Sunday, January 22, 2023

ዘመነ አስተርእዮ

 ዘመነ አስተርእዮ
















ዘመነ አስተርእዮ

መጻሕፍቶቼን ለመግዛት የሚከተለውን ሊንክ ይጫኑ

አስተርእዮ ማለት “አስተርአየ” ከሚለው ግስ ታየ፣ አሳየ፣ ወይም ተገለጠ፣ ማለት ነው። ዘመነ አስተርእዮ ማለትም የመገለጥ ወይም የመታየት ዘመን ማለት ነው። በዚህ ስም የሚጠሩት ወቅቶች በመሠረታዊነት ከልደት እስከ ጥምቀት ያሉት የእግዚአብሔር ወልድ በአላት ናቸው። ሆኖም ግን እነዚህ የመጀመሪያ ስለሆኑ ነው እንጅ በጠቅላላ ከልደቱ እስከ ዕርገቱ ያሉት የታሪክ ክስተቶች ሁሉ የመገለጥ ሥራዎች ወይም ክንውኖች ናቸው።

አንድን ነገር ወይም አካል ተገለጠ ወይም ታየ፣ ስንል መጀመሪያ ያልታየ፣ ያልተገለጠ፣ ይፋ ያልወጣ, ወዘተ መሆን አለበት። ቀድሞ በባሕርዩ/ በተፈጥሮው የታወቀ፣ የተገለጠ፣ ይፋ የሆነ፣ ነገርን፣አካልን፣ ተገለጠ ወይም ይፋ ሆነ አንልም። ምክንያቱም አዲስ ነገር አይደለም።

አሁን ባብራራሁት (ከዚህ በላይ ባለው) ቋንቋዊ ትንታኔ መሠረት እነዚህ ወቅቶች የመገለጥ ወይም የመታየት ወቅቶች በመባል የሚጠሩበትም ምክንያት በባሕርዩ መመርመር፣ በቦታ መወሰን፣ በአካል መወሰን,  በአካላዊ ዐይን መታየት፣ ወዘተ የሌለበት በአንድነትና በሦስትነት የሚመሰገን የዘላለም፤ አምላክ እግዚአብሔር በባሕርይ ልጁ በእግዚአብሔር ወልድ አማካኝነት ለዓለም የታየባቸው የተገለጠባቸው፣ እግዚአብሔር ወልድም በሥጋዌ እንደሰው በግልጽ በአካል ይፋ የሆነባቸው፤ ወቅቶች ስለሆኑ ነው።

“አስተርአየ ዘኢያስተርኢ” የማይታየው፣ የማይወሰነው፣ የማይዳሰሰው ታየ፣ተወሰነ፣ ተዳሰሰ። በነዚህ ዕለታት ወይም ዘመናት እግዚአብሔር ወልድ የእግዚአብሔር አብ ቃሉና ልጁ፤ የሕያው እግዚአብሔር ሕያው የባሕርይ ልጅ፤ ከሦስቱ አካላት አንዱ አካል መሆኑን አየን፤ እንዲሁም የማይታየውን እግዚአብሔርንም በእግዚአብሔር ወልድ አየንባቸው። አስተርእዮ ማለትም ማየት መታየት፣ ማሳየት ወዘተ ማለት ነው።

 ይህንንም የእግዚአብሔር ቃል “ለእግዚአብሔርሰ አልቦ ዘርእዮ ግሙራ አላ ወልድ ዋሕድ ዘሀሎ ውስተ ሕፅነ አቡሁ ውእቱ ነገረነ” = “መቼም ቢሆን እግዚአብሔርን ያየው አንድስንኳ የለም በአባቱ እቅፍ ያለ አንድ ልጁ እርሱ ተረከው” በማለት በእግዚአብሔር ወልድ ወይም በመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዴት እንዳየነው ይነግረናል ። ዮሐንስ 1፡18

አስተርእዮ በዕለተ  ልደቱ/በልደቱ እንዴት አየነው?

