Tuesday, August 5, 2014

Part 13

Learn Geez Language part 13

በዛሬው በክፍል አሥራ ሦስት ትምህርታችን ባለፈው በክፍል አሥር ትምህርታችን ቃል በገባሁላችሁ መሠረት በግእዝ ቋንቋ ሁለት ጽሁፎችን አቅርቤ እያንዳንዳችሁ ወደ አማርኛ ለመተርጎም እንድትሞክሩና ከፈተናው መልስ በኋላ ትርጉማቸውን እንደምተረጉምላችሁ ተነጋግረን ነበር። ስለዚህ ሁላችሁም ሞክራችሁ እንደ ሚሆን ሙሉ ተስፋ አለኝ።

ዛሬ ከተለመደው ጊዜ ዘግየት ብዬ ነው ትምህርቱን ያዘጋጀሁት እስከ ዛሬ በየ15 ቀናት አርብ ወይም ቅዳሜ ነበር የግእዝን ትምህርት የማስተላልፈው ሆኖም ግን በሥራ ጥበት ምክንያት በሦስ ቀናት ዘግይቷል። ቢሆንም ዋናው ቁም ነገር ግን የሚተላለፈውን በተላለፈበት ቀን አንድ ጊዜ ብቻ አዳምጦ ወይም አንቦ ማለፉ ላይ ሳይሆን እየደጋገሙ ማጥናቱና በተለያዩ አጋጣሚዎች ልምምድ ማድረጉ ስለሆነ በመካከል ሰፋ ያለ የጊዜ ክፍተት መኖሩ ይጠቅማል እንጂ አይጎዳም ብዬ አምናለሁ።

በመሆኑም ዛሬ ሁለቱን (2) የግእዝ ደብዳቤዎች ወይም ጽሁፎች ወደ አማርኛ እተረጉምላችኋለሁ። በንግግራችን መሠረት ቀድማችሁ ለመተርጎም የሞከራችሁ ሰዎች ከሙከራችሁ ጋር እኔ የምሰጠውን ትርጉም አነጻጽሩ። የሚስተካከለውን አስተካክሉ ወይም አርሙ። ያልገባችሁን በጥያቄ መልክ ብታቀርቡልኝ ማብራርያ ልሰጣችሁ እችላለሁ።

ለመተርጎም ያልሞከራችሁም ካላችሁ አሁንም መሞከሩ አይከፋም ። ምክንያቱም ካልሞከርን በምንም ተአምር በመስማት ብቻ ማወቅ አንችልም ። ይህ የሥርዓተ ትምህርት የማይታበል ሐቅ ነው።

አሁን ለመከታተል ያመቻችሁ ዘንድ በከፊል በከፊል ዐረፍተ ነገራቱን እየከፋፈልኩ ወይም በመለያየት እተረጉምላችኋለሁ ተከታተሉ። አፈታቱ የሚሄደው ዐረፍተ ነገሩ በአማርኛ ሲነገር እንደሚሰጠው ትርጉም እንጂ እንደ ግእዙ የቃላት አቀማመጥ ቅደም ተከተሉን ላይጠብቅ ይችላል።

ይህ ማለት ለምሳሌ፡ “ኦ ድንግል ምልእተ ውዳሴ” የሚለውን ወደ አማርኛ መፍታት ብንፈልግ ልክ እንደ ቃላቱ አቀማመጥ ከመጀመሪያው ማለትም ኦ ድንግል ከሚለው አንጀምርም የምንጀምረው “ምልእተ ውዳሴ” ከሚለው ይሆናል። ይህ ሕግ በተለያዩ ዐረፍተ ነገራት ተመሳሳይ አይሆንም ፡ ከመጀመሪያው ዐረፍተ ነገር ወይም ቃል ሊጀምርም ይችላል። የሚወስነው የያንዳንዱ ዐረፍተ ነገር ይዘት ነው።

ሰለዚህ “ኦ ድንግል ምልእተ ውዳሴ” የሚለውን ለመፍታት ምልእተ ውዳሴ ከሚለው ከሦስተኛው ቃል እንጀምራለን። በመሆኑም ወደ አማርኛ ሲተረጎም “ምስጋናን የተመላሽ ድንግል ሆይ” ይሆናል ማለት ነው። ስለዚህ በዚህ ዐረፍተ ነገር ይዘት ግእዙ ወደ አማርኛ ሲተረጎም በግእዙ የመጀመሪያ ቃል ወይም ሆሄ የነበረው በአማርኛው መጨረሻ ላይ ሆነ ማለት ነው።

