What is Welcome Corps?
Welcome
Corps (welcomecorps.org)
ሰላም ጤና ይስጥልኝ ከአውደ ጥናት ነው፤ የዛሬው ግጅቴ
በማኅበራዊ ሕይወት ዙሪያ የሚቀር መረጃ ነክ ትምህርት ነው::
በዚህ ዝግጅት የአሜሪካ መንግስት ስላወጣው አዲስ ወደ አሜሪካ መግቢያ መንገድ
እንዴት፣ በማንና ለምን የሚሉትን ቁልፍ ጥያቄዎች በማካተት ሙሉ መረጃ እሰጣችኋለሁ።
ይህንን ለማቅረብ ያነሣሳኝ ከተለያዩ ክፍሎች ተደጋጋሚ
ጥያቄዎች ሲነሱ ስለሰማሁ ትክክለኛውን መረጃ ለማካፈል በማሰብ ነው።
የዚህን መረጃ ትክክለኛነት ለማረጋገጥም ሊንኮችን ከዚህ
ዝግጅት መጨረሻ ላይ አስቀምጥላችኋለሁ ማየትና ማረጋገጥ ትችላላችሁ።
ስለዚህ መረጃውን የምትፈሉጉ ሰዎች ተከታተሉ፣ ጥያቄ ካላችሁም
ጠይቁ፤ ለሌሎችም በማስተላለፍ ወይም ሸር በማድረግ እንዲጠቀሙ አድርጉ።
Welcome
Corps
ዌልካም ኮርፕስ የሚባለው አሜሪካውያን በግሩፕ ወይም
በማኅበር በመሆን በተፈጥሮ ችግርም ሆነ በፖለቲካ ምክንያት ከመኖሪያቸው ተፈናቅለው በመላው ዓለም በችግር ላይ የሚገኙ ስደተኞችን
በሃላፊነት ተቀብለው ወደ አሜሪካ እንዲያስገቡ የሚያደርግ አዲስ የተቋቋመ የስደተኞች መልሶ ማቋቋም ፕሮግራም አስፈጻሚ መሥሪያ ቤት
ነው። ዌልካም ኮርፕ በቀጥታ የተቋቋመው በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በኩል ነው።
የሚከተሉት
ተቋማት የየራሳቸው
የሥራ ድርሻ
አላቸው
1.
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በቀጥታ ጉዳዩን በመምራት
2.
የአሜሪካ የጤና ጥበቃና የሰብአዊ አገልግሎት መሥሪያ ቤት ስደተኞቹ ወደ አሜሪካ ከገቡ በኋላ ከስፖንሰሮች
ጋር በመሆን እስከ 90 ቀናት የተለያዩ የርዳታ ድጋፎችን በማድረግ
3.
የአሜሪካ የብሔራዊ ደኅንነት መሥሪያ ቤት የስደተኞቹን ማንንነት በማጣራትና ተቀባይነታቸውን በማረጋገጥ
ይሠራሉ።
4. ከተጠቀሱት ሌላ የተለያዩ
የበጎ አድራጎት ድርጅቶችም በበጎ አድራጎት ሥራ ይሳተፋሉ፤ ለምሳሌ
·
የእምነት የበጎ አድራጎት ተቋማት
·
የአገር አቀፍና የዓለም አቀፍ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ይሳተፋሉ።
የፕሮግራሙ
እቅዶች
·
በዓመት 125,000 ስደተኞችን ወደ አሜሪካ ማስገባት
·
በዚህ
ዓመት ብቻ 5,000 ስደተኞችን መቀበል
·
መጀመሪያ የሚመጡት ስደተኞች ከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ አገራት ነው
·
ይህንን እቅድ ለማሳካት
10,000 የግል ስፖንሰሮችን ማግኘት አለባቸው፤
·
ስፖንሰሮች ከጥር/January19/2023 ጀምረው እየተመዘገቡ ነው።
·
የመጀመሪያዎቹ ስደተኞች ሚያዝያ/April ላይ ወደ አሜሪካ ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ዌልካም ኮርፕ ከዚህ በላይ የተጠቀሱትን እቅዶች ለማሳካት