በልደቱ ታየ ስንል በቤተልሔም የከብቶች በረት መላእክትና ሰዎች በአንድነት በአካል አዩት፤ ከፊት ለፊቱ ቆመው ዘመሩለት፣ አመሰገኑት፤ የጥበብ ሰዎችም በአካለ ሥጋ ቀርበው ወርቅ፣ ዕጣን፣ ከርቤ በስጦታ አቀረቡለት። ማለትም የማይወሰነው ተወስኖ፣ የማይታየው ተገልጦ፣ ታየ፣ አማኑኤል ወይም አምላክ ወሰብእ ሆነ፤ እግዚአብሔር ምስሌነ፡ እግዚአብሔር ከኛጋር ሆነ ወይም ነው ማለትም ተግባራዊ ትርጉሙ ይኸው ነው።

አስተርእዮ በዕለተ  ጥምቀቱ/በጥምቀቱ እንዴት አየነው?

በጥምቀቱ ታየ ስንል በፈለገ ዮርዳኖስ በዮሐንስ እጅ ሲጠመቅ ሰማያት ተከፈቱ። የባሕርይ አባቱ እግዚአብሔር አብ በሰማይ ደመና “ዝንቱ ውእቱ ወልድየ ዘአፈቅር ዘቦቱ ሠመርኩ” = “በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው” ሲል በአካለ ሥጋ በዮርዳኖስ ወንዝ በዮሐንስ እጅ ለሚጠመቀው የባሕርይ ልጁ እግዚአብሔር ወልድ ድምፁን አሰማ። ማቴ.3፡17።

 የባሕርይ ሕይወቱ መንፈስቅዱስ በነጭ ርግብ አምሳል በራሱላይ በመቀመጥ በእደ ዮሐንስ የሚጠመቀው ማን እንደሆነ አመለከተ። ማቴ. 3፡16።

ስለዚህም በጥምቀት የአብ የወልድ መንፈስ ቅዱስ የስም፡ የአካልየግብር፡ ሦስትነ፣ የባሕርይ፡ የኅልውና፡ የአገዛዝ፡ ወዘተ አንድነት፡ ታየ፤ ተገለጠም። ማለትም እግዚአብሔር አብና እግዚአብሔር መንፈስቅዱስ በቃላቸው በእግዚአብሔር ወልድ አማካኝነት ተገለጡ። ለዚህም ነው “ዘመነ አስተርእዮ” ወይም የመገለጥ ዘመን የምንለው። ማቴዎስ 3፡13 (ስለ ጥምቀት ሙሉ ታሪክና ትምህርት “ሀብታችንና ሥርዓቱ” የተባለውን መጽሐፌን ወይም በአውደ ጥናት የዩቱብ ድረገጼ” “ምን ማለት ነው” የሚለውን ተከታታይ ትምህርት ይመልከቱ።

ከዚህ በላይ ያየነው ዘመነ አስተርእዮ የሚለውን ሃይለ ቃል በመተርጎም እና ዘመነ አስተርእዮ ያስባሉትን ምክንያቶቹን ልደትን እና ጥምቀትን መሠረት አድርገን በማብራራት ነበር። በመቀጠል ደግሞ በአላቱን በተለይ ስለልደት ባጭሩ ዘርዘር አድርገን እንመለከታለን።

ተስፋ፣ ፍቅር፣ ሰላም፣ ደስታ።

በዘመነ አስተርእዮ ያገኘናቸውን አራት ወሳኝና የሥጋዌ ውጤቶችን ከማየታችን በፊት የተወሰኑ ስያሜዎችንና ትርጉማቸውን እንመለከታለን።

ልደት ማለት መወለድ ማለት ሲሆን (ለፍጡራን ልደት ሲባል ካለመኖር ወደ መኖር መምጣት ማለት ነው) ለአምላክ ግን ልደት ሲባል ለየት ያለ ትንታኔ ይሰጠዋል። ምክንያቱም እግዚአብሔር ወልድ ያልነበረበት ጊዜ ስለሌለ ለፍጡራን የተሰጠው የልደት ትንታኔ ሊሰጠው አይችልም።  

የእግዚአብሔር ወልድ የኩነትና የሥጋዌ ስሞች

 በመጀመሪያ ክርስቶስ ብለን የምንጠራው ከሦስቱ የእግዚአብሔር አካላት አንዱን ቃልን ሲሆን በሚከተሉት ስድስት አበይት ስሞች እንጠራዋለን።

1.  ቃል፡ የእግዚአብሔር አብ እና የእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ቃላቸው ስለሆነ በኩነት ወይም በመሆን ስሙ ቃል ተብሎ ይጠራል።

