Friday, July 24, 2015

ግእዝ ጽሁፍ ክፍል 28 ዘንድ አንቀጽ

Ge'ez Lessons for Beginners part 28 text (ዘንድ አንቀጽ = in order to)


መሀረ = አስተማረ (ያለፈ ድርጊት) past
ይምህር= ያስተምራል (ወደፊት የሚደረግ ትንቢት) futur
ይምሀር= ያስተምር ዘንድ (ምክንያታዊ ) in order to


እርማት፡ መሀረ = አስተማረይሜህር 
ይምሀር
ይምሀር
መሐረ = ይቅር አለ የሚለው ግስ ሲሆን ነው ይምህር በማለት የሚረባው። መሀረ = አስተማረ የሚለው ግን መሀረ (ሐላፊ) ይሜህር (ትንቢት) ማለትም በትንቢት (በሁለተኛው ግስ) የሚገኘው ሆሄ "ም" ሳይሆኝ "ሜ" (ይሜህር) ይሆናል።



ተንሥአ ይምሀር መምህረ ግእዝ =የግእዝ መምህር ያስተምር ዘንድ ተነሣ
ዘንድ አንቀጽ = In order to
ባለፉት ተከታታይ ክፍሎች በክፍል 25 ስለ አራቱ አበይት አናቅጽ ስለ
1.      ሃላፊ፤
2.     ትንቢት፤
3.     ዘንድ  እና
4.     ትዕዛዝ (ዘንድ እና ትዕዛዝ ሳልሳይ ወይም 3ኛ ይባላሉ) ጠቅለል ባለ መልኩ ተምረን ነበር።
በድጋሚ ለማስታዎስ ያህል ግሦቹ የሚከተሉት ናቸው።
ሖረ=  ሄደ  ሃላፊ አንቀጽ
ይሐውር= ይሄዳል  ትንቢት አንቀጽ
ይሑር= ይሄድ ዘንድ  ዘንድ አንቀጽ
ይሑር= ይሂድ  ትእዛዝ አንቀጽ
በመሆኑም እነዚህን ግሦች መሠረት አድርገን እንደ መግቢያ ከተማርን በኋላ በመቀጠልም አንድ በአንድ  በክፍል 26 ስለ ሃላፊ ግሥ ወይ አንቀጽ፤ በክፍል 27 ስለ ትንቢት ግሥ ወይም አናቅጽ ተምረናል።
በዛሬው በክፍል 28 ትምህርታችን ደግሞ
ስለ ዘንድ አንቀጽ እንማራለን። ዘንድ አንቀጽ ሳልሳይ ተብሎም ይጠራል ።ሦስተኛ ማለት ነው። ምክንያቱም በሦስተኛ ተራቁጥር ስለሚገኝ ነው። ዘንድ አንቀጽ የሚባለውም ዘንድ ተብሎ ስለሚተረጎም ነው። (ይሄድ ዘንድ)
ዘንድ አንቀጽ ከአበይት ግሦች ሦስተኛው አንቀጽ ሲሆን በቀጥታ ማሠሪያ አንቀጽ አይሆንም ማለትም አያሥርም። (ውእቱን መርምሮ ካልሆነ በስተቀር)፤
 ስለዚህ ሌላ ተጨማሪ አንቀጽን ይፈልጋል። ውእቱ (ገብረ ሥላሴ) ተንሥአ ይሁር = እሱ ይሄድ ዘንድ ተነሣ፤ ብንል የዚህ ዐረፍተ ነገር ማሠርያ የሆነው “ተንሥአ” የሚለው ግሥ ሲሆን ይሁር የሚለው ምክንያቱን ይገልጻል እንጂ አያሥርም። ስለዚህ በዚህ ዐረፍተ ነገር ሁለት አበይት ግሦች ሲኖሩ አንዱ ብቻ ማሠሪያ ሆነ። ለዚህም ነው ዘንድ አንቀጽ በቀጥታ ስለማያሥር ሌላ ሁለተኛ አንቀጽን ይሻል ያልነው።
ዘንድ አንቀጽ አገባባዊ ባሕርይ አለው፤ (ከመ ከሚለው አገባብ ጋር ተመሳሳይ ትርጉም እና ሥራ አለው። ሁለቱ ማለትም ከመ እና ዘንድ አንቀጽ በአንድ ላይ ይነገራሉ። ይህ በሚሆንበት ጊዜ ዘንድ አንቀጹ የተለመደውን ትርጉሙን ሲይዝ “ከመ” የሚለው አገባብ የዘንድ አንቀጹ ሞገሥ ወይም አጃቢ ይባላል።
ለምሳሌ
