Saturday, January 28, 2023

የእመቤታችን የቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያም ዕረፍት


የእመቤታችን የቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያም ዕረፍት ባጭሩ

እመቤታችን የተወለደችው ቅድመ ክርስቶስ በ5486 ዓ/ዓ ግንቦት 1 ቀን  ሲሆን ዘመነ ፍዳ ሊፈጸም 14 ዓመታት ሲቀሩት ማለት ነው፤ በመሆኑም በዚህ ዓለም እንደሚከተለው፣ በተጠቀሱት ቦታዎች ከልጇ ከእግዚአብሔር ወልድና ከተጠቀሱት ቅዱሳን ጋር ለ64 ዓመታት ኖራለች።

·         3 ዓመታት በወላጆቿ በቅዱስ ኢያቄምና በቅድስት ሐና ቤት

·         12 ዓመታት በቤተ መቅደስ እያገለገለች መላእክት እየመገቧት

·         9 ወራት ከ5 ቀናት በጠባቂዋ በቅዱስ ዮሴፍ ቤት

·         33 ዓመታት ከ 3 ወራት ከክርስቶስ ጋር ማለትም ከልጇና ከአምላኳ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ወንጌልን በመማርና መከራንም በመቀበል፣

·         ለ 15 ዓመታት በቀራንዮ አደባባይ በአደራነት ከተቀበላት ከወንጌላዊው ከቅዱስ ዮሐንስ ቤት ቆይታለች።

ማለትም ከ 5486 ዓ/ዓ እስከ 50 ዓ/ም ድረስ በድምሩ 64 ዓመታትን(ለ14 ዓመታት በዘመነ ፍዳ፣ ለ50 ዓመታት በዘመነ ምሕረት ማለት ነው) በምድራዊው ዓለም ከኖረች በኋላ ጥር 21 ቀን በዕለተ ዕሁድ በ50ዓ/ም ቅዱሳን ሐዋርያት በተገኙበት ከዚህ ዓለም በሞተ ሥጋ ተለየች።

ቅዱሳን ሐዋርያት በክብር አጅበው  ቅዱስ ሥጋዋን ወደ ጌቴሴማኒ የመቃብር ቦታ ይዘው ሲጓዙ ቤተ አይሁድ የቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያምን ቅዱስ አስከሬን ከሐዋርያት ነጥቀው ለማቃጠል በማሰብ ሲመጡ መላእክት ቅዱስ ሥጋዋን  ከሐዋርያት ነጥቀው በገነት ውስጥ ከዕፀ ሕይወት ሥር አኑረውት እስከ ነሐሴ 14 ቀን ቆይቷል። 


አምላካችን በቸርነት ይጠብቀን፣ የእመቤታችን ቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያም በረከትና አማላጅነት አይለየን።