2.  ወልድ፡ የእግዚአብሔር አብ የባሕርይ ልጅ ስለሆነ በግብር ስሙ “ወልድ” ተብሎ ይጠራል፤ ወልድ ማለት የተወለደ ማለት ነው። እግዚአብሔር ወልድ ሁለት ልደቶች አሉት፤

አንዱ ልደቱ ቅድመዓለም ያለእናት ከባሕርይ አባቱ ከአብ የተወለደው ልደት ሲሆን ይህ ልደት በጊዜ፣ በዘመን፣ በቦታ የሚወሰን አይደለም።

ሁለተኛው ልደቱ ከቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያም ያለአባት የተወለደው ልደቱ ሲሆን ይህ ልደቱ ግን በዘመን፣ በጊዜ፣ በቦታም የተወሰነ ነው። ስለዚህም ከቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያም የተወለደው በተለመደው ታሪክ በዘመነ ማቴዎስ ታህሣስ 29 ቀን ማክሰኞ ከሌሊቱ 6 ሰዓት በቤተልሔም የከብቶች በረት ነው(ዕለቱ እሁድ እንደነበረ የሚናገሩ መጻሕፍትም አሉ)። ስለ ክርስቶስ ትክክለኛ የልደት ቀን ለማወቅ “የዘመኑ ታሪክ” የተሰኘውን መጽሐፌን ተመልከቱ። ስለዚህ ሁለተኛ ልደቱ ቀኑ፣ ቦታው ዘመኑ፣ ወዘተ የታወቀ ነው።

3.   አማኑኤል፡ አማኑኤል ማለት ታላቁ ነቢይ ኢሳይያስና ከእግዚአብሔር የተላከው መልአክ እንደነገሩን “አምላክ ወሰብእ” ወይም እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ማለት ነው። ይህ ማለትም እግዚአብሔር በተዋሕዶ ሰው፤ ሰውም አምላክ በመሆን ፍጹም አምላክ ፍጹምም ሰው መሆኑን የሚገልጥ ስም ነው። ይህንንም ንቢዩ ኢሳይያስ በትንቢቱ “…ጌታ ራሱ ምልክት ይሰጣችኋል፣ እንሆ ድንግል ትፀንሳለች፣ ወንድ ልጅም ተወልዳለች፣ ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች…”። በማለት የተነበየው ሲሆን ኢሳ.7፡14፤ ወንጌላዊው ቅዱስ ማቴዎስም መልአኩ የነቢዩን ቃል ጠቅሶ ለቅዱስ ዮሴፍ ያስተላለፈውን መልእክት ጽፉል። ማቴ. 1፡18

4.  ኢየሱስ፡ መድኃኒት ማለት ነው፤ ምክንያቱም ዓለምን ያዳነ ስለሆነ

5.  ክርስቶስ፡ ቅቡዕ ማለት ሲሆን በዶግማችን የተዋሐደ ተብሎ ይተረጎማል።

6.  መድኃኔዓለም፡ መድኀኒት የሚለው ቃልና ዓለም የሚለው ቃላ በአንድ ላይ ተናቦ የሚፈጥረው ስያሜ ነው፤ ትርጉሙም “ዓለምን ያዳነ፤ የዓለም ወይም የፍጥረት አዳኝ ማለት ነው። በአጠቃላይ የተዘረዘሩት ስሞች ባሕርዩን እና ሥራውን የሚገልጡ ናቸው።

ለመሆኑ እግዚአብሔር ወልድ ለምን ተወለደ?

 ባጭሩ የሰውን ዘር ለማዳን ነው። በአዳምና በሔዋን ምክንያት ሰው ሁሉ ለሞት በሚያበቃ ወንጀል ተጠያቄ በመሆን የሞት ፍርድ ተፈርዶበት ስለነበር፤ ይህንን የሞት ፍርድ ደግሞ ከአምላክ በስተቀር ፍጡር ሊያስወግደው ስለማይችል ይህንን የሞት ፍርድ ለመሻር በተዋሕዶ ሰው መሆንንን መርጧል። ይህንን ያስመረጠው ደግሞ አስቀድሞ ከወደደውና በመልኩና በምሳሌው ፈጥሮ ካከበረው ከሰውልጅ ጋር ያለው ኢምክንያታዊ ፍቅር ነው። አባ ሕርያቆስም “ፍቅር ሰሀቦ ለወልድ ኀያል እመንበሩ ወአብጽሆ እስከለሞት” እንዲል።

“ኃጢአተኞችን ሊያድን ክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ዓለም መጣ፣ የሚለው ቃል የታመነና ሁሉ እንዲቀበሉት የተገባ ነው…” 1ኛ ጤሞ.1፡15

ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስም “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዷልና። ዓለም በልጁ እንዲድን ነው እንጂ በዓለም እንዲፈርድ እግዚአብሔር ወደ ዓለም አላከውምና” ዮሐ. 3፡16

የክርስቶስ ልደት ምን ዓይነት በአል ነው?

