልኩ ወይም በመለያየት እተረጉምላችኋለሁ ተከታተሉ። አፈታቱ የሚሄደው ዐረፍተ ነገሩ በአማርኛ ሲነገር እንደሚሰጠው ትርጉም እንጂ እንደ ግእዙ የቃላት አቀማመጥ ቅደም ተከተሉን ላይጠብቅ ይችላል።

ይህ ማለት ለምሳሌ፡ “ኦ ድንግል ምልእተ ውዳሴ” የሚለውን ወደ አማርኛ መፍታት ብንፈልግ ልክ እንደ ቃላቱ አቀማመጥ ከመጀመሪያው ማለትም ኦ ድንግል ከሚለው አንጀምርም የምንጀምረው “ምልእተ ውዳሴ” ከሚለው ይሆናል። ይህ ሕግ በተለያዩ ዐረፍተ ነገራት ተመሳሳይ አይሆንም ፡ ከመጀመሪያው ዐረፍተ ነገር ወይም ቃል ሊጀምርም ይችላል። የሚወስነው የያንዳንዱ ዐረፍተ ነገር ይዘት ነው።

ሰለዚህ “ኦ ድንግል ምልእተ ውዳሴ” የሚለውን ለመፍታት ምልእተ ውዳሴ ከሚለው ከሦስተኛው ቃል እንጀምራለን። በመሆኑም ወደ አማርኛ ሲተረጎም “ምስጋናን የተመላሽ ድንግል ሆይ” ይሆናል ማለት ነው። ስለዚህ በዚህ ዐረፍተ ነገር ይዘት ግእዙ ወደ አማርኛ ሲተረጎም በግእዙ የመጀመሪያ ቃል ወይም ሆሄ የነበረው በአማርኛው መጨረሻ ላይ ሆነ ማለት ነው።

ሳስረዳ ቃላቱን ወይም ዐረፍተ ነገራቱን የምደጋግምላችሁ በማወቅ ነው። ምክንያቱም በትምህርት ላይ መደጋገም ተማሪዎች ያልሰሙትን እንዲሰሙ፤ ያልተገነዘቡትን እንዲገነዘቡ ይረዳል።

ሁሉም በአንድ ጊዜ ሲፈታ
ግእዝ፡
ሰላም ለክሙ አኃውየ ወአኃትየ አርድእተ ልሳነ ግእዝ ኩልክሙ፤ ዮም እፈቅድ ከመ እንብብክሙ ወአለብወክሙ በይነ አሰርቱ ወአሃዱ ክፍላተ ትምህርትነ ዘመሐርኩክሙ በቅድም። ወእምኔሆሙ እጤይቀክሙ አሠርተ ጥያቄያተ። ወናሁ ይደልወክሙ ታንብቡ ወትስምኡ ኩሎሙ አርእስተ ትምህርት ዳግመ።

አማርኛ
የግእዝ ቋንቋ ተማሪዎች ወንድሞቼና እኅቶቼ ሁላችሁ ሰላም ለእናንተ ይሁን (እንደ ምን አላችሁ)? ዛሬ በዛሬው ዕለት ከዚህ በፊት ስላስተማርኳችሁ አሥራ አንድ የትምህርት ክፍሎች(ክፍሎቻችን) አስታውሳችሁና እነግራችሁ ዘንድ እወዳለሁ። ከእነሱም ውስጥ (ከተጠቀሱት11 ክፍሎች) አሥር ጥያቄዎችን እጠይቃችኋለሁ።ስለዚህ አሁን (ከዛሬ ጀምሮ) ሁሉንም የትምህርት ክፍሎች ደግማችሁ (እንደገና) ታነቡና ትሰሙ ዘንድ ይገባችኋል።

በከፊል በከፊል ሲተረጎም፡
ሰላም ለክሙ አኃውየ ወአኃትየ አርድእተ ልሳነ ግእዝ ኩልክሙ፤
የግእዝ ቋንቋ ተማሪዎች ወንድሞቼና እኅቶቼ ሁላችሁ ሰላም ለእናንተ ይሁን (እንደ ምን አላችሁ)
ዮም እፈቅድ ከመ እንብብክሙ ወአለብወክሙ በይነ አሰርቱ ወአሃዱ ክፍላተ ትምህርትነ ዘመሐርኩክሙ በቅድም።
ዛሬ በዛሬው ዕለት ከዚህ በፊት ስላስተማርኳችሁ አሥራ አንድ የትምህርት ክፍሎች(ክፍሎቻችን) አስታውሳችሁና እነግራችሁ ዘንድ እወዳለሁ።
ወእምኔሆሙ እጤይቀክሙ አሠርተ ጥያቄያተ።
ከእነሱም ውስጥ(ከተጠቀሱት11 ክፍሎች) አሥር ጥያቄዎችን እጠይቃችኋለሁ።
ወናሁ ይደልወክሙ ታንብቡ ወትስምኡ ኩሎሙ አርእስተ ትምህርት ዳግመ።
ስለዚህ አሁን (ከዛሬ ጀምሮ) ሁሉንም የትምህርት ክፍሎች ደግማችሁ (እንደገና) ታነቡና ትሰሙ ዘንድ ይገባችኋል።

