Tuesday, May 26, 2020

የእንግሊዘኛ ታሪክ



ልሣነ ግእዝ የጋራ ቋንቋችን የሚለውን መጽሐፍ ለመግዛት ከዚህ በታች ያለውን ራሱ መጽሐፉን ይጫኑ



ሰላም ጤና ይስጥልኝ፡ ከአውደ ጥናት ነው።


ዛሬ አዲስና ለየት ያለ ዜናን ይዠላችሁ ቀርቤያለሁ፤ ይህ ዜና ለብዙዎቻችሁ በተለይም አውደ ጥናትን ለምታውቁና የአውደ ጥናትን የትምህርት አሰጣጥ ዘዴ ለተገነዘባችሁ ሁሉ መልካምና አስደሳች ዜና ነው ብየ አምናለሁ ።

ይኸውም አውደ ጥናት የእንግሊዘኛ ቋንቋን ለጀማሪዎች ለማስተማር መወሰኗን የሚያበሥር  ዜና ነው። እንደሚታወቀው የእንግሊዘኛ ቋንቋ የውዴታ ትምህርት ሳይሆን የግዴታ ትምህርት ነው። ምክንያቱም የዓለማችን ሁሉ አንደበትና የዕድገት መሣሪያ በመሆኑ በተለይ ለሥጋዊው ሕይወት መሳካት አማራጭ የሌለው ምርጫ ነው። ስለዚህ ቢያንስ የውዴታ ግዴታ ነው ማለት ነው።

አውደ ጥናትም ይህንን የእንግሊዘኛን ቋንቋ ተፈላጊነት ግምት ውስጥ በማስገባት ጥቅሙን ተረድተው ይልቁንም በቋንቋቸው እንግሊዘኛን መማር የሚፈልጉትን ለመርዳት የግእዝን ቋንቋ በምታስተምርበት ዘዴ ቀላልና ግልጽ በሆነው የማስተማር ንድፋ እቅድ አውጥታ ለማስተማር በበጎ ፈቃድ መነሣቷን በደስታ አበሥራችኋለሁ። ስለዚህ ከአሁኑ አውደ ጥናትን ሰብስክራይብ በማድረግ ትምህርቱ ሲጀመር ለመከታተል ተዘጋጅታችሁ መጠበቅ ይኖርባችኋል። ከዚህ ቀጥየ ስለ እንግሊዘኛ ቋንቋ ታሪካዊ አመጣጥ አጭር ማብራርያን እሰጣችኋለሁ እንከታተል።

መጽሐፍ ቅዱስ እና የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን “የጥበብ መጀመሪያው እግዚአብሔርን መፍራት ነው” ይላሉ፤ ይህም የማይታበል ሐቅ ነው። በአንጻሩም የትምህርትና የሥነ ጽሁፍ ምሁራን ደግሞ በበኩላቸው “የትምህርት መጀመሪያው ስለሚማሩት ትምህርት ስያሜና ይዘት፤ ታሪክና ጥቅም ጠንቅቆ ማወቅ ነው” ይላሉ። ይህም አባባል በበኩሉ ተግባራዊ እውነት አለው።

እኛም ይህንኑ አባባል መሠረት በማድረግ ለመጀመር ስላሰብነው የእንግሊዘኛ ቋንቋ በመጠኑም ቢሆን እንደ መግቢያ ይሆነን ዘድን “እንግሊዘኛ” ምን ማለት ነው? የማን ቋንቋ ነው? እንዴትስ አሁን ከደረሰበት ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደረስ? ለምንስ የግዴታ ትምህርት ወይም የውዴታ ግዴታ ሊሆን ቻለ? ወዘተርፈ የሚሉትን ነጥቦች በመዳሰስ እንነጋገራለን፤ እንከታተል መልካም ቆይታ።

የእንግሊዘኛ ቋንቋ ስያሜና ምድብ
አብዛኛዎቻችን እንደምናውቀው እንግሊዘኛ የኢንግላንድ ቋንቋ ነው፤ “ኢንግላንድ” ደግሞ የታላቋ ብሪታንያ ሌላው ስሟ ነው፤ “ኢንግላንድ” የሚለው የቃሉ ትርጉም ግን  “ኤንግልስ” እና “ላንድ” ከተባሉ ሁለት የተለያዩ ቃላት የተመሠረተ ሲሆን “ኤንግለስ” የአንድ ጥንታዊ ሰው መጠሪያ ስም ።  “ላንድ” የሚለው ሁለተኛው ቃል ደግሞ በእንግሊዘኛ ቋንቋ “መሬት ወይም ቦታ ማለት ነው። ስለዚህ “ኢንግላንድ” ማለት የኤንግለስ ቦታ ወይም አገር ማለት ነው። ይህም በእንግሊዘኛው (The Land of Angles) እንደ ማለት ሲሆን የኤንግለስ መሬት ወይም አገር ተብሎ ይተረጎማል።

ኤንግልስ ማነው?
ኤንግለስ ለመጀመሪያ ጊዜ ከአውሮፓ ወይም ከምዕራባዊው ጀርመን ተነሥተው አሁን ኢንግላንድ ወደ ሚባለው ቦታ መጥተው አካባቢውን በመያዝ ነዋሪዎቹን አስለቅቀው አገሩን ከተቆጣጠሩት ኤንግልስ፣ ሳክስንስ፣ እና ጁለስ ከተባሉት ሦስት ሰዎች(Angles, Saxson, and Jules) መካከል አንዱ ነው። ስለዚህ ኢንግላንድ የሚለው ስያሜ የተወሰደው ከዚሁ ኤንግልስ ከተባለው አውሮፓዊ ወይም ጀርመናዊ ሰው ስም በመነሣት ነው። በመሆኑም የእርሱ አገርና ቋንቋ መሆኑን ለመግለጽ በስሙ አገሩን ኢንግላንድ፤ ቋንቋውን ደግሞ “ኢንግሊዥ” ብለውታል።