2 ዓይነት ፕሮግራሞችን ነድፏል። አንዱ በአሁኑ ጊዜ ተጀምሮ በመካሄድ ላይ ያለ ሲሆን 2ኛው በዚህ ዓመት አጋማሽ
ላይ ይጀመራል ተብሎ የሚጠበቅ ነው።
የዌልካም
ኮርፕ ፕሮግራሞችና የአሠራር ሒደቶች
ከላይ እንደገለጽኩት በዚህ ፕሮግራም ሁለት ዓይነት የአሠራር እቅዶች አሉ
1ኛ አምስት (5) ወይም ከዚያ በላይ የሆኑ አሜሪካውያንና የአሜሪካ
ኗሪዎች በጋራ በመሆን ዌልካም ኮርፕ የሚያቀርብላቸውን ማነኛውንም ስደተኛ በውክልና (ስፖንሰር አድርገው)
እንዲቀበሉ የሚያስችል ሲሆን
2ኛው እንደዚሁ አምስት(5) ወይም ከዚያ በላይ የሆኑ አሜሪካውያንና
የአሜሪካ ኗሪዎች በጋራ በመሆን ራሳቸው መርጠው ለዌልካም ኮርፕ በማቅረብ ያቀረቧቸው ስደተኞች ተቀባይነትን ሲያገኙ በውክልና (በስፖንሰርነት) የማምጣት ፕሮግራም ነው፣ ይህ ፕሮግራም ቤተሰብንም ሊያካትት
ይችላል።
በአሁኑ ጊዜ በ1ኛ ተራቁጥር የተጠቀሰው ብቻ ተጀምሮ
ዝግጅት እየተደረገበት ነው።
በ2ኛ ደረጃ የተጠቀሰው ግን በዚህ ዓመት አጋማሽ ላይ ጀምሮ ሥርዓትና መመሪያ ተዘጋጅቶለት ይፋ እንደሚሆን ይጠበቃል።
በአሁኑ ጊዜ ግን ምንም ዓይነት ተጨባጭ የሆነ መረጃ አልተሰጠበትም።
በቀጣይ ለከፍተኛ ትምህርት ተማሪዎችም ተመሳሳይ ዕድል መካተቱ እንደማይቀርም በድርጅቱ ድረ-ገጽ ተገልጿል።
ስደተኞቹ
እነማናቸው?
በመጀመሪያው ዙር ስደተኞቹ
በመላው ዓለም የሚገኙ በአሜሪካ የስደተኞች ጉዳይ መሥሪያ ቤት በኩል አመልክተው፣ ማመልከቻቸው ተቀባይነትን ያገኘ ባጭሩ ሁሉንም
መመዘኛና ግዴታ አሟልተው ወደ አሜሪካ ለመግባት በመጠባበቅ ላይ የሚገኙ ናቸው።
ስፖንሰር መሆን
የሚቻለው እንዴት
ነው? መሆን የሚችሉት ሰዎችስ እነማን ናቸው?
·
ስፖንሰር
ለመሆን ቢያንስ 5 ግለሰዎች በኅብረት መሰባሰብ አለባቸው
·
የአሜሪካ ዜጋ የሆኑ
·
በአሜሪካ ሕጋዊና ቋሚ የመኖሪያ ፈቃድ ያላቸው
·
ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በላይ የሆናቸው
·
ታሪካቸው ተጠንቶ
መልካም ሰብእናቸው የተረጋገጠ
·
ስፖንሰሮቹ ለያንዳንዱ ስደተኛ $2,375 መሰብሰብ አለባቸው
·
ስደተኞቹን እንዴት ለመቀበል እንደሚዘጋጁ የጽሁፍ ፕላን ጽፈው ለዌልካም ኮርፕ
ማቅረብና ተቀባይነት ማግኘት አለባቸው
·
ለሥራው ብቃትና ቁርጠኝነታቸውን የሚያስረዳ የስምምነት ሰነድ መፈረም አለባቸው
ስፖንሰሮች
ወይም በማኅበር
የሚሰባሰቡት አባላት ቀረቤታ
ለአሠራርና ስደተኞችንም በቅርበት ለመርዳት አመች ይሆንላቸው ዘንድ ስደተኞችን በስፖንሰርነት በማኅበር የተደራጁ አባላት።
በአንድ አካባቢ የሚኖሩ መሆን አለባቸው፤ እነዚህም
·
ጓደኛሞች
·
ጎረቤቶች
·
የሥጋ ዘመዶች
·
የሥራ ባልደረቦች
·
የእምነት ማኅበራት አባላት
·
ለምሳሌ የጽዋ ማኅበራት
·
በአንድ አጥቢያ ቤተክርስቲያን ያሉ ምእመናን ወዘተ መሆን ይኖርባቸዋል።
ስፖንሰሮች እንዴት ነው
የሚሰባሰቡት? የሚያደርጉትስ ዝግጅት?
