Friday, February 14, 2020

የቃል ትምህርት: ጸሎተ ሃይማኖት በልሣነ ግእዝ/የሃይማኖት ጸሎት


ጸሎተ ሃይማኖት

ነአምን በአሐዱ አምላክ እግዚአብሔር አብ አኃዜ ኵሉ ገባሬ ሰማያት ወምድር ዘያስተርኢ ወዘኢያስተርኢ።

ወነአምን በአሐዱ እግዚእ ኢየሱስ ክርስቶስ ወልደ አብ ዋሕድ ዘህልው ምስሌሁ እምቅድመ ይትፈጠር ዓለም ብርሃን ዘእምብርሃን አምላክ ዘእምአምላክ ዘበአማን ዘተወልደ ወአኮ ዘተገብረ ዘዕሩይ ምስለ አብ በመለኮቱ ።

ዘቦቱ ኵሉ ኮነ ወዘእንበሌሁሰ አልቦ ዘኮነ ወኢምንትኒ ዘበሰማይኒ ወዘበምድርኒ። ዘበእንቲአነ ለሰብእ ወበእንተ መድኀኒትነ ወረደ እምሰማያት። ተሰብአ ወተሠገወ እመንፈስ ቅዱስ ወእማርያም እምቅድስት ድንግል

ኮነ ብእሴ ወተሰቅለ በእንቲአነ በመዋዕለ ጲላጦስ ጴንጤናዊ ። ሐመ ወሞተ ወተቀብረ ወተንሥአ እሙታን አመ ሣልስት ዕለት በከመ ጽሑፍ ውስተ ቅዱሳት መጻሕፍት። ዐርገ በስብሐት ውስተ ሰማያት ወነበረ በየማነ አቡሁ ዳግመ ይመጽእ በስብሐት ይኰንን ሕያዋነ ወሙታነ ወአልቦ ማኅለቅት ለመንግሥቱ።

ወነአምን በመንፈስ ቅዱስ እግዚእ ማኅየዊ ዘሠረጸ እምአብ ንስግድ ሎቱ ወንሰብሖ ምስለ አብ ወወልድ ዘነበበ በነቢያት። ወነአምን በአሐቲ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እንተ ላዕለ ኵሉ ጉባኤ ዘሐዋርያት።

ወነአምን በአሐቲ ጥምቀት ለስርየተ ኀጢአት። ወንሴፎ ትንሣኤ ሙታን ወሕይወተ ዘይመጽእ ለዓለመ ዓለም።

መጻሕፍቶቼን ለመግዛት የሚከተለውን ሊንክ ይጠቀሙ                                                                                                                                          

ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ይተዋወቁ

የተሰኘው ይህ መጽሐፍ ሦስት ምዕራፎችንና አሥር አበይት  ክፍሎችን የያዘ ሲሆን በመጽሐፍ ቅዱስ ዙሪያ በአማርኛ ቋንቋ  ከተጻፉ መጻሕፍት ሁሉ ባቀራረቡና በይዘቱ ፍፁም 
የመጀመሪያው ነው ። ስለመጽሐፍ ቅዱስና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስላለው ሁሉ በዚህ መጽሐፍ ተካቶ ይገኛል  በቂ ግንዛቤ ከሌላቸው  ጀማሪዎች እስከ መጽሐፍ ቅዱስ መምህራን ድረስ ከዚህ  መጽሐፍ የማይለካ ዘርፈ ብዙ እውቀትን ያገኛሉ ፤ ይማሩበታል ያስተምሩበታልም  




ስለዚህ ስለእምነትዎ በሚገባ በማወቅም ሆነ በማሳወቅ ራሰዎን  ቤተሰበዎንና ሕብረተሰቡን ሕያው በሆነው በሕያው እግዚአብሔር ቃል ማነጽ ከፈለጉ  ስለ እያንዳንዱ እምነት መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚል ፤ የተለያዩ የሃይማኖት ተቋማት የሚቀበሉት መጽሐፍ ቅዱስ እርሰዎ ከያዙት ጋር የሚመሳሰል ወይም የሚለያይ መሆኑን ማወቅየሚሹ ከሆነ  ስለመጽሐፍ ቅዱስ የማስተማርና የመስበክ ሃላፊነት ካለብዎ  የሰንበት ትምህርት ቤት ዘማሪ  ዲያቆን  ቄስ መነኩሴ  ጳጳስ  ኤጲስ ቆጶስ ወዘተ ከሆኑ ወይም በመጽሐፍ ቅዱስ ዙሪያ ጥናት የሚያካሂዱ ከሆነ  በአጠቃላይ ፍፁም የሆነውን ሃይማኖታዊውንና ማኅበራዊውን ሕገ-መንግሥት ሊመሩበት ከወደዱ ከዘፍጥረት እስከ ራእየ-ዮሐንስ  እንዲሁም  2 የቀኖና መጻሕፍትን ጨምሮ 81  76  73 66ቱና 24  የዕብራውያን ብሉይ ኪዳን የሚገኙ መጻሕፍት ሁሉ በቀላልና ልዩ በሆነ ዘመዊ አቀራረብ የመጽሐፉ ጸሐፊ  የተጻፈበት ዘመንና ቦታ  የመጽሐፉ ፍሬ-ሐሣብ ባጭሩ  የመጽሐፉ ጠቅላላ ይዘት ባጭር ትንታኔ ምርጥ ጥቅሶች  ልዩና ያልተለመዱ  እንዲሁም የመጽሐፉ መልዕክት በሚሉ መሠረታውያን አርእስት የያንዳንዱመጽሐፍ ይዘት ማራኪ በሆነ መንገድ የመጽሐፉን ጠቅላላ ሐሣብ ባጭሩ ተምሮ በሰፊው  መረዳት በሚያስችል ዘዴ ቀርቧል 