ሳስረዳ ቃላቱን ወይም ዐረፍተ ነገራቱን የምደጋግምላችሁ በማወቅ ነው። ምክንያቱም በትምህርት ላይ መደጋገም ተማሪዎች ያልሰሙትን እንዲሰሙ፤ ያልተገነዘቡትን እንዲገነዘቡ ይረዳል።

ሁሉም በአንድ ጊዜ ሲፈታ
ግእዝ፡
ሰላም ለክሙ አኃውየ ወአኃትየ አርድእተ ልሳነ ግእዝ ኩልክሙ፤ ዮም እፈቅድ ከመ እንብብክሙ ወአለብወክሙ በይነ አሰርቱ ወአሃዱ ክፍላተ ትምህርትነ ዘመሐርኩክሙ በቅድም። ወእምኔሆሙ እጤይቀክሙ አሠርተ ጥያቄያተ። ወናሁ ይደልወክሙ ታንብቡ ወትስምኡ ኩሎሙ አርእስተ ትምህርት ዳግመ።

አማርኛ
የግእዝ ቋንቋ ተማሪዎች ወንድሞቼና እኅቶቼ ሁላችሁ ሰላም ለእናንተ ይሁን (እንደ ምን አላችሁ)? ዛሬ በዛሬው ዕለት ከዚህ በፊት ስላስተማርኳችሁ አሥራ አንድ የትምህርት ክፍሎች(ክፍሎቻችን) አስታውሳችሁና እነግራችሁ ዘንድ እወዳለሁ። ከእነሱም ውስጥ (ከተጠቀሱት11 ክፍሎች) አሥር ጥያቄዎችን እጠይቃችኋለሁ።ስለዚህ አሁን (ከዛሬ ጀምሮ) ሁሉንም የትምህርት ክፍሎች ደግማችሁ (እንደገና) ታነቡና ትሰሙ ዘንድ ይገባችኋል።

በከፊል በከፊል ሲተረጎም፡
ሰላም ለክሙ አኃውየ ወአኃትየ አርድእተ ልሳነ ግእዝ ኩልክሙ፤
የግእዝ ቋንቋ ተማሪዎች ወንድሞቼና እኅቶቼ ሁላችሁ ሰላም ለእናንተ ይሁን (እንደ ምን አላችሁ)
ዮም እፈቅድ ከመ እንብብክሙ ወአለብወክሙ በይነ አሰርቱ ወአሃዱ ክፍላተ ትምህርትነ ዘመሐርኩክሙ በቅድም።
ዛሬ በዛሬው ዕለት ከዚህ በፊት ስላስተማርኳችሁ አሥራ አንድ የትምህርት ክፍሎች(ክፍሎቻችን) አስታውሳችሁና እነግራችሁ ዘንድ እወዳለሁ።
ወእምኔሆሙ እጤይቀክሙ አሠርተ ጥያቄያተ።
ከእነሱም ውስጥ(ከተጠቀሱት11 ክፍሎች) አሥር ጥያቄዎችን እጠይቃችኋለሁ።
ወናሁ ይደልወክሙ ታንብቡ ወትስምኡ ኩሎሙ አርእስተ ትምህርት ዳግመ።
ስለዚህ አሁን (ከዛሬ ጀምሮ) ሁሉንም የትምህርት ክፍሎች ደግማችሁ (እንደገና) ታነቡና ትሰሙ ዘንድ ይገባችኋል።