የሁለተኛው ደብዳቤ ፍች፡

ሁለተኛው ደብዳቤ ለመፍታ መከፋፈል አያስፈልገኝም ምክንያቱም የዐረፍተ ነገራቱ ይዘት ራሱ የተከፋፈለ ስለሆነ ለመተርጎምም ሆነ ለመከታተል ቀላልና አመች ነው። ቶሎ ለመገንዘብ ይረዳችሁ ዘንድ በሁሉም ጽሁፎች ውስጥ ያሉትን ቃላትና ትርጎማቸውን አሁንም ደግሜ አቅርቤላችኋለሁ።
ግእዝ፡
ዛቲ ጦማረ መልእክት ትብጻሕ ኀበ አርድእትየ አርድእተ ልሳነ ግእዝ ዘበኀበ ኵሉ ተፈቅረ። ኦ አርድእት አፍቀርኩ ከመ እምሐርክሙ በይነ ዜና ፍጥረት ዘእግዚአብሔር አምላክነ፡
በቀዳሚ  ዕለት (በእሁድ ዕለት) ገብረ እግዚአብሔር ሰማየ ወምድረ
በሰኑይ ዕለት ገብረ(ፈጠረ) ባሕረ ወየብሰ
በሠሉስ ዕለት ገብረ ሐመልማለ ሣዕር ወዕፀወ፤ ወአዝርእተ
በረቡዕ ዕለት ገብረ ፀሓየ ወወርኀ ወከዋክብተ
በኀሙስ ዕለት ገብረ እንስሳ ወአራዊተ፤ ወአእዋፈ ወኩሎ
በሰዱስ ዕለት ገብሮሙ/ ፈጠሮሙ ለአዳም ወሔዋን  ብእሴ ወብእሲተ
ወበሳብዕት ዕለት አዕረፈ እግዚአብሔር እምኵሉ ግብሩ።
አማርኛ
ይህች የመልእክት ደብዳቤ(ጽሁፍ) በሁሉ ዘንድ የተወደደ የሆነው የግእዝ ቋንቋ ተማሪዎቼ ትድረስ።
ተማሪዎች ሆይ አምላካችሁ እግዚአብሔር  ስለፈጠረው  ፍጥረት ነገር  ወይም ዜና፤ ታሪክ አስተምራችሁ ዘንድ ወደድኩ።
በመጀመሪያው ዕለት(በእሁድ ዕለት) እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ፈጠረ።
በእለተ ሰኞ (በሁለተኛው ቀን ባሕርንና የብስን ፈጠረ።
በሦስተኛው ቀን የሣር ልምላሜዎችን ዕጸዋትን እና አዝርእትን ፈጠረ።
በዕለተ ረቡዕ ፀሐይን፤ ጨረቃን እና ከዋክብትን ፈጠረ።
በአምስተኛው ቀን እንስሳን፤ አራዊትን፤ እና አእዋፍን(ወፎችን) የመሳሰሉትን ፈጠረ።
በስድስተኛው ቀን አዳምን እና ሔዋንን ወንድ እና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው።
በሰባተኛዋም ቀን እግዚአብሔር ከሥራው ሁሉ አረፈ።
የሚቀጥለው ትምህርት በሁለት ሰዎች መካከል የሚደረግ የግእዝ ውይይት/ጭ ውውት/(Dialogue) ይሆናል።

የቃላት ትርጉም፡ ለመጀመሪያው ምንባብ



አኃውየ =ወንድሞቼ
አኃትየ=እኅቶቼ
ወ=እና
ልሳን=ቋንቋ
ኩልክሙ=ሁላችሁ(ሁላችሁም)
ዮም=ዛሬ
እፈቅድ=እወዳለሁ
በቅድም = በመጀመሪያ/በፊት/ከዚህ በፊት
ከመ=ዘንድ(እንደ)
እንብብክሙ=እነግራችሁ ዘንድ
አለብወክሙ=አስታውሳችሁ ዘንድ
በይነ=ስለ
10ቱ=አሥሩ
ወሠርቱ ወአሐዱ=አሥራ አንዱ
እምኔሆሙ=ከነሱ
እጤይቀክሙ=እጠይቃችኋለሁ
አሠርተ ጥያቄያተ=10 ጥያቄዎችን
ናሁ=አሁን
ይደልዎክሙ=ይገባችኋል
ታንብቡ=ታነቡ ዘንድ
ወታጽምኡ=ትሰሙ/ታዳምጡ ዘንድ
ኩሎሙ=ሁሉንም
አርእስተ ትምህርት= የትምህርት አርእስት/ክፍሎች
ዳግሞ=እንደገና/ሁለተኛ/ዳግሞኛ

የቃላት ትርጉም ለሁለተኛው ምንባብ

ጦማር=ጽሁፍ /ደብዳቤ
ገብረ=ፈጠረ/ሠራ/አደረገ
መልእክት=በቁሙ መልእክት
ትብጻሕ=ትድረስ
ዘበኀበ ኩሉ=በሁሉ ዘንድ
ኦ=ሆይ
በቀዳሚ ዕለት=በመጀመሪያው ቀን
ዕለት=ቀን
በሰኑይ=በሁለተኛው
በሰሉስ=በሦስተናው
በረቡዕ=በአራተኛው
በሐሙስ=በአምስተኛው
በሳድስ=በስድስተኛው
በሳብዕት=በሰባተኛዋ
ማስታዎሻ፦
የመጀመሪያ ቀን የተባለው ዕሁድ
ሰኑይ =ሰኞ
ሰሉስ=ማክሰኞ
ረቡዕ =ረቡዕ
ሐሙስ=ሐሙስ
ሳድስ=አርብ
ሳብዕት=ቅዳሚት/ቅዳሜ