በእኔ እይታ የክርስትና እምነት ተከታይ የሆነ ሁሉ ከልጅ እስካዋቂ  ይህንን መጽሐፍ ሊይዝ ይገባልእላለሁ  በመሆኑም እርሰዎም ከመጽሐፍ ቅዱሰዎ ጋር ተዋውቀው ያስተዋውቁት እላለሁ 

"ልሣነ ግእዝ የጋራ ቋንቋችን 

"Lisane Ge'ez Yegara Quanquachin" is a study book for Ge'ez Language. This book is part one and teaches Ge'ez language for Amharic speakers however, includes also some basic English grammars and vocabularies to help the people who are interested to learn some basic Ge'ez words.


 ይህ "ልሣነ ግእዝ የጋራ ቋንቋችን የተሰኘው መጽሐፍ በአቀራረቡ ለየት ያለ ቀላልና በጣም ዘመናዊ የሆነ አቋራጭ የትምህርት አሰጣጥ ዘዴን የተከተለ ነው።

ከዚህ መጽሐፍ የግእዝን ቋንቋ በአማርኛ የሚማሩ ሲሆን መጠነና የሆነ የእንግሊዘኛ ቃላትንና አገባቦችንም ያስተምራል። ይህ መጽሐፍ በመሠረታዊነት የተዘጋጀው ቋንቋውን ምንም ለማያውቁ ጀማሪዎችና መጠነኛ ግንዛቤ ኖሯቸው ሰዋስዋዊ አካሄዱን ግን ለማያውቁ ሲሆን ከዚያም በላይ የእውቀት ደረጃ ላሉም ቢሆን በተለይ የአገባብ መዋቅሮችን በተመለከተ ሰፊ ግንዛቤን እንዲሰጥ ታስቦ ነው።

መጽሐፉን ካህናት፤ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች፤ በየአብያተ ክርስቲያናት ሕጻናትንና ወጣቶችን በመሰብሰብ የእምነትንና የሥነ ምግባርን ትምህርት የሚያስተምሩ መምህራን ለማስተማሪያነትም ሆነ የግል እውቀትን ለማዳበር እንዲሁም በማነኛውም የቋንቋ ጥናት ላይ የሚገኙ ተማሪዎች የቋንቋን አካሄድ፤ የቃላትን ቅንብርና አገባብ ለመገንዘብ ሊጠቀሙበት ይችላሉ። ለወጣንያንና ለማዕከላውያን የተዘጋጀ 1ኛ መጽሐፍ እንደ መሆኑ መጠንም በውስጡ የሚገኘው እያንዳንዱ ርእስ የተሰጠው ትርጉም፤ አገልግሎትና ትንታኔ ያለቀለት ሳይሆን ለክፍል አንድ የተመጠነ ብቻ ነው።

 ማለትም በክፍል ሁለትና በቀጣዮቹም ክፍሎች ትምህርቱ እየሰፋና እያደገ ወይም እየጨመረ የሚሄድ ነው። ስለዚህ አንድ ቃል ወይም አገባብ እናንተ የምታውቁትን ሁሉ አካቶ ባለመገኘቱ የተረሣ ወይም ሳይታወቅ የታለፈ እንዳይመስላችሁ፤ ለክፍል አንድ ተመጥኖ የቀረበ ስለሆነ ብቻ ነው። ለወደፊቱ በእኔ የሚዘጋጁ የግእዝ መማሪያ መጻሕፍት ከዚህ መጽሐፍ የሚቀጥሉ እንጅ ይህንን ክፍል የማያካትቱ ስለሚሆኑ የቋንቋው ሙሉ ፍላጎት ያለው ሁሉ ከዚህ ከመሠረታዊው ትምህርት መጀመር አማራጭ የሌለው በመሆኑ ይህን መጽሐፍ ማግኘት ይኖርበታል ብየ አምናለሁ። እንደዚህ ከሆነ ማለትም መሠረቱን በሚገባ መገንዘብ ከቻላችሁ ጽኑ እና በአለት ላይ የተመሠረተ መሠረት ስለሚኖራችሁ ቀጣዩ ትምህርት በጣም ቀላል እና ግልጽ እንደ ሚሆንላችሁ አልጠራጠርም።

Monday, February 10, 2020

“ነአኵተከ እግዚኦ ወንሴብሐከ..” የሚባለው የዘወትር ጸሎት በግእዝ ቋንቋ


ነአኵተከ

ነአኵተከ ፡ እግዚኦ ፡ ወንሴብሐከ ፡ ንባርከከ ