Sunday, August 13, 2017

መልስ ለትርጉም ጥያቄዎች


መልስ
የትርጉም ጥያቄ  አንድ

ወደ አማርጛ ይቀይሩ


"ወሀሎ አሐዱ ብእሲ ዘስሙ መላኩ አስማማው ዘይነብር በብሔረ አሜሪካ ወውእቱ ይሜህር ልሳነ ግእዝ በውስተ አውደ ጥናት "

ትርጉም1፡ =
 በአሜሪካን አገር የሚኖር ስሙ መላኩ አስማማው የሚባል አንድ ሰው አለ፤ እሱም በአውደ ጥናት የግእዝ ቋንቋን ያስተምራል።

ወይም ትርጉም 2፡=
አንድ በአሜሪካን አገር የሚኖር ስሙ መላኩ አስማማው የሚባል አንድ ሰው አለ፤ እሱም የግእዝ ቋንቋን በአውደ ጥናት ውስጥ ያስተምራል (እያስተማረ ነው)።

የትርጉም ጥያቄ ሁለት

ወደ አማርኛ ይቀይሩ


“ዛቲ ጦማረ መልእክት ትብጻህ ኀበ አርድእተ ልሣነ ግእዝ ዘመጽሐፈ ገጽ
እምነ መምህረ ልሣነ ግእዝ”

ትርጉም አንድ፡=
ይህች የመልእክት ደብዳቤ በፌስ ቡክ የግእዝ ቋንቋ ተማሪዎች ወደ ሆኑት ትድረስ።
                      ከግእዝ ቋንቋ አስተማሪ(መምህር)
ወይም ትርጉም ሁለት፡=
ይች የሰላምታ ደብዳቤ ከግእዝ ቋንቋ  አስተማሪ(መምህር) በፌስ ቡክ የግእዝ ቋንቋን ወደ ሚማሩ ተማሪዎች ትድረስ።

የግእዝን ሥነ ጽሁፍ በተለያየ ዓይነት መልኩ በተለይ የቃላትን ቅደም ተከተል በመቀያየር ሊተረጎም ይችላል፤ ነገር ግን አንዳንድ መታለፍ የሌለባቸው ሕጎች አሉ።
ለምሣሌ

“ይሜህር ልሣነ ግእዝ ቢል”

1.      የግእዝን ቋንቋ ያስተምራል
2.     የግእዝ ቋንቋን ያስተምራል
3.     ግእዝን ያስተምራል


እነዚህ ሦስቱም ለሰሚ በትክክል ሊረዱ ይችላሉ ማለትም ተናጋሪው ምን ማለት እንደ ፈለገ ማወቅ ይቻላል። በሰዋስው ህግ ግን ትክክለኛው አፈታት ወይም ትርጉም ሁለተኛው(2ኛው ) ነው። ምክንያቱም “ን” የሚለውን ተሳቢ ወይም (Direct Object) ለማምጣት የቃሉ የመጨረሻ ሆሄ “ግእዝ” “ራብዕ” “ሐምስ” ወይም “ሣብዕ” መሆን አለበት ስለዚህ “የግእዝን ቋንቋ” ማለት አይቻልም ለምን “ግእዝ” የሚጨርሰው በ”ሳድስ” ልሣነ ግእዝ ሲል “ልሣነ” የሚለው በ”ግእዝ” ስለሚጨርስ ተሳቢ መሆን ይችላል።

ይህ አገላለጽ ለአሁኑ ሊከብዳችሁ ስለሚችል። ሌላ ጊዜ ስለ “ገቢርና ተገብሮ” ስንማር ቪዲዮ ስላለ በደንብ ይገባችኋል። አሁን ግን አትጨነቁ።


የተወሰናችሁት ሠርታችሁታል፤ በተለይ ትርጉሙን ምን ለማለት እንደተፈለገ በደንብ ሁላችሁም ታውቁታላችሁ። የሰጣችሁትም ትርጉም ለሁሉም ሰው ያለምንም ችግር ሊገባ ወይም ሊረዳ የሚችል ነው። ብቻ የቃላትን አገባብ ወይም ግራመር የሚያውቁ ሰዎች ብቻ ናቸው የሰዋስው ስህተት መኖሩን ሊያውቁ የሚችሉት።
እና በጣም ጥሩ እየተራመዳችሁ ነው በርቱ።

 የቤት ሥራ!!

አሁን የሚከተለውን ሥነ ጽሁፍ ማለትም የተረጎማችሁትን ወደ የራሳችሁ ወይም በራሳችሁ ስም ጻፉ(ቀይሩት) በሚከተለው ዓይነት ቃላቱ እንደየ ጾታችሁና የምትኖሩበት አገር ትቀይራላችሁ።

"ወሀሎ  አሐዱ  ብእሲ  ዘስሙ  መላኩ አስማማው     ዘይነብር  በብሔረ አሜሪካ   ወውእቱ ይሜህር ልሳነ ግእዝ በውስተ አውደ ጥናት ።"
----- ----- -----  -----         የራሳችሁን ስም           ----    የምትኖሩበት አገር    -----     -----    ልሣነ ግእዝ  ---     የምትኖሩበት አገር



ምን አልባት ቃላቱ እንዳይከብዳችሁ የሚከተሉትን ቃላት ተጠቀሙ።

ሀለወት =ለሴት አለች ወይም ነበረች
አሐቲ= ለሴት አንዲት
ብእሲት= ሴት
ዘስማ= ለሴት ስሟ
ዘትነብር= ለሴት የምትኖር
ወይእቲ= ለሴት እሷም
ትሜህር= ለሴት ታስተምራለች

ካልገባችሁ ከመሥራታችሁ በፊት ጠይቁ
መልካም ሥራ
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
እምነ አውደ ጥናት ዘግእዝ


No comments:

Post a Comment