Wednesday, February 24, 2021

How to study effectively? Basic studding rules/ማነኛውንም ነገር እንዴት ማጥናት አንችላ...


መሠረታዊ የአጠናን ጥበብ፥ በዚህ ዓይነት መንገድ ካጠናችሁ በእውነትም ስኬት ታገኛላችሁ

ሰላም ጤና ይስጥልኝ ከአውደ ጥናት ነው።

 ዛሬ ለየት ያለ ዝግጅት ነው ያለኝ፤ እንደምታውቁት አውደ ጥናት የእምነት ወይም የአማርኛ እና የግእዝ ትምህርቶችን ብቻ ሳይሆን በማኅበራዊ ሕይወታችን በሥጋዊ ጉዟችን ሁሉ የሚጠቅሙን ልዩ ልዩ ትምህርቶች የሚሰጡበት ቻናል ወይም ድረ ገጽ ነው።

በመሆኑም የሥነ ምግባር፤ የቋንቋ፤ የትምህርት ሌሎችንም ትምህርቶች ከምሁራን በመጠየቅ ከመጻሕፍት በማንበብ በጥናት ላይ የተመረኮዙ አርእስትን እያዘጋጀሁ ወደ እናንተ አደርሳለሁ ማለት ነው። የእኔ ዕቅድ በተቻለ መጠን ሰዎች ወደ አውደ ጥናት መጥተው በሥጋዊውም ሆነ በመንፈሳዊ ሕይወታቸው የሚፈልጉትን ሁሉ ማግኘት እንዲችሉ ለማድረግ ነው፤ ለዚህም ነው የተለያዩ ሊቃውንትን በተለያዩ አርእስት ቃለ መጠይቅ እያደረግሁ ሳቀርብ የምትመለከቱት።

የበለጠ ለመሥራት ግን የሁላችሁም ተሳትፎ ወሳኝ በመሆኑ አውደ ጥናትን በተለያየ መንገድ በምትችሉት ሁሉ መደገፍና ተሳትፎም ማድረግ ትችላላችሁ።

 መጻሕፍት ለመግዛት የሚከተሉትን የመጻሕፍቱን ሥዕሎች ይጫኑ ወይም በ+1 703 254 6601 በመደወል ያነጋግሩኝ በአድራሻዎ ይላክለዎታል፤ I am directing you to amazon market place. buy my books on amazon.

 

የአጠናን ጥበብ

መሠረታዊ የአጠናን ጥበብን በአጭሩ ነው የምንመለከተው፤

በቀላሉ በሚከተሉት ስድስት አርእስት ልንከፍለው እንችላለን

1.  ለጥናት የሚያነሣሳ ኃይል ወይም ምክንያት መኖር (ለምን አጠናለሁ?)
2.  የአጠናኑን መንገድ መቀየስ (ጊዜና ቦታ)
3.  የጥናት ልክ (የጊዜ ውሱንነት)
4.  ቅኝት(መቃኘት)
5.  ጥናት
6.  ክለሳ

በነዚህ ከዚህ በላይ በተጠቀሱት ነጥቦች መሠረት በአጭሩ እንነጋገራለን።

የጥናት ምክንያት (ለማጥናት የሚያነሣሳ ኃይል ወይም ምክንያት (ለምን አጠናለሁ)

·        ራሴን ለማሻሻል

·        ገንዘብ ለማግኘት

·        ዝናን ለማግኘት

·        ለዕድገት ወዘተ

ለምን እንደምናጠና በቂ ምክንያት ካገኘን በኋላ ደግሞ እንዴት እና በየት ማጥናት እንዳለብን ማቀድ ይኖርብናል። ማቀድ ግዴታ ይኖርብና “ለመሥራት የማያቅድ ሰው ላለመሥራት ያቀደ ነው” ይባላል። ምክንያቱም ያለ እቅድ መሥራት የትም ሊያደርሰን አይችልም ልክ የት መሄድ እንደሚፈልግ ሳያውቅ መኪናውን አሥነሥቶ በትልቅ ጎዳና ላይ የሚያሽከረክር ሰውን ይመስላል።

እንዴት አጠናለሁ? (የጊዜ አጠቃቀምና የቦታ ምርጫ፤ መቼና ምን ያህል ደቂቃ ወይም ሰዓት)

በክፍል ውስጥ ወይም በሌላ መንገድ የምንማርበትን ጊዜ ወይም ሌሎች የግልም ሆኑ የጋራ ጉዳዮችን የምናከናውንበትን ጊዜ የማይሻማ ለጥናት የተለየ ጊዜን መምረጥ ነው።

·        ማታ፡ ከትምህርት ወይም ከሥራ መልስ

·        ጠዋት፡ ከትምህርት ወይም ከሥራ በኋላ

·        ቀን፡ በረፍት ሰዓት ወይም ሥራ ስንጨርስ

·        ሌሊት፡ ከእንቅልፋችን ቀንሰን ወዘተ(የሚስማማንን ጊዜ መፍጠር)

ለምን ያህል ጊዜ ማጥናት እንችላለን(ያለን ጊዜ ምን ያህል ነው?)