የክርስቶስ የልደት በአል ልክ እያንዳንዱ ሰው የተወለደበትን ቀን እንደሚያከብር ወይም እንደሚከበርለት ሁሉ አምላክ ለሰው ዘር ድኅነት ስል ከሥጋችን ሥጋን ከነፍሳችን ነፍስን ነሥቶ በተዋሕዶ ከቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያም የተወለደበትን ቀን አንድ ብለን በመቁጠር የምናከብረው በአል ሲሆን ዓመተ ምህረትን አንድ ብለን የቆጠርንበት ዕለትም ነው።ስለዚህ የአዲሱ የምሕረት ዓመት መጀመሪያም ነው።

ጥንተ ልደቱ ማለትም ለመጀመሪያ ጊዜ የተወለደበት ቀንና ዕለት እንዲሁም ዘመን በታሪክ መጻሕፍት እንደተጻፈው በ5500 ዘመን የፍጻሜ ቅጽበት ታህሣስ 29 ቀን ዕለተ ማክሰኞ በዘመነ ማቴዎስ ከሌሊቱ 6 ሰዓት በገሊላ አውራጃ በቤተልሔም ነበር። (በሌላ ታሪክ ዕለቱ እሑድ እንደነበር ይተረካል)። ስለዚህ ዛሬ የምናከብረው 2015ኛ ዓመተ ምህረትን ነው። የ2015 ዓመተምህረት በአል መስከረም አንድ ቀን ቢከበርም ዓመቱ የተጀመረው ዛሬ ጌታ በተወለደባት ክብረ በአል ነው።

ዓመተ ምሕረትን ከቆጠርን አይቀር በጠቅላላ ለዓለም ማለትም የዓለም ወይም የፍጥረት አንዱ ክፍል እንደመሆናችን መጠን ለእኛ የተሰጠንን በዓለም ላይ የመኖር ዕድሜም ሳናስታውስ ማለፍ የለብንም ብየ አምናለሁ።

ስለዚህ ይህንን የ2015ኛ የምህረት ዓመት ለማግኘት ለ5500 ዘመናት በተስፋ ኖረን ነበር፤ ከዚያ በኋላ ተስፋው በእግዚአብሔር ወልድ ከድንግል መወለድ ተፈጽሞ እንሆ 2015 የምሕረት ዓመታትን ኖረናል። “የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ከሴት የተወለደውን ከሕግም በታች የተወለደውን ልጁን ላከ” ገላ. 4፡4። ስለዚህ ዓለም ከተፈጠረ ዛሬ 7515ኛ ዓመትን ይዟል እንደ መጽሐፍ ቅዱስ አባባልም የዓለም ዕድሜ በ8000(ስምንት ሺህ) የተወሰነ ነው። “ይህ ዓለም ስምንት(8)ሺህ ይኑር ብሎ ስለወሰነው ነው እንጂ ስለነሳቸው አይደለም አለኝ ዕዝራ ሱቱኤል 6፡5።

በአሁኑ ጊዜ ዓለም ዕድሜዋን ልትጨርስ 485 ዓመታት ብቻ ቀርተዋታል። ነገር ግን እንደ ቅዱስ ወንጌል ቃል 8ኛው ሺህ ውስጥ በየትኛው ቅጽበት ዓለም እንደምታልፍ ሁሉን ከሚያውቅ ከሕያው እግዚአብሔር በስተቀር የሚያውቅ የለም። ማለትም በ8ኛው ሽህ ውስጥ መጀመሪያ፣ መካከል፣ ወይም መጨረሻ ሊሆን ይችላል ማለት ነው። “ስለዚያች ቀንና ስለዚያች ሰዓት ግን ከአባት ብቻ በቀር የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ፣ ልጅም ቢሆን የሚያውቅ የለም፤ የኖኅ ዘመን እንደነበረ የሰውልጅ መምጣት እንዲሁ ይሆናልና” ማቴዎስ፡ 24፡36