እንግሊዘኛ የኢንዶ ኤብሮፒያን ቋንቋዎች ቤተሰብ ከሚባሉት ውስጥ አንዱ ቋንቋ ሲሆን ምንጩ የምዕራባዊ ጀርመን ቋንቋ እንደነበር ይነገራል። ይህ የቋንቋ ቤተ ሰብ የአውሮፓን፤ የሕንድን፣ እና የኢራንን ቋንቋዎች የሚያቅፍ የቋንቋ ቤተሰብ ነው። ይህ ኢንዶ-ኤብሮፒያን ቤተሰብ የሚባለው የቋንቋ ስብስብ በዓለም ላይ “አፍሮ-አስያቲክ” ከሚባለው የቋንቋዎች ቤተሰብ ቀጥሎ ሁለተኛውን ደረጃ ይዞ ይገኛል። አፍሮ-አስያቲክ የሚባለው የቋንቋ ቤተሰብ ግን ከዓለም አንደኛው ሲሆን የሰመቲክ ወይም የእኛ ቋንቋዎች ሁሉ የሚጠቃለሉት በአፍሮ-አስያቲክ ቤተሰብ ቋንቋዎች ሥር ነው።

እንግሊዘኛ ከ6ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ወደ ሦስት ሺህ ለሚጠጉ ዓመታት ራሱን እያሻሻለ እያደገ አሁን ከደረሰበት አለም አቀፍ ቋንቋነት ደርሷል።
 እንግሊዘኛ ከሌሎች ቋንቋዎች ጋር ሲነጻጸር በዕድሜ በጣም ጥንታዊ ባይሆንም ከ 1 ሚሊየን በላይ ቃላት ያሉትና ከልዩ ልዩ ጥንታውያን ቋንቋዎች የተወሰዱ ብዙ ቃላትንም ሰብስቦ የያዘ ቋንቋ ነው። በነዚህ ልዩ ልዩ ጉዞዎቹም ከእድገቱ ጋር አብረው የተጓዙ ልዩ ልዩ ስያሜዎችም ነበሩት ለምሳሌ፤ ጀርመኒክ ላንጉች(የጀርመን ቋንቋ)፤ አንግሎ-ሳክሰንስ ኢንግሊዥ ወይም የአንግሎ ሳክሰን እንግሊዘኛ፤  ሸክስፒሪያን ኢንግልዥ፤ ወይም የሸክስፒር እንግሊዘኛ እየተባለ ይጠራ ነበር።

በአሁኑ ጊዜ እንግሊዘኛ በዓለማችን አንደኛና ብቸኛው አለም አቀፍ መግባቢያ ነው። የአለም አቀፍ ድርጅቶችና የዓለም አቀፍ ግንኙነት፤ የሥራ ቋንቅው ነው፤ የኮምፕዩተር፤ የኢንተርኔት የሌሎችም ቁልፍ የሆኑ ሥልጣኔ ወለድ ሥራዎችና መሣሪያዎች ቋንቋ ነው።

ለምሳሌ፡
·        የተባበሩት መንግሥታት ወይም (United Nations)
·        የአውሮፓ ሕብረት ወይም (Europian Union)
·        የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን ድርጅት ወይም (NATO)
·        የዓለም የጠና ድርጅት ወይም (WHO) የሥራ ቋንቋ ነው።
የዓለም አቀፍ ግንኙነት ባለሙያዎች እንግሊዘኛን አለመማር እንደማይቻል ሲናገሩ

ምክንያቱም ይላሉ
·        የአለማችን መግባብያ አንደበት ነው
·        ከ380 ሚሊየን በላይ ለሚሆኑ ሰዎች የአፍ መፍቻ ቋንቋ ነው
·        ከ300 ሚሊየን በላይ ለሚሆነው ሕዝብ 2ኛ ቋንቋ ነው
·        ከ28 በላይ ለሚሆኑ አገሮች ብሔራዊ ቋንቋቸው ነው
·        በዓለም አቀፍ ደረጃ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መማሪያ ቋንቋ ነው
·        ከ1.5 ቢሊየን በላይ የሚሆነው የአለም ሕዝብ በአሁኑ ጊዜ እየተማረው ይገኛል
·        ታላላቅና ቁልፍ ለሆኑ አለም አቀፍ ድርጅቶች የሥራ ቋንቋ ነው
·         የኮምፕዩተር፤ የኢንተርኔት፤ የሌሎችም ልዩ ልዩ ቴክኖሎጅ-ነክ ለሆኑ የሥራ መስኮች ብቸኛው ቋንቋ ነው
·         በዓለም ላይ 96% ወይም ዘጠና ስድስት ከመቶ የሚሆነው የምርምር ሥነ ጽሁፍ የተጻፈው በእንግሊዘኛ ነው
·          ከ50 ዓመታት በኋላ በዓለማችን ከግማሽ በላይ የሚሆነው ሕዝብ የእንግሊዘኛ ተጠቃሚ እንደሚሆን ይተነበያል። ይላሉ

ታዲያ ከዚህ በላይ ባየናቸው አጭር የእንግሊዘኛ ዓለም አቀፍ ድርሻዎች መሠረት እንግሊዘኛን አለመማር ጉዳት አለው? ወይስ የለውም? መልሱን ከናንተ።


ልዑል አምላክ ማስተዋሉን ያድለን
መልካም ትምህርት
ከአውደ ጥናት



ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ይተዋወቁ የሚለውን መጽሐፍ ለመግዛት ከዚህ በታች ያለውን ራሱ መጽሐፉን ይጫኑ

No comments:

Post a Comment