Tuesday, August 18, 2020

Pronouns/ተውላጠ አስማት

 Pronous - ተውላጠ አስማት     

                       

ሰላም ጤና ይስጥልኝ ከአውደ ጥናት ነው፤


መጻሕፍት ለመግዛት ከዚህ በታች ያሉትን መጻሕፍቱን ይጫኑ ወይም በ +1 703 254 6601 ደውሉ 




በዛሬው በክፍል 7 የእንግሊዘኛ ቋንቋ ትምህርታችን የምንማረው ከ8ቱ የንግግር ክፍሎች በሁለተኛ ደረጃ የጠቀስነውን Pronoun/ፕሮናውን የተባለውን ርእስ ነው።  Pronouns/ፕሮናውንስ የሚባሉት በጣም ብዙ ዓይነት ናቸው እኛ ግና ለጊዜው የተወሰኑትን ብቻ ነው የምንማረው። በመጀመሪያ

 

·         Pronoun/ፕሮ ናውን ማለት ምን ማለት ነው?

·         የፕሮናውን ሥራ ምንድ ነው?

·         ፕሮ ናውን ስንት ዓይነት ነው?

 

የሚሉትን ሦስት መሠረታውያን ጥያቄዎች ከመለስን በኋላ Pronouns/ፕሮ ናውንስ በተግባር በዐረፍተ ነገር ሲገቡ ምን እንደሚመስሉ አንድ በአንድ እንማራለን። መልካም ትምህርት።

 

Pronoun/ፕሮናውን ምን ማለት ነው፡ (ስያሜን የሚመለከት ማብራርያ)

Pronoun: A word that replaces a noun in a sentences or takes the place of noun in a sentence. = ፕሮ ናውን የሚባለው በዐረፍተ ነገር ውስጥ ስምን ተክቶ የሚገባ ወይም የስምን ቦታ የሚይዝ ነው

 

ባለፈው በክፍል 6 ትምህርታችን Noun/“ናውን” ማለት “ስም” ማለት እንደሆነና የተለያዩ የስም ዓይነቶችን በመጥቀስ ተምረን ነበር።

ስለዚህ የዛሬው ደግሞ Pro/“ፕሮ” የሚለውን Prefix/ “ፕሪፊሽ” ከማስቀድሙ በስተቀር Noun/“ናውን” የሚለው ስያሜ አይቀየርም፤ Pro/ፕሮ የሚለው ተቀጽላ ስላለ ግን ለየት ያለ ማብራርያን እሰጣለሁ ።

 

·         Pro/ፕሮ = ምትክ/ፈንታ

·         Noun/ናውን = ስም

·         ስለዚህ በአንድ ላይ Pronoun/“ፕሮ ናውን” ወይም በብዙ Pronouns/“ፕሮናውንስ” = በስም ፈንታ ወይም ምትክ ማለት ይሆናል።  በግእዝ “ተውላጠ ስም” በአማርኛ “የስም ተለዋጮች” የሚባሉት ሲሆኑ  ስምን ወይም ስሞችን ተክተው የሚገቡ ናቸው። በእንግሊዘኛው “in place of noun” ማለት ነው። ይህም ማለት በስም ምትክ ማለት ነው።(በስም ምትክ የሚገቡ ለማለት ነው)

 

 

የፕሮ ናውንስ ሥራ ምንድነው? (የሚሠጡትን አገልግሎት የሚመለከት)

 

ፕሮናውንስ ሥራቸው በስም ምትክ መግባትና ስም የሚሠራውን መሥራት ነው። (The word that replaces noun in sentence is called “pronoun”) በዐረፍተ ነገር ውስጥ ስምን የሚተካ ቃል ፕሮናውን ይባላል። ስለዚህ ፕሮናውንን ወይም ተውላጠ ስሞችን መቸና እንዴት እንደ ምንጠቀም በሚከተሉት ምሳሌዎች እንመልከት።

 

ምሳሌ፡ በመጀመሪያ በአማርኛ እንዴት እንደምንጠቀምባቸው በትክክል ሊገባን ይገባል፤ ስለዚህ በመጀመሪያ በእንግሊዘኛ ዐረፍተ ነገር ከመሥራታችን በፊት በአማርኛ እናያለን።

·         አበራ ከአልማዝ ጋር ይሠራል

·         አበራ ከአልማዝ ጋር መሥራት ይወዳል

·         አበራ እና አልማዝ አብረው መሥራት ይወዳሉ። በነዚህ ሦስት ዐረፍተ ነገራት ሁለት ስሞች አሉ ስሞቹ 6 ጊዜ ተደጋግመው ተጠቅሰዋል። ስለዚህ የስሞች መደጋገም ደግሞ ንግግርን የማይማርክ  ወይም አሰልች ያደርጋል። በመሆኑም ድግግሞሺን ለማስቀረት “ተውላጠ ስሞችን” መጠቀም አለብን።

 

አበራ ከአልማዝ ጋር ይሠራል፤

እሱ እርሷ ጋር መሥራትን ይወዳል፤

እነሱ አብረው መሥራት ይወዳሉ።


አሁን የፕሮናውንን ወይም የስም ተለዋጮችን ሥራ አስተውሉ፤ አበራ ከአልማዝ ጋር ይሠራል ካልን በኋላ እንደ ገና ተመሳሳይ ስሞችን ከመደጋገም ማለትም “አበራ” በማለት ፈንታ “እሱ” “አልማዝ” በማለት ፈንታ “እርሷ”፣ አበራና አልማዝ በማለት ፈንታ “እነሱ” የሚባሉትን ተውላጠ አስማት ወይም የስም ተለዋጮች በመጠቀም 1ኛ ስማቸውን ከመደጋገምና አስልች ድግግሞሽ ከማድረግ ተቆጠብን፤ ሁለተኛ 4 ቃላትን (አበራና አልማዝን ሁለት ጊዜ) ከመጻፍ “እሱ” “እሷ” “እነሱ” በሚሉት ቃላት በማጠቃለል ወረቀትና ጊዜን መቆጠብ ቻልን ማለት ነው።