አንድ ሰው ፍላጎትና ችሎታ ያላቸውን 5 ወይም ከዚያ በላይ
ሰዎችን ያነጋግርና ፈቃደኛ ሲሆኑ ስደተኞችን ለመቀበል መሰባሰባቸውን፣ ለሚጠበቅባቸው ሃላፊነትም ብቁዎች መሆናቸውንና ስንት ስደተኞችን
መቀበል እንደሚፈልጉ በመግለጽ ለ“ዌልካም ኮርፕስ” በጽሁፍ ማመልከቻ ያቀርባል።
ዌልካም ኮርፕ ማመልከቻውን ከመረመረ በኋላ ማመልከቻቸው
ተቀባይነትን ካገኘ ስለ ስደተኞቹ አቀባበል ሕግና ደንብ እንዲሁም አጠቃላይ ሃላፊነታቸውን በተመለከተ ሥልጠና ይሰጣቸዋል፤ እያንዳንዱ አባል በዌልካም ኮርፕ ድረ-ገጽ አካውንት
ይከፍታል፤ በግሩፑ $2,375 ዶላር ገንዘብ ይሰበሰባል፣ ቢያንስ 60% ስደተኞቹ ወደ አሜሪካ ከመግባታቸው በፊት መሰብሰብ አለበት፣ የሚመጡት ስደተኞች
ሙሉ መረጃ ቀድሞ ማወቅ ይኖርባቸዋል፤ ከመረጃዎቹም
·
ሙሉ ስም
·
ዕድሜ
·
የትውልድ አገር
·
ቋንቋ
·
ፆታ
·
የትምህርት ደረጃ
·
የእንግሊዘኛ ቋንቋ የችሎታ ደረጃ
·
የበረራ ቁጥር
·
አሜሪካ የሚገቡበት ቀንና ሰዓት
ከስፖንሰሮች ሙሉ
ሃላፊነቶች
መካከል የሚከተሉት ይገኙባቸዋል
በሃላፊነት የሚቀበሏቸውን ስደተኞች እንዴት ማቋቋምና ራሳቸውን ማስቻል እንዳለባቸው ሙሉ የጽሁፍ ፕላን
ወይም እቅድ ያወጣሉ
ስደተኞቹ የሚኖሩበትን ቤት ቀድመው ያዘጋጃሉ
በኤርፖርት ተገኝተው ስደተኞችን ተቀብለው ወዳዘጋጁላቸው ቤት ያስገባሉ
ቤቱ ንጹህ፣ሰላማዊ ሰፈርና ዋጋውም ራሳቸውን ከቻሉ በኋላም ሊኖሩበት የሚችሉ ወርሃዊ ክፍያው/ኪራዩ ተመጣጣኝ
የሆነ መሆን አለበት።
ከተሰበሰበው ገንዘብ በተጨማሪ ልዩ ልዩ ዕቃዎችንና ቁሳቁሶችን ያቀርባሉ፡ ለምሳሌ የቤት እቃዎችን፣ አልጋ፣ወንበር፣ የምግብና
የመጸዳጃ ዕቃዎች፣ ኮምፕዩተር፣ ሶፍትዌር፣ ልጆች ካሉም የልጆች መጫዎችዎች፣ወዘተ ያቀርባሉ።
ስደተኞቹ ራሳቸውን ስከሚችሉ ድረስ በተለይ ለመጀመሪያ
30 ቀናት የኪስ ገንዘብ፣ ምግብና የምግብ ወጭዎችን ያሟላሉ። ማመልከቻ በመሙላትና
·
ሶሻል ሰክዩሪቲ ካርድ
·
የሥራ ፈቃድ
·
መታወቂያ(መንጃ ፈቃድ)
·
ዕድሜው ከ18-25 ዓመት የሆነው ወንድ ካለ የብሔራዊ ውትድርና ካርድ ወዘተ
·
ልዩ ልዩ ጥቅማጥቅሞችንና ሰብአዊ አገልግሎቶችን ከመንግሥታዊ መዋቅሮች እንዲያገኙ መረጃ መሰብሰብና መስጠት ማመልከቻ መሙላትና
ማስፈጸም
·
ለትምህርት የደረሱ ሕጻናት ካሉ ለትምህርት ማስመዝገብ