መርድእ ሖረ ከመ ይትመሀር ልሣነ ግእዝ = ተማሪ የግእዝን ቋንቋ ይማር ዘንድ ሄደ። በዚህ ዐ/ነገር ላይ ከመ የይትመሀር አዳማቂ ሆነ እንጂ ሌላ አገልግሎት አልሰጠም። ምክንያቱም “ይትምሀር” የሚለው ግሥ ራሱ ትርጉሙ “ይማር ዘንድ” የሚል ነው። ልዩነታቸው ዘንድ አንቀጽ  አንቀጽም ነው እንደ አገባብም ይተረጎማል፤ “ከመ” ግን “እንደ” የሚል ትርጉም ነው ያለው። ስሙም አገባብ ይባላል። ለሁለቱም ማለትም ለዘንድ አንቀጽና “ከመ” ለሚለው አገባብ ምሳሌዎቹን ተመልከቱ
መነኮስ ቆመ ከመ ይጼሊ= መነኩሴ ይጸልይ ዘንድ ቆመ።
መነኮስ ቆመ ይጸሊ = መነኩሴ ይጸልይ ዘንድ ቆመ።
 በነዚህ በሁለቱ ዐረፍተ ነገራት መሠረት ዘንድ አንቀጽና “ከመ” የሚለው አገባብ ተመሳሳይ አገልግሎት አላቸው። ነገር ግን “ከመ” ከአንቀጽ ጋር በመሆን አንቀጹ እንዳያሥር ለመከላከል ነው የሚያገለግለው፤ ዘንድ አንቀጽ ግን   ብቻውን በመሆን ነው የሚነገረው የራሱ የሆነ አገባባዊ ባሕርይ አለው ማለት ነው።
ዘንድ አንቀጽ ከሁሉም ግሦች (ከሐላፊ፤ከትንቢት፤ እና ከትእዛዝ አናቅጽ ) ጋር አብሮ ይሠራል።
ምሳሌ፡
·         ይብላእ ሆረ = ይበላ ዘንድ ሄደ (ሃላፊ)
·         የሐውር ይብላእ= ይበላ ዘንድ ይሄዳል (ትንቢት)
·         ይሁር ይብላእ= ይበላ ዘንድ ይህድ(ትእዛዝ)
ዘንድ አንቀጽ በዓረፍተ ነገር ሲገባ ለሌላ ድርጊት ወይም አንቀጽ እንደ ምክንያት በመሆን ይገባል።
ለምሳሌ “ መርድእ ሖረ ይትምሀር” ቢል የዓረፍተ ነገሩን ባለቤት የጎዞ ምክንያት ይገልጽለታል። ማለትም ተማሪው የሄደበት ምክንያት “ይማር ዘንድ” ወይም ለመማር ነው። በማለት ምክንያቱን ገለጸለት ማለት ነው።
ከግሡ መጀመሪያ ላይ ባእድ ሆሄን ይጨምራል ሆሄያቱም “አሥራው” ይባላሉ
ምሳሌ
መሀረ መሠረታዊ ግሥ ሲሆን
ይትመሀር “ይ እና ት’ ባእድ ሆሄ ይባላሉ ። ምክንያቱም ከመሠረታዊው ግሥ ያልነበሩ የመሠረታዊው ግሥ ወገን ስላልሆኑ ነው። ከግሡ መጀመሪያ ላይ ስለሚገኙ ደግሞ “አሥራው” ይባላሉ በአማርኛ ሥሮች ማለት ነው፤፡
ስለዚህ ለማጠቃለል ያህል የዘንድ አንቀጽ መሠረታዊ ወይም አበይት መለያዎችን  ባጭሩ እንደሚከተለው ይመልከቱ።
·         ዘንድ አንቀጽ ከአበይ አናቅጽ መካከል ሦስተኛው አንቀጽ ነው በዚህም ሳልሳይ “ሦስተኛ” ይባላል
·         ዘንድ ተብሎ ስለሚተረጎም “ዘንድ አንቀጽ” እየተባለ ይጠራል። ስለዚህ ስሙ ከትርጉም ጋር የተያያዘ ነው።
·         ብቻውን ስለማያሥር ሌላ ግሥ (ሃላፊ፤ ትንቢት፤ ወይም ትእዛዝ “ አናቅጽ) ያስፈልገዋል።
·         ከሁሉም አበይ አናቅጽ ማለትም ከሃላፊ፤ከትንቢት፤ እና ከትእዛዝ አናቅጽ ጋር እየተቀናጀ ያገለግላል
·         አገባባዊ ትርጉምና ሥራ አለው። ለምሳሌ “ከመ” ከሚለው አገባብና ከመሰሎቹ ጋር በትርጉምና በአገልግሎት ይመሳሰላል
·         ሁለት ነገሮችን በአንድ ላይ ይዟል፡ ዘንድ የሚል አገባብ(ከ) እና አንቀጽ “ያእምር”= ያውቅ ዘንድ= ያውቅ(አንቀጽ) ዘንድ=አገብባብ(ከ) ስለዚህ አገባብና አንቀጽ በአንድ ላይ ይበኙበታል።
·         የዐረፍተ ነገርን ምክንያታዊ ተግባር ይገልጻል
·         ከግሡ መጀመሪያ ላይ “አሥራው የሚባሉትን ሆሄያት ይጨምራል።