የሁለተኛው ደብዳቤ ፍች፡

ሁለተኛው ደብዳቤ ለመፍታ መከፋፈል አያስፈልገኝም ምክንያቱም የዐረፍተ ነገራቱ ይዘት ራሱ የተከፋፈለ ስለሆነ ለመተርጎምም ሆነ ለመከታተል ቀላልና አመች ነው። ቶሎ ለመገንዘብ ይረዳችሁ ዘንድ በሁሉም ጽሁፎች ውስጥ ያሉትን ቃላትና ትርጎማቸውን አሁንም ደግሜ አቅርቤላችኋለሁ።
ግእዝ፡
ዛቲ ጦማረ መልእክት ትብጻሕ ኀበ አርድእትየ አርድእተ ልሳነ ግእዝ ዘበኀበ ኵሉ ተፈቅረ። ኦ አርድእት አፍቀርኩ ከመ እምሐርክሙ በይነ ዜና ፍጥረት ዘእግዚአብሔር አምላክነ፡
በቀዳሚ  ዕለት (በእሁድ ዕለት) ገብረ እግዚአብሔር ሰማየ ወምድረ
በሰኑይ ዕለት ገብረ(ፈጠረ) ባሕረ ወየብሰ
በሠሉስ ዕለት ገብረ ሐመልማለ ሣዕር ወዕፀወ፤ ወአዝርእተ
በረቡዕ ዕለት ገብረ ፀሓየ ወወርኀ ወከዋክብተ
በኀሙስ ዕለት ገብረ እንስሳ ወአራዊተ፤ ወአእዋፈ ወኩሎ
በሰዱስ ዕለት ገብሮሙ/ ፈጠሮሙ ለአዳም ወሔዋን  ብእሴ ወብእሲተ
ወበሳብዕት ዕለት አዕረፈ እግዚአብሔር እምኵሉ ግብሩ።
አማርኛ
ይህች የመልእክት ደብዳቤ(ጽሁፍ) በሁሉ ዘንድ የተወደደ የሆነው የግእዝ ቋንቋ ተማሪዎቼ ትድረስ።
ተማሪዎች ሆይ አምላካችሁ እግዚአብሔር  ስለፈጠረው  ፍጥረት ነገር  ወይም ዜና፤ ታሪክ አስተምራችሁ ዘንድ ወደድኩ።
በመጀመሪያው ዕለት(በእሁድ ዕለት) እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ፈጠረ።
በእለተ ሰኞ (በሁለተኛው ቀን ባሕርንና የብስን ፈጠረ።
በሦስተኛው ቀን የሣር ልምላሜዎችን ዕጸዋትን እና አዝርእትን ፈጠረ።
በዕለተ ረቡዕ ፀሐይን፤ ጨረቃን እና ከዋክብትን ፈጠረ።
በአምስተኛው ቀን እንስሳን፤ አራዊትን፤ እና አእዋፍን(ወፎችን) የመሳሰሉትን ፈጠረ።
በስድስተኛው ቀን አዳምን እና ሔዋንን ወንድ እና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው።
በሰባተኛዋም ቀን እግዚአብሔር ከሥራው ሁሉ አረፈ።
የሚቀጥለው ትምህርት በሁለት ሰዎች መካከል የሚደረግ የግእዝ ውይይት/ጭ ውውት/(Dialogue) ይሆናል።

የቃላት ትርጉም፡ ለመጀመሪያው ምንባብ



አኃውየ =ወንድሞቼ
አኃትየ=እኅቶቼ
ወ=እና
ልሳን=ቋንቋ
ኩልክሙ=ሁላችሁ(ሁላችሁም)
ዮም=ዛሬ
እፈቅድ=እወዳለሁ
በቅድም = በመጀመሪያ/በፊት/ከዚህ በፊት
ከመ=ዘንድ(እንደ)
እንብብክሙ=እነግራችሁ ዘንድ
አለብወክሙ=አስታውሳችሁ ዘንድ
በይነ=ስለ
10ቱ=አሥሩ
ወሠርቱ ወአሐዱ=አሥራ አንዱ
እምኔሆሙ=ከነሱ
እጤይቀክሙ=እጠይቃችኋለሁ
አሠርተ ጥያቄያተ=10 ጥያቄዎችን
ናሁ=አሁን
ይደልዎክሙ=ይገባችኋል
ታንብቡ=ታነቡ ዘንድ
ወታጽምኡ=ትሰሙ/ታዳምጡ ዘንድ
ኩሎሙ=ሁሉንም
አርእስተ ትምህርት= የትምህርት አርእስት/ክፍሎች
ዳግሞ=እንደገና/ሁለተኛ/ዳግሞኛ

የቃላት ትርጉም ለሁለተኛው ምንባብ

ጦማር=ጽሁፍ /ደብዳቤ
ገብረ=ፈጠረ/ሠራ/አደረገ
መልእክት=በቁሙ መልእክት
ትብጻሕ=ትድረስ
ዘበኀበ ኩሉ=በሁሉ ዘንድ
ኦ=ሆይ
በቀዳሚ ዕለት=በመጀመሪያው ቀን
ዕለት=ቀን
በሰኑይ=በሁለተኛው
በሰሉስ=በሦስተናው
በረቡዕ=በአራተኛው
በሐሙስ=በአምስተኛው
በሳድስ=በስድስተኛው
በሳብዕት=በሰባተኛዋ
ማስታዎሻ፦
የመጀመሪያ ቀን የተባለው ዕሁድ
ሰኑይ =ሰኞ
ሰሉስ=ማክሰኞ
ረቡዕ =ረቡዕ
ሐሙስ=ሐሙስ
ሳድስ=አርብ
ሳብዕት=ቅዳሚት/ቅዳሜ


No comments:

Post a Comment