·
ወደ እንግሊዘኛ ትምህርት ቤት ወስዶ ማስመዝገብና እንዲከታተሉ ማድረግ፣ አሰልጣኝን
መቅጠር፣ ላይብረሪ መውሰድ፤ ወሳኝ በሆኑ ቦታዎች ለምሳሌ
በሕክምና ተቋማት፣ በመንግሥታዊና ማኅበራዊ ተቋማት አገልግሎትን ለማግኘት ሐሣባቸውን በትክክል ለማስረዳት የትርጉምና የአስተርጓሚ
አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረግ፤ ወደ እምነት ቦታዎች፣ ወደ ማኅበራዊና ባሕላዊ ተቋማት፣ የገበያ ማዕከላት፣ ምግብ
ቤቶች ወዘተ መሄድ እንዲችሉ መርዳት፣ ቦታ ማሳየት፣ ማድረስ፣ በእግርም ሆነ በመኪና ራሳቸውን ችለው እንዲሄዱም ማስቻል።
ስለ አሜሪካ ኑሮ፣ ወይም ሕይወት፣ ባሕል፣ ሕግና ሥርዓት፣ መብትና ግዴታዎች፣የራስ ጥንቃቄና ራስን እንዴት መጠበቅ
እንዳለባቸው፣ የባቡር፣ የአውቶብስ፣ የታክሲ፣ የባንክና ወዘተ አጠቃቀምና ሕግ ሌሎችንም ሁሉ በሚገባ ማወቅና መጠቀም እንዲችሉ ማሳወቅ።
ስደተኞች በወቅቱ ሥራ አግኝተው እንዲሠሩ ለማድረግ የሥራ ልምድን ልዩ ችሎታን፣ የትምህርት ደረጃን
ወዘተ የሚገልጥ ጽሁፍን በማዘጋጀት፣ ሥራ በመፈለግ፣ የሥራ ሥልጠና እንዲወስዱ በማድረግ አዘጋጅቶ ሥራ ማስያዝ፡
ስደተኞቹ ራሳቸውን የሚችሉበት ጊዜ ከመድረሱ በፊት መቼ ራሳቸውን መቻል እንዳለባቸው
የስፖንሰሮች የሃላፊነት ጊዜ ሳያልቅ ማስታወቅና ራሳቸውን እንዴት መቻል እንዳለባቸው ቀድሞ ማስረዳትና ማዘጋጀት
ማጠቃለያና የኔ የግሌ
አስተያየት
ጉዳዩ በጥቅሉና በደፈናው 5 ሰዎች ሆነው $2375 ዶላር
በመክፈል ቤተሰዎቻቸውን መውሰድ ይችላሉ በሚል አንድ ነጠላ ዐረፍተ ነገር እንደሚነገረው አይደለም። በመጀመሪያ ደረጃ ይህ ዘመድን
የማምጣት ፕሮግራም አሁን አልተጀመረም፣ መመዘኛውና ሥርዓቱ ምንና እንዴት እንደሆነም የታወቀ ነገር የለም፣ ብዙ ሰዎች እንደተጀመረ
አስመስለው ጉዳዩን አቅለው ሲናገሩ እሰማለሁ፣ ግን የሚታወቅ ነገር የለም፤ በድርጅቱ ድረገጽም የሚለው ወደፊት መረጃ ይሰጣል ነው
የሚለው።
ባጠቃላይ መልኩ ግን ሕጋዊ ሓላፊነቱ ቀላል አይደለም፣
ሙሉ ሕጋዊ ሃላፊነትን መውሰድንና ሰፊ ጊዜን መሥዋዕት ማድረግን ይጠይቃል። ሃላፊነቱ ደግሞ በአንድ ሰው ብቻ የማይወሰን በመሆኑና
የአምስት ሰዎችን ሙሉ አወንታና ችሎታን የሚጨምር በመሆኑ ተቀባይ ለማግኘት አንድ ፈቃደኛ በቂ አይደለም።