 

እነዚህ ሦስት ከላይ የሠራናቸው ዐረፍተ ነገራት በእንግሊዘኛ ደግሞ እንደሚከተለው ይቀመጣሉ።

·         Abera works with Almaz (አበራ ወርክስ ዊዝ አልማዝ)

·         Abera likes working with Almaz(አበራ ላይክስ ወርኪንግ ዊዝ አልማዝ)

·         Abera and Almaz like working together (አበራ ኤንድ አልማዝ ላይክ ወርኪንግ ትጌዘር)

 

አሁንም ከላይ በአማርኛው እንዳየነው በሦስቱም የእንግሊዘኛ ዐረፍተ ነገራት የተደጋገሙ ስሞች አሉ። ስለዚህ ዐረፍተ ነገሩ የማይስብና የሚያሰለች ድግግሞሽ እንዳይሆን “ተውላጠ ስሞችን/ፕሮናውንን እንጠቀማለን” ስለዚህ.

 

·         Abera works with Almaz.

·         He likes working with her.

·         They like working together.

 

በመሆኑም ተውላጠ ስሞችን የምንጠቀመው አንደኛ የስሞች ድግግሞሽን ለመቀነስና ዐረፍተ ነገሩን ማራኪ የማይሰለች ለማድረግ፤ ሁለተኛ ደግሞ ስም መጥራት የማንፈልግ ከሆነ ተውላጠ ስሞችን እንጠቀማለን። ተውላጠ ስሞችን በመጠቀም ወረቀትና ጊዜን መቆጠብ እንደምንችልም አትዘንጉ

 

ፕሮናውንስ ስንት ዓይነት ነው/ናቸው?(አከፋፈላቸውን የሚመለከት)

 

ከላይ ስጀምር እንደነገርኳችሁ pronouns/ፕሮናውንስ የሚባሉት ብዙ ዓይነት ናቸው ለምሳሌ

1.   Personal pronouns/ፐርሰናል ፕሮናውንስ

2.   Relative pronouns/ረለቲብ ፕሮናውንስ

3.   Reflexive pronouns/ረፍለክሲብ ፕሮናውንስ

4.   Interrogative pronouns/ኢንተሮጌቲብ ፕሮናውንስ

ወዘተርፈ ይገኙበታል።

 ለዛሬው የመጀመሪያውን “ፐርሰናል ፕሮናውን” የሚባለውን እንማራለን ማለት ነው።

 

Personal pronouns/ፐርሰናል ፕሮናውን/ ሰብአዊ ወይም አካላዊ የስም ተለዋጮች

ፐርሰናል ፕሮናውን “ፐርሰን” ማለት ሰው ወይም አካል ማለት ሲሆን “ፐርሰናል ፕሮናውን” የሚለው = ሰብአዊ ወይም አካላዊ ተውላጠስም ማለት ነው። ፐርሰናል ፕሮናውኖች ለሰዎች እና ለቤት እንሥሳት የምንጠቀምባቸው ናቸው። በሦስት አበይት ክፍሎች ይከፈላሉ። እነሱም የዐረፍተ ነገር ባለቤቶች፣ ተሳቢዎች፣ እና ባለቤትነትን የሚያመለክቱ ተውላጠ ስሞች ይባላሉ በእንግሊዘኛው እንደሚከተለው ይገለጻሉ።

·         Subjective pronouns/ባለቤት የሚሆኑ ተውላጠ ስሞች

·         Objective pronouns and /ተሳቢ የሚሆኑ ተውላጠ ስሞች እና

·         Possessive pronouns/ ባለቤትነትን የሚያመለክቱ ተውላጠ ስሞች

የሚባሉት ሲሆኑ በሚቀጥለው በክፍል 8 ትምህርታችን እያንዳንዳቸውን በተናጠል በምሳሌ እንመለከታለን።


Words in this video to be learned/ በዚህ ቪድዮ ውስጥ የሚገኙ መጠናት ያለባቸው ቃላት

·         Pronoun = የስም ተለዋጭ

·         Subject = ባለበት/የዐረፍተ ነገር ባለቤት

·         Object = ተሳቢ ወይም ተደራጊ

·         Possessive = አመልካች(ባለቤትነትን፤ባለንብረትነትን የሚያመለክት)

·         Person = ሰው/አካላዊ ሰው

·         Relative = ተዛማጅ/ዘመድ

·         Reflexive = መልሶ የሚያንጸባርቅ/ወደራሱ የሚያመለክት

·         Interrogative = መጠየቂያ/መመርመሪያ

·         To like = መውደድ

·         To work = መሥራት(ግስ)

·         Working =መሥራት(ስም ከ አር፣ ወይም ኢዝ ከሚባሉት ግሶች ጋር ግስ የሚሆንበትም ጊዜ አለ)

·         With = ጋር ወይም ጋራ/አብሮ..

·         He = እሱ

·         She = እሷ

·         Her = እሷን/የሷ..

·         They = እነሱ

ልዑል አምላክ ማስተዋሉን ያድለን

ከአውደ ጥናት ዘእንግሊዘኛ

No comments:

Post a Comment