ቅዱስ መጽሐፍ በሚነግረን መሠረትም የዓለምን ፍፃሜ የሚተርኩ ምልክቶች ሙሉ በሙሉ በዓለማችን ታይተዋል አሁንም በባሰ ሁኔታ እየታዩ ነው። ታዲያ የዘመኑን ፍጻሜ እያየን ዘመኑን ቀድመን ወይም ከዘመኑ ጋር ከማለፋችን በፊት ልንዘጋጅ ይገባል እላለሁ።

በክርስቶስ ልደት የተገኙ አራት መሠረታውያን ስጦታዎች

ከላይ እንደገለጽኩት በአምላክ መወለድ አራት መሠረታዊ ነገሮችን አይተናል፤ አግኝተናልም። እነዚህም

1.  ተስፋ

2.  ፍቅር

3.  ሰላም

4.  ደስታ

የተባሉት ወሳኝ ነገሮች ወይም መንፈሳዊ ስጦታዎች ናቸው። እነዚህንም እንደሚከተለው አብራራለሁ።

ተስፋ፦ ለ5500 ዓመታት የጠበቅነው ተስፋ በከፊልም ቢሆን እውን ሆነ፤ ሙሉ በሙሉ በሞቱና በትንሣኤው እንደሚፈጸምም እምነታችን ጎለበተ፣ ተስፍችን ለመለመ። በመሆኑም ፍጹም የማይታበል ለሆነው ተስፋ ማረጋገጫ ሆነን።(ይህ ትንታኔ የልደትን ቀን መሠረት በማድረግ ነው እንጅ ተስፋችን ሙሉ በሙሉ ተፈጽሞ ከሞት ወደሕይወት የተሸጋገርንበትን የምሕረት ዓመት መቁጠር ከጀመርን 2015 ዓመታት አልፈዋል ስለዚህ ያልተፈጸመ ተስፋ የለም)

ፍቅር፦ ከመፈጠራችን በፊት የወደደንና በመልኩና በምሳሌው ፈጥሮ ያከበረን አምላካችን ባለመታዘዝ ከበደልነው በኋላ እንኳን በማይደበዝዝ ኢምክንያታዊ ፍቅሩ ምን ያህል እንደሚወደን የፍቅሩን ጽናት አወቅን። “በዚህ የእግዚአብሔር ፍቅር በእኛ ዘንድ ተገለጠ፣ በእርሱ በኩል በሕይወት እንኖር ዘንድ እግዚአብሔር አንድ ልጁን ወደ ዓለም ልኮታልና” 1ኛ ዮሐ. 49

ሰላም፦ በፍጡራንና በፈጣሪ መካከል የነበረውን መራራቅ ያስወገደ ነው፤ ስለዚህም ሰዎችና መላእክት በኅብረት የሰላምን መዝሙር እየዘመሩ አምላካቸውን አመሰገኑ ለሰው ዘርም መልካም ዜናን፣ ምኞትን አበሠሩ። “ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን ሰላምም በምድር ለሰውም በጎ ፈቃድ..” በማለት ሉቃስ 2፡ 13

ደስታ፦ በቤተልሔም የተሰማው ዜና ለሰብአዊ ፍጡር ሁሉ ፍጹም ደስታን የሚሰጥ መደኃኒት ስለተወለደ የአምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን ኃዘናችንን ወደ ደስታ ለወጠው። “እንሆ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ፤ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና።” ሉቃስ 2፡10

መልእክት፦

እግዚአብሔር ከእኛ ተወልዷል፣ የእርሱ አካል የኛ የእኛም የእርሱ ሆኗል፤ “አማኑኤል” ማለትም ትርጉሙ ይኸውነው፤ “እግዚአብሔር ምስሌነ” ስለዚህ አካላችን የእርሱ ማደሪያና መኖሪያ ነው፤ የእኛ አካል ለእርሱ ብቻ የተጠበቀና የተዘጋጀ መሆን አለበት እንጂ እንደ ቤተልሔም ቤቶች በሌላው ተመልቶ ለክርስቶስ ብቁ ያልሆነ ሊሆን አይገባም።

 

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

No comments:

Post a Comment