በይፋ 5ቱ ወይም ከዚያ በላይ የተደራጁት ሰዎች የሚያዋጡት
ገንዘብ ትንሽ መስሎ ቢታይም፣ ከሚዋጣው ገንዘብ ሌላ የኪስ ገንዘብ እንዲሁም ለምግብ፣ ለቁሳቁስና ለሌሎችም ተጓዳኝ ነገሮች የሚወጣው
ወጭና ከሁሉም በላይ ስደተኞቹ ራሱን የቻለ መኖሪያ ቤት በኪራይ ተይዞላቸው
የሚኖሩ ስለሆነ ሙሉ በሙሉ ራሳቸውን እንዲችሉ ለማድረግ ጠንካራ ጥረትንና ጊዜን ይጠይቃል።
በ90 ቀናት ውስጥ ራሳቸውን ማስቻል ካልተቻለም ሃላፊነቱ
ይቀጥላል። (በርግጥ ስፖንሰሮችን በተለያዩ መንገዶች የሚደግፉ ሌሎች የርዳታ ድርጅቶችም
አሉ ግን ሃላፊነቱ የስፖንሰሮቹ ነው)
ሌላው በዚህ ፕሮግራም ሰዎች የራሳቸውን ቤተሰዎች፣ ልጆቻቸውን፣
ወላጆቻቸውን ወንድም እኅቶቻቸውን ወዘተ ስፖንሰር አድርገው ለማምጣት ምንም ዓይነት የተለየና ጉዳዩን ቀላል እንዲሆን የሚያደርግ
አይደለም፤ ምክንያቱም አሁን ባለው መሠረታዊ መረጃ ስፖንሰሮች እንዲመጡ የሚፈልጓቸውን ሰዎች ለድርጅቱ ያቀርባሉ፤ ከዚያ በኋላ የአሜሪካ
የስደተኞች ሕግና ሥርዓት የሚያዘውን ሁሉ አሟልተው መገኘት ሲችሉ ብቻ ነው የሚፈቀደው። ማለትም መመዘኛው በግላችን አመልክተን ከሚቀርብልን
መመዘኛ የተለየ አይደለም።
ስለዚህ ባጠቃላይ ይዘቱን፣ መመዘኛውና መመሪያውን ሃላፊነቱንም
መሠረት በማድረግ ስገመግም ያለምንም የግል ጥቅምና እቅድ ማነኛውንም ስደተኛ በሰብአዊ ፍጡርነቱ ለመርዳት ፍላጎት፣ ገንዘብና ጊዜ
ያላአቸውን ግለሰዎች በረዳትነት ለማግኘት የታቀደ ፕሮግራም ይመስለኛል።
ይህ ሁሉ እንዳለ ሆነ ቤተሰዎቻችንን ማምጣት አለብን የምትሉ
ወይም በጓደኛ በዘመድ እርዳታ መምጣት አለብን የምትሉ ሰዎች ፍላጎታችሁ ወይም ሙከራችሁ ውጤት ሊኖረው የሚችለው የሚከተሉት ሲሟሉ ወይም ሲኖሩ ነው ብየ
አምናለሁ
1.
መምጣት
የምንፈልግ ዋናውና የመጀመሪያው የአሜሪካን የስደተኞች ሙሉ መመዘኛዎችን በማወቅ የምናሟላ መሆናችንን መረዳት ይኖርብናል።
2. ቢያንስ አምስት ሙሉ ሐላፊነትን በሕጋዊ መንገድ ሊወስዱ የሚችሉ
ፈቃዱ ገንዘቡ ጊዜው ያላቸው ጓደኞችና ዘመዶች ሲኖራችሁ
3. ወይም አንድ ሰው ኖሯችሁ በሕጋዊ መንገድ ሙሉ ሐላፊነትን ለመውሰድ
ፈቃድ፣ ጊዜና ገንዘብ ያላቸው ቢያንስ ሌሎች 4 ሰዎችን ማግኘት የሚችል ሲኖር ብቻ ነው።
ሠናይ ለክሙ
ከአውደ ጥናት