·        30 ደቂቃ፤ 1 ሰዓት፣ 2 ሰዓት ወዘተ

የምናጠናውስ በየት ነው? (ጸጥታ ያለው፣ ሊረብሸንና ሐሣባችንን ሊበትን የሚችል ድምጽና ዕይታ የሌለው ሠወር እና ጸጥ ያለ ቦታ ወይም ክፍል ማግኘት ይጠበቅብናል።

አሁን ለምን እንደምናጠና፤ በየት እንደምናጠና፣ ለምን ያህል ጊዜ እንደምናጠና አውቀናል ተዘጋጅተናል ማለት ነው፤ በሌላ አባባል የተሟላ እቅድ አውጥተናል።

ትልቁ ፈተና የአላማ ጽናት ነው፤ ማለትም ላወጣነው እቅድ ወይም መርሐግብር ተገዥ ለመሆን ቃል መግባት ይጠበቅብናል።

 ካልሆነ ግን እቅዳችን ግብ ሳይመታ ሊቀር ይችላል። ይህ ታላቁ ሥራ ነው፤ (የሚያቅደው ሰው ብዙ ነው ነገር ግን እቅዱን በሥራ ላይ የሚያውለው ግን በጣም አናሣ ቍጥር ያለው ነው) ባለሙያዎች ዕቅድ ከሚያወጣው ሕዝብ መካከል ለእቅዱ ተገዥ በመሆን ለስኬት የሚበቃው ከመቶ 8 ሲሆን አቅዶ ሳይሳካለት የሚቀረው ከመቶ 92% ነው ይላሉ። ስለዚህ እኛ ከ8ቱ ውስጥ ራሻችንን ለመመደብ መጣር አለብን።

በዕቅድ መመራትና በዕቅዳችን መጽናት የሚጠቅመን በሁሉም የሕይወት አቅጣጫ ነው፤ ለሥጋም፤ ለነፍስም፤ ለጤናም፤ ለብልጽግናም፤ ለደስታም፤ ባጭሩ ለሁሉም። ስለዚህ በእቅዳችን መጽናትና ላወጣነው መመሪያ ወይም መርሐግብር ተገዥዎች መሆን አለብን።

የአጠናን ዘዴ (እንዴት እንጀምር)

አሁን እቅዳችንን ጨርሰን መርሐግብር አውጥተን፤ ማስታዎሻ የምንይዝበት ደብተርና ስክብሪቶ ይዘን በመረጥነው ጊዜ፣ በወሰነው ቦታ፣ ተሰይመናል ወይም ተቀምጠናል፤ የምናጠናው መጽሐፍ በእጃችን ገብቷል፤ አሁን መቃኘት ወደሚለው ክፍል ልናልፍ ነው።

መቃኘት

መጽሐፉን ወይም የሚጠናውን ነገር በእጃችን ይዘን እናየዋለን፣ እናስተውለዋለን፤ ምንድነው የምናየውና የምናስተውለው

  • ·        ርእሱ ምን ይላል?
  • ·        ቅርጹ ምን ይመስላል?
  • ·        ቀለሙ ምን ዓይነት ነው?
  • ·        በሽፋኑ ላይ ምን ያህል ሥዕሎች አሉ? ምን ዓይነትስ ናቸው?
  • ·        ምንያህል ገጽ ነው? ወዘተ…

ከዚህ በላይ የተዘረዘሩት እያንዳንዳቸው የራሳቸው የሆነ መልእክትን የሚያስተላልፉ ናቸው። መልእክታቸውም በመጽሐፉ ውስጥ ያለውን መሠረታዊ ሐሣብ የሚገልጡ፤ የትምህርቱን ይዘት፣ ስፋት እና ጥበት የሚናገሩ ናቸው።

እነዚህን ሁሉ ካየን በኋላ ራሳችንን ለሰከንዶች(ለደቂቃዎች) መጠየቅ አለብን፤ ማለትም መገመት (ይህ ርእስና በሽፋኑ ያሉት ጽሁፎችና ሥዕሎች ምንን ሊወክሉ ይችላሉ ወዘተ እያሉ መመራመር) ይኖርብናል።

 

አሁን ወደ መጽሐፉ ገብተን ማጥናት ልንጀምር ነው፤ መጀመሪያ የምናገኛቸው የአርእስት ማውጫ፤ መግቢያ፤ እና መግለጫ የሚባሉት የመጽሐፉን ምዕራፍ አንድን ከመጀመራችን በፊት የምናያቸው ዋና ዋናዎቹ ክፍሎች ናቸው።

