Friday, April 9, 2021

አራቱ የቤተ ክህነት የትምህርት አከፋፈሎችና ዓይነቶች


መጻሕፍት ለመግዛት ከዚህ በታች ያለውን ራሱ መጽሐፉን ይጫኑ ወይም በ+1 703 254 6601 ይደውሉ


የቤተ ክህነት ትምህርት ዓይነትና አከፋፈል ወይም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ትምህርት ዓይነትና አከፋፈል

የቤተ ክህነት ትምህርት በአራት አበይት ክፍሎች ይከፈላል፤ እነዚህም ክፍሎች የሚከተሉት ናቸው

1.   የንባብ ትምህር (የቃል ትምህርትም በዚህ ይጠቃለላል)

2.  የዜማ ትምህርት

3.  የቅኔ ትምህር እና

4.  የመጻሕፍት ትርጓሜ ትምህር የሚባሉት ናቸው

አራቱንም ክፍሎት በአጭሩ እንደሚከተለው እናብራራቸዋለን

የንባብ ትምህር፡

ይህ የትምህርት ክፍል የመጀመሪያው ክፍል ሲሆን ከፊደል ጀምሮ እስከ መዝሙረ ዳዊት ድረስ ወይም ከቍጥር እስከ ቁም ንባብ ድረስ የሚደርስ ሲሆን በውስጡ አራት ክፍሎች አሉት

እነሱም ቍጥር፣ ግእዝ ንባብ፣ ውርድ ንባብ፣ እና ቍም ንባብ የሚባሉት ናቸው

 

·        ቍጥር - የፊደላትን ስያሜ መልክ ቅርጽ፣ እንዲሁም የግልና የጋራ ስያሜያቸውን ለይቶ ማወቅ ነው፤ ይህም በፊደል ገበታና መመልእክተ ዮሐንስ መሠረት የሚሰጥ ነው

 

·        ግእዝ ንባብ - የግእዝ ንባብ የሚባለው ተማሪው ፊደላትን ከተማረና ካወቀ በኋላ የዮሐንስ መልእክት 1ኛን “ማጋዝ” ወይም የግእዝ ንባብ በሚባለው የአነባበብ ወይም የአነጋገር ዘይቤ እየመላለሰ ድምፁን ከፍ አድርጎ በመናገር የሚማረው የአነባበብ ስልት ነው።

 

·        ውርድ ንባብ - ውርድ ንባብ የሚባለው የአነባበብስ ስልት ደግሞ ከግእዝ የአነባበብ ስልት ቀጥሎ የሚጠና ወይም የሚሰጥ የአነባበብ ስልት ሲሆን የማሳዘንና የማራራት ቃና ያለው የንባብ ስልት ሲሆን በቤተ ክርስቲያን አልፎ አልፎ በሥርዓተ ማኅሌትም የሚባልበት ጊዜ አለ ይልቁንም በሥቅለት 11 ሰዓት አካባቢ ዲያብሎስ ወይም ሰይጣን በሚቀጠቀጥበት ምሳሌያዊ ሥርዓት “ፍካሬ ዘጻድቃን ወዘኃጥአን” የሚባለው የመጀመሪያው የዳዊት መዝሙር በውርድ ንባብ ይነበባል።

 

·        ቁም ንባብ  - ቁም ንባብ የሚባለው ከፍተኛው የሥርዓተ ንባብ ክፍል ሲሆን ማነኛውም መደበኛ ሥርዓተ ንባብ በቤተክርስቲያንም ሆነ በሌላ የሥርዓተ ጸሎት አገልግሎት የሚነበበው በዚሁ በቁም ንባብ የአነባበብ ስልት ነው። ተማሪው የዮሐንስ መልእክት አንደኛን ካነበበ በኋላ ቀጥሎ የዳዊት መዝሙራትን ነው የሚማረው። ስለዚህ “የንባብ ክፍል” ከፊደል እስከ መዝሙረ ዳዊት ድረስ የሚቀጥል ወይም የሚደርስ ሲሆን። ተማሪው ከዚህ ደረጃ በኋላ ማነኛውንም መጽሐፍ ሊያነብ ይችላል፤ ወይም ማንበብ የሚያስችል የእውቀት ደረጃ ይኖረዋል።