Sunday, June 28, 2015

ግእዝ ክፍል 27 ትንቢት አንቀጽ

 ክፍል 27 ትንቢታዊ አንቀጽ/ ካልዓይ 


ባለፉት ሁለት ተከታታይ ክፍሎች ማለትም በክፍል 25 ስለ አበይት አናቅጽ፤ማለትም ስለ ሐላፊ ወይም ቀዳማይ፤ ትንቢት ወይም ካልአይ፤ እንዲሁም ዘንድ እና ትእዛዝ ወይም ሳልሳይ፤ ስለሚሉት ግሦች ጠቅለል ባለመልኩ ተምረናል። በክፍል 26 ደግሞ ከነዚሁ 4 አናቅጽ መካከል አንዱ ስለሆነው ስለ ሐላፊ ግሥ ተምረናል። ዛሬ ደግሞ ስለ ትንቢት ወይም ካልአይ አንቀጽ እንማራለን።

ትንቢት ወይም ካልአይ  ተብሎም ይጠራል። ካልአይ ሁለተኛ ማለት ነው
በግእዝ ቋንቋ የመጀመሪያው ግሥ ሐላፊ ነው፤ ማለትም ማነኛውም የግእዝ ግሥ ተጽፎ የሚገኘው በሐላፊ ጊዜ ነው። ቀጥሉ ሁለተኛው ትንቢት ወይም ካልአይ ይባላል። (ስናረባው ማለት ነው) ስለዚህ ዛሬ ከግሥ ርባታ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ስለሚገኘው ስለ ትንቢት አንቀጽ እንማራለን ማለት ነው። ለምሳሌ

ግሡ “ወሀበ” ቢሆን ይህ ግሥ “ሐላፊ” ይባላል። ምክንያቱም ትርጉሙ ሰጠ ማለት ነው። ሰጠ  ማለት ደግሞ ያለፈ ድርጊትን ነው የሚነግረን። የዚህ ግሥ ሁለተኛው ወይም ትንቲታዊው “ይሁብ” ይሆናል። ይሁብ ማለት ደግሞ ይሰጣል ማለት ነው። ይሰጣል ስንል ያለፈ ድርጊት ሳይሆን ወደፊት የሚደረግ ነው። ስለዚህ ትንቢት አንቀጽ የሚባለው ለዚህ ነው።
የትንቢት አንቀጽ አበይት መለያወች እና አገልግሎቶች