ሦስቱንም መመልከት ይኖርብናል፤ የአርእስት ማውጫ፣ በያንዳንዱ ምዕራፍ ወይም ክፍል የሚገኙትን ንዑሳን አርእስት የሚያስተዋውቀን፤ የምግብ ሜኑ ማለት ነው፤ የአርእስት ማውጫውን ማየት ጠቅላላ የመጽሐፉን ሐሳብና ይዘት ለማወቅ ብቻ ሳይሆን፤ የምንቸኩልና ከመጽሐፉ ውስጥ የተወሰነ ነገር ብቻ ማጥናት የምንፈልግ ከሆነ የምንፈልገውን በቶሎ አውጥተን ለመመልከት ወይም ለማጥናት ይረዳናል።

መግቢያን መግለጫ

መግቢያ እና መግለጫ ማንበብ ስለ መጽሐፉ ይዘትና አጠቃቀም ግልጽ የሆነ ግንባቤን ይሰጣል፤ ምክንያቱም ከስያሜያቸው እንደምንረዳው “መግቢያ” ማለት የመጽሐፉን ይዘት ወይም መልእክት ለመመርመር ከመጀመራችን በፊት በሩን የሚከፍትልንና አጠቃላይ ማብራርያ የሚሰጠን ክፍል ነው። መግቢያ ሳያነብ ዋናውን ምዕራፍ ወይም ክፍል የሚጀምር ሰው፣ በሩን በመክፈቻ ከፍቶ ሳይሆን መክፈቻውን ሰብሮ የገባን ወይም አንድን የሚፈልገውን ነገር ለማግኘት የሚገኝበት በየት እንደሆነ ሳያውቅ በየቦታው እየገባ የሚፈልግን ሰው ይመስላል።

መግለጫው ደግሞ ከስሙ እንደምንረዳው ስለመጽሐፉ አከፋፈልና አጠቃቀም የሚነግረን ክፍል ነው። (መጽሐፉ ስንት ምዕራፎችና ክፍሎች እንዳሉት የትኛው ትምህርት በየትኛው ምዕራፍ ወይም ክፍል እንደሚገኝ ወዘተ) የሚነግረን ክፍል ነው።

በመቀጠልም በየምዕራፉ መጨረሻ የሚገኙ ማጠቃለያዎችንና ጥያቄዎችን ቀድመን መመልከትና ሐሳባዊ መልስ ለመስጠት መሞከር

ዋናውን ጥናታችንን ስንጀምር

  • ለምን?
  • እንዴት?
  • መቼ?
  • በየት?

ማን? ወዘተ በሚሉት ወሳኝ ጥያቄዎች መሠረት ራሳችንን እየጠየቅን መልሱን እያገኘን ማጥናት መቻል አለብን።

የምናነበውን ወይም የምናጠናውን ሐሣብ ወይም ትምርት ቃልም ሊሆን ይችላል በአእምሯችን እንዲቀረጽ ከምናውቀው ነገር ጋር በማያያዝ ወይም በማዛመድ የማይረሳ ማድረግ መቻል።

ለምሳሌ፡

እንግሊዘኛ የምናጠና ከሆነ እና ቃላትን እንዲሁ ያለምንም ዘዴ ለመሸምደድ ከመሞከር ይልቅ ከአማርኛ ከግእዝ ከሌሎችንም ከምናውቃቸው ቋንቋዎች ጋር በማዛመድ ለማስታዎስ መጣር፤

“ማይ” ማለት በእንግሊዘኛ “የእኔ” ማለት ነው፤ መግእዝ “ማይ” ማለት “ውሀ” ማለት ነው፡(ትግርኛና ግእዝ የሚያውቅ ተማሪ “ማይ” የሚለውን የእንግሊዘኛ ቃል በቀላሉ በአእምሮው ቀረጸው ማለት ነው።

“ጉድ” ማለት በአማርኛ አስደንጋጭ ቃል ነው፤ በእንግሊዘኛ ግን “መልካም” ማለት ነው፤ ስለዚህ እነዚህን ቃላት በማዛመድ የማይረሱ ማድረግ እንችላለን፤ ከዚህም ሌላ ብዙ ነገሮችን ማግኘት እንችላለን፤ ግዴታ ቀጥታና ግልጽ ተመሳሳይነት ባይኖራቸውም ብዙ ልዩ ልዩ ዘዴዎችን በመፍጠር ከባሕላችን ከታሪካችን ወዘተ ጋር በተዘዋዋሪ ማዛመድ እንችላለን፤ (በሌላ ርእስ በበለጠ ልንመለከተው እንችላለን)

 

የመጨረሻው መከለስ(መደጋገም) ልምምድ ማድረግ ወዘተ የሚለው ክፍል ነው። “መደጋገም የማወቅ እናት ናት” ይባላል። አንድን ነገር መልሰን መልሰን መላልሰን ከሠራነው አንዱ የሕይወታችን ክፍል ስለሚሆን ልክ እንጀራ ለመጉረስ አፋችን ያለበትን መፈለግ እንደማንሻና በብራትም ሆነ አመልካች እንደማያስፈልገን ሁሉ የለመድነው ሥራም ዐይናችንን ጨፍነን እንኳን መሥራት የምንችለው ይሆናል።

ይቆየን


No comments:

Post a Comment