 

ተማሪው በዚሁ በንባብ ክፍል ሌሎችንም የቃል ትምህርቶች ይማራል እነዚህም ከዘወትር ጸሎትት (አአትብ ገጽየ ብሎ) ጀምሮ እስከ መልክአ ኢየሱስ ድረስ ያሉትን የዘወትር ጸሎት፣ የሰባቱ ቀናት ውዳሴ ማርያም፣ አንቀጸ ብርሃን፣ መልክዐ ማርያም፣ እና መልክአ ኢየሱስ የተባሉትን የቃል ትምህርቶች በቃሉ ይማራቸዋል፤ ወይም ያጠናቸዋል።

 

የንባብ ክፍል መማሪያዎች በመሠረታዊነት ሦስት ሲሆኑ

·        የፊደል ገበታ

·        የዮሐንስ መልእክት 1ኛ እና

·        መዝሙረ ዳዊት ናቸው


የዜማ ትምህርት

ይህ ትምህርት ሦስት አበይት ክፍሎች አሉት እነሱም

1.  ጾመ ድጓ እና ድጓ፣ ምዕራፍ

2.  መዋሥዕትና ዝማሬ

3.  ቅዳሴ የሚባሉት ናቸው

በወል ስማቸው “ፀዋትወ ዜማ” ተብለውም ይጠራሉ የዜማ ክፍሎች ከዚህ በላይ ባሉት አበይት ክፍሎች ተጠቃለው ቢጠሩም በውስጣቸው ብዙ ንዑሳን ክፍሎችና አርእስት ይገኙባቸዋል።

ተማሪው የዜማ ትምህርቱን “ሰላም ለኪ” ይልና በውዳሴ ማርያም ዜማ ትምህርቱን ይጀምራል፤ በመቀጠልም ጾመ ድጓ፣  መዝገበ ድጓ፣ መዋሥዕት፣ ዝማሬ፤ አቋቋም - ዝማሜ፣ መረግድ፣ ጽፍት ወዘተ ይማራል። ማለትም

·        ጾመ ድጓ

·        ድጓ (መዝገበ ድጓ)

·        መዋሥዕት

·        ዝማሬ

·        አቋቋም - ዝማሜ፣ መረግድ፣ ጽፋት

·        ቅዳሴ ወዘተ የሚባሉትን ይማራል

ተማሪው እነዚህን እና ሌሎችንም ያልተጠቀሱ ንዑሳን የዜማ አይነቶችን ተምሮ ሲያጠናቅቅ “የፀዋትወ ዜማ” ባለሙያ ይባላል። “የቅዳሴ” ትምህርት ከሌሎቹ የዜማ ክፍሎት ተለይቶ ሥጋውና ደሙ የሚለወጥበት የአምልኮት ጸሎት ነው። የፀዋትወ ዜማ ደራሲ “ኢትዮጵያዊው ቅዱስ ያሬድ” ሲሆን የዜማው ዓይነት ግእዝ እዝል እና አራራይ ተብሎ በሦስት የተከፈለ ነው። በልዩ ልዩ የዜማው ክፍሎት የሚገኙት ሁሉ ከብሉያት፣ ከሐዲሳትና ከሊቃውንት መጻሕፍት የተወሰዱና ተብራርተው የሚገለጹ ናቸው።

የቅኔ ትምህርት

የቅኔ ትምህርት የሚጀምረው የግእዝን ቋንቋ በመማር ነው፣ ተማሪው መጀመሪያ የግእዝን ቋንቋ የአማርኛ ትርጉም እና የቃላቱን መዋቅር ባሕርይ ሥራና ጠባይ ወዘተ ይማራል፤ በመቀጠልም አብሮ ከቋንቋው ጥናት ጋር የቅኔን መንገድ እና መዋቅር መምህሩ መሚነድፍለት መዋቅር ድርሰት እየደረሰ ቅኔን ይፈጥራል።

ቅኔ 9 አበይት ክፍሎች አሉት፤ እነሱም የሚከተሉት ናቸው።

1.  ጉባኤ ቃና

2.  ዘአምላኪየ

3.  ሚበዝኁ

4.  ዋዜማ

5.  ሥላሴ

6.  ዘይእዜ

7.  መወድስ

8.  ክብር ይእቲ

9.  ዕጣነ ሞገር የሚባሉት ናቸው

ከነዚህም ሌላ ሣህልከ፣ሕንፄሃ፣አጭር ዋዜማ፣አጭር መወድስ(ኵልክሙ) የሚባሉ አሉ።

ተማሪው በአንዱ ክፍል በተሳካ ሁኔታ የዜማ ልኩን እና ምሥጢሩን ጠብቆ አገባቡን አስማምቶ ጸያፉን ለይቶ የተሟላ ቅኔ ማቅረብ ሲችል ወደ ሚቀጥለው እያለፈ ወይም እየተሸጋገረ እስከ ዘጠነኛው ክፍል ይደርሳል፤ ከዚህ በኋላ ተማሪው በቤተ ክርስቲያን መቀኘት ይጀምራል።

ቅኔ ከጥንት ጀምሮ የነበረ በብሉይ ኪዳንና በአዲስ ኪዳንም የተነገረለት ቢሆንም ኢትዮጵያዊ ይዘት ያለውን ቅኔና የቅኔ መዋቅር የደረሱ ቅዱስ ያሬድና ዮሐንስ ገብላዊ የተባለው ሰው እንደሆኑ ሊቃውንት ይመሠክራሉ።

 

የትርጓሜ መጻሕፍት

ትርጓሜ መጻሕፍት የሚባለው የትምህርት ክፍል ከስያሜው እንደምንረዳው የቅዱሳት መጻሕፍትን ተደራራቢ ትርጉም እና ምሥጢር በማመሥጠርና በማራቀቅ ታሪካዊ ምንጫቸውንና ማስተላለፍ የሚፈልጉትን መንፈሳዊ መልእክት በመረዳት ማስረዳት ነው፤ የትርጓሜ መጻሕፍት ትምህርትን መማር የሚችለው የቅኔ ትምህርትን የተማረ ተማሪ ብቻ ነው።

ትርጓሜ መጻሕፍት የሚባለው የትምህርት ክፍል በአራት አበይት ክፍሎች ይከፈላል፤ እነሱም ከዚህ በታች በተራ በቅደም ተከተል የተጠቀሱት ናቸው።

1.  መጻሕፍተ ብሉያት - 46ቱ የበሉይ ኪዳን መጻሕፍት

2.  መጻሕፍተ ሐዲሳት - 35ቱ የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት

3.  መጻሕፍተ ሊቃውንት - ሐይማኖተ አበው፣ ፍትሐ ነገሥት፣ አቡሻክር (ባህረ ሐሳብ)

4.  መጻሕፍተ መነኮሳት - ማርይሳቅ፣ ፊልክስዮስ፣ አረጋዊ መንፈሳዊ

በነዚህ የትምህርት ደረጃዎች ሁሉ መምህራኑ የእምነትን የገብረ ገብነትን እና የትህትናን ባጭሩ የመልካም ሥነ ምግባርን ትምህርት ያስተምራሉ። እነዚህም

·        ፈሪሀ እግዚአብሔርን- እግዚአብሔርን መፍራት

·        ኀፊረ ገጽን - ታላላቆችን ማክበርና በአክብሮት መፍራት

·        አትሕቶ ርእስን - በታላላቆች ፊት በትህትና ራስን ዝቅ አንገትን ደፋ ማድረግ

·        ገቢረ ሠናይ - መልካም ነገርን መሥራት ወይም ማድረግ ወዘተ ናቸው።

·        ምንጭ፡ “ትዝታዬ” መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ

የመጻሕፍትን ትርጓሜ ትምህርት የጀመሩት ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት እንደሆኑ የመጻሕፍት ትርጓሜ ሊቃውንት ይተርካሉ።

 

ልዑል አምላክ ማስተዋሉን ያድለን

ከአውደ ጥናት ዘግእዝ