1.      ወደ ፊት ለሚደረግ ድርጊት የሚያገለግል ነው (Futur tense )
2.     ተዘውትሮ ለሚደረግ () ድርጊትም ይሆናል(present tense)
3.      አገባቦችን በመጠቀም በመደረግ ላይ ለሚገኝ ድርጊትም ይሆናል።(present continuous) ስለዚህ በብዙ ዓይነት መልኩ እንጠቀምበታለን ማለት ነው።
4.     ከግሡ መጀመሪያ ላይ ባእድ ሆሄን ይጨምራል (እነዚህ ባዕድ ሆሄያት ስማቸው አሥራው ሲባሉ ቁጥራቸው 4 ነው። በአማርኛ “ሥሮች” ማለት ነው። ይ፤ት፤ን፤እ፤ ናቸው። በ ሀ እና በ አ ግሦች ግዕዛቸውና ራብአቸውም ይገኛል። (በትንቢት ፤ በዘንድ፤ በትእዛዝ፤ አናቅጽ ብቻ የሚገቡ ናቸው) ለወደፊቱ ስለነዚህ ፊደላት ሙሉ ትምህርት እንማራለን፤ ለአሁኑ ግን ጠቅለል አድርገን ነው የምናያቸው።
ከዚህ ቀጥሉ ካልአይ ግሥ ለትንቢታዊ ፤ ተዘውትሮ ለሚደረግ፤ እና በመደረግ ላይ ላለ ድርጊት እንዴት እንደሚገባ እናያለን። በመጨረሻም ስለሚጨምራቸው ባዕድ ፊደላት በሦስት ግሦች እንደ ምሳሌ እናያለን።


መሳሌ፡1 ለትንቢታዊ ድርጊት
·         አነ አሀውር ኀበ ብሔረ ግብፅ ድኅረ ሰለስቱ ዓመታት
ምሳሌ፡2 ዘወትር ለሚደረግ ድርጊት
·         “ይብል ዓብድ በልቡ አልቦ እግዚአብሔር” (ሰነፍ በልቡ እግዚአብሔር የለም ይላል)
·         አንትሙ ተአምሩ ልሳነ ግእዝ
·         ሕጻን ይበኪ እንዘ ይበልእ
ምሳሌ 3፡ በመደረግ ላይ ላለ ድርጊት
ምንተ ትገብሩ አኀውየ?  እንዘ ንትሜሀር ልሳነ ግእዝ

ምሳሌ 4፡ ከግሡ መጀመሪያ ላይ ባእድ ሆሄን ሲጨምር
ሰአለ =ይስእል (ለመን)
ባረከ=ይባርክ

ገብረ=ይገብር

Saturday, June 6, 2015

ግእዝ ክፍል 26 ሐላፊ አንቀጽ

ክፍል 26


ሐላፊ ግሥ/past tense

በሃላፊ ጊዜ በግእዝ ሆሄ የሚጨርሱ ግሶች (መራሕያን)

ሐላፊ ግሥ ወይም አንቀጽ ቀዳማይ በመባልም ይጠራል መጀመሪያ ማለት ነው፤ ስለዚህ የመጀመሪያ ስለሆነ ቀዳማይ ወይም የመጀመሪያ ተባለ። በዛሬው በክፍል 26 ትምህርታችን ይህንኑ ሐላፊ ግሥን ብቻ የሚከተሉትን 5 ግሦች መሠረት አድርገን እንማራለን።

በግእዝ ቋንቋ ሐላፊ ግሥ የሚሆነው የመጀመሪያው መሠረታዊ ግሥ ነው። ማለትም ማነኛውም ግሥ ተጽፎ የሚገኘው በሐላፊ ጊዜ ነው። ማነኛውም ግሥ የሚጀምረው በሦስተኛ መደብ በወንድ ጾታ፤ በአንድ ቍጥር ነው። ስለዚህ የግእዝን መዝበበ ቃላት መጽሐፍ ገልጠን ብንመለከት ዘር ግሥ ሁሉ ተጽፎ የሚገኘው በሦስተኛ መደብ ነጠላ በወድ ፆታ ሲሆን ጊዜውም በሃላፊ ጊዜ ነው።

በሚከተለው ዓይነት ማለት ነው። የሚከተሉት የአምስቱ ግሦች ባለቤት ሦስተኛ መደብ ነጠላ ለውንድ ሲህን ይህም “ውእቱ” የሚለው ተውላጠ ስም ነው።
·         ቀደሰ
·         ሆረ
·         አእመረ
·         ኀሠሠ
·         ባረከ
ሐላፊ ማለት ያለፈ ጊዜን የሚያመለክት የተደረገ፤ የተሠራ፤ ያለቀለት፤ ሥራ ወይም ድርጊት ነው። ሐላፊ ጊዜን የበለጠ ግልጽ ለማድረግ እንደ ቅድመ፤ቅድም፤ ትማልም፤ ወዘተ የመሳሰሉትን አገባቦች መጠቀም እንችላለን።
·         ቀደሰ፡= አመሰገነ
ውእቱ ቀደሰ ምስለ ካህናት =እሱ ከካህናት ጋር አመሰገነ። ይህ ዐረፍተ ነገር ወይም ግሥ የሚነግረን ነገ የሚደረግ፤ ወይም በመደረግ ላይ ያለ ድርጊትን ሳይሆን ያለፈ፤ የተደረገ፤ ያለቀለትን ታሪክ ነው። ሓላፊ ግሥ በአሥሩ መራኅያን ሁሉ እንደ ሚከተለው ይረባል።
3ኛ መደብ
1.      ቀደ-ሰ
2.     ቀደ-ሱ
3.     ቀደ-ሰት
4.     ቀደ-ሳ
2ኛ መደብ
5.     ቀደ-ስከ
6.     ቀደ-ስክሙ
7.     ቀደ-ስኪ
8.     ቀደ-ስክን
1ኛ መደብ
9.     ቀደ-ስኩ
10.    ቀደ-ስነ




ሐላፊ ግሣቸውን ወደ ግእዝ ሆሄ የሚቀይሩ ወይም ሃላፊ ግሳቸው ግእዝ የሚሆን ግሦች ወይም መራሕያን ሦስት ናቸው።

በሐላፊ ጊዜ የመጨረሻውን የግሡን ሆሄ ወደ ግእዝ ሆሄ የሚቀይር ግሥ ወይም መራሂ

ውእቱ ሆረ (ይህ ግሥ ምንጊዜም ግእዝ ሆሄን ቢጠቀምም እንደ ግሱ ሁኔታ ይቀያየራል፤ ግእዝነቱን ግን አይቀይርም።

አንተ ሆርከ (ይህ ግሥ በማነኛውም ዓይነት ግሥ ይሁን ለሐላፊ ጊዜ“ከ” የሚለውን ሆሄ ብቻ ይጠቀማል።

ንሕነ ሆርነ (ይህ ግሥ በማነኛውም ዓይነት ግሥ ይሁን ለሐላፊ ጊዜ“ነ” የሚለውን ሆሄ ብቻ ይጠቀማል።

በነዚህ ከዚህ በላይ በተጠቀሱት በሦስቱ መራሕያን በ3ኛ መደብ ነጠላ ለወንድ፤ በሁለተኛ መደብ ነጠላ ለወንድ፤ እና በአንደኛ መደብ ብዙ ለወንድም ለሴትም ግሡ ለሃላፊ ጊዜ ሲሆን በግእዝ ሆሄ ይጨርሳል። ወይም የመጨረሻው ሆሄ ግእዝ ይሆናል።

በተጨማሪም አንተ በሚለው የግሱ የመጨረሻ ሆሄ ከግእዝ ወደ ሳድስ ይቀየርና “ከ” የሚለውን ሆሄ ይጨምራል። ለምሳሌ. “ሆርከ”።
ንሕነ በሚለው ደግሞ የግሱን የመጨረሻ ሆሄ ወደ ሳድስ ይቀይርና “ነ” የሚለውን ሆሄ ይጨምራል። ለምሳሌ.“ሆርነ” ።

ውእቱ በሚለው ግን ግሱ አይቀየርም “ሆረ”።

Friday, May 15, 2015

ግእዝ ክፍል 24

የግእዝ ትምህርት ክፍል 24


ሰላም ለሁላችሁ ይሁን እንኳን ለብርሃነ ትንሣኤው አደረሳችሁ

ባለፈው በክፍል 23 ትምህርታችን “አውደ ጥናት” ስለምትባል አንዲት እናት በግእዝ ቋንቋ አጭር ታሪክን ጽፌላችሁ ነበር። ይህ ክፍል ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ በግእዝ ቋንቋ ብቻ የተዘጋጀ ነበር። ይህንንም ያደረግሁት ልምምድ እንድታደርጉ እንደ መመሪያ እንዲሆናችሁ በማሰብ ነው።
ዛሬ በክፍል 24 ትምህርታችን ደግሞ ትርጉሙንና ተጨማሪ ማብራርያን  እነግራችኋለሁ(የክፍል 23ን ማለት ነው)። እያንዳንዳችሁም የራሳችሁን ታሪክ ለመጻፍ ሞክሩ።
አንድ ታሪክ ለመጻፍ እንደሚታወቀው ሦስት ነገሮች ወይም ክፍሎች መኖር አለባቸው። እነዚህም
1.      መግቢያ
2.     ዋና ታሪክ እና
3.     መዝጊያ ወይም ማጠቃለያ ያስፈልገዋል። ይህ ማለት ስለ ምን መናገር እንደ ፈለግን ለአድማጮቻችን  እንናገራለን (ይህ መግቢያ ይባላል)

መናገር የምንፈልገውን ፍሬ ሐሣብ በዝርዝር እንናገራለን (ይህ ዋና ታሪክ ወይም የጽሁፉ ዋና ክፍል ይባላል)
እንደ ገና የተናገርነውን ታሪክ ባጭሩ ፍሬ ሐሳቦችን ብቻ ለአድማጮቻችን  እንነግራቸዋለን (ይህ ማጠቃለያ ይባላል)

በሌላ አገላለጽ መግቢያው ቀድመው ስለሚሰጠው ታሪክ እንዲያስቡና ምን ዓይነት መልእክትና ፍሬ ሐሳብ እንደሚኖረው ለመገመትና በተገቢው መልኩ ለመከታተል እንዲችሉ ይረዳቸዋል።

ዋናው ንግግር ታሪኩን በልዩ ልዩ ማስረጃና ድጋፍ ማስተማር ማለት ነው ስለዚህ አድማጮቹ ፍሬ ሐሣቡን እስከ ማስረጃው አዳመጡ።
ማጠቃለያው ደግሞ ከሰሙት ታሪክ መካከል ባጭሩ ፍሬ ሐሳቦችን ብቻ ጨምቆ ወይም አጣርቶ በማውጣት ስለሚነገር ከረጅሙ ንግግር ውስጥ ፍሬ ሐሳቦችን ቶሎ ማስታዎስ እንዲችሉ ይረዳቸዋል።

እነዚህ ሦስት ነገሮች የአንድ ታሪክ አካላት ናቸው። የአጻጻፍ ስልታቸው ግን ሊለያይ ወይም ሊያጥርና ሊረዝም ይችላል።
በዛሬው ትምህርታችን ግን ባጭር አጠቃቀም ብቻ እናያለን።

ከዚህ በላይ ያለው አገላለጽ ብዙጊዜ  ለመጻሕፍት (መጽሐፍ ስንጽፍ) ለሌሎችን ጥናታዊ ጽሁፎችን ስናዘጋጅ ለመሳሰሉት የምንጠቀምበት ነው። ከተቻለ ለማነኛውም ንግግር በዚህ ዓይነት ምልኩ ማቅረቡ ይመረጣል ። ካልሆነ ግን

በመልካም ምኞት ወይም በሰላምታ መጀመርና መደምደም እንችላለን / ለምሳሌ እንደምን አደራችሁ በማለት የንግግራችንን ርእስ ብቻ በመጥቀስ እንጀምራለን; ስንጨርስም ለሰሚወቻችን መልካም ምኞትን በመመኝት መልካም አዳር በማለት በመሳሰሉት የእምነት ጉባኤ ከሆነ (እግዚአብሔር ለመስማት የተዘጋጀን ያድርገን፤ የሰማነውን በልቡናችን ይጻፍልን በማለት መጀመርና መጨረስ እንችላለን ።


አሁን የክፍል 23ን መግቢያ፤ ዋና ፍሬ ሐሣብና ፤ ማጠቃለያ እንመልከት
መግቢያ
ሰላም ለክሙ አኃውየ ወአኃትየ አርድእተ ልሳነ ግእዝ ኩልክሙ። (ይህ ሰላምታ ነው)

ዮምሰ ፈቀድኩ ከመ እምሀርክሙ ልሳነ ግእዝ በልሳነ ግእዝ ባህቲቱ። ወእስእለክሙ ከመ ትስምኡ ወታጽምኡ በእዝነ ልቡናክሙ፤ ወትነጽሩ በዐይነ ልቡናክሙ። ኅበ ዜና አሐቲ ብእሲት ዘእዜንወክሙ ድኅረ ሰለስቱ ቅጽበታት።
 ዮም በእሥራ ወሰለስቱ ክፍለ ትምህርትነ እዜንወክሙ በይነ አሐቲ ብእሲት ዘስማ አውደ ጥናት። (መመሪያ)

(ሰላም ለክሙ/ለክን/ለኪ/ለከ (አንድ ወንድ ካለ ብዙ ሴቶች ቢኖሩም በወንዶች አንቀጽ ነው የሚጠራው)

(ዮም፤ ናሁ
እነግረክሙ፤
እዜንወክሙ፤

እዜንወክሙ በይነ አሐቲ ብእሲት ዘስማ አውደ ጥናት።

(ዮም እነግረክሙ፤እዜንወክሙ፤
እዜንወክሙ በይነ አሐቲ ብእሲት።


ዋናው ታሪክ
ቅድመ ሰለስቱ ዓመታት
 እንዘ አሀውር በፍንወት ረከብኩ እቤርተ ዕድሜ ብእሲተ ዘስማ አውደ ጥናት፤ ወስመ ጥምቀታ ወለተ ማርያም። ወይእቲሰ እምነ ነገደ ኢትዮጵያ። ወብእሲት ነበበተኒ ከመ ወለደት ብዙኃነ ደቂቀ እለ ይነብሩ ዝርዋነ በውስተ ኵሉ ዓለም ወሰአለተኒ ከመ እምሀር ላቲ ደቂቃ ልሳነ ግእዝ ወቅኔ ወአነኒ እቤላ ኦሆ።
ማጠቃለያ/መዝጊያ
ተፈጸመ ዜና ሕይወታ ለብእሲት

ናሁ እጤይቀክሙ ሐምስተ ጥያቄያተ እለ ወጽኡ እምነ ዜናሃ ለብእሲት ዘዜነውኩክሙ በዛቲ ዕለት

(ይህ ክፍል ሊረዝም ይችል ነበር። ማጠቃለያ ሲባል በዋናው ታሪክ ውስጥ የተጻፉትን በአጭሩ እንደ ገና መግለጽ ነው። ከዚህ ላይ ግን ታሪኩ ማለቁን በመናገር እና ከታሪኩ ውስጥ ጥያቄዎችን በማውጣትና በመጠየቅ ይጨርሳል። በመሆኑም በተዛዋሪ መንገድ ማጠቃለያ ተሰጠ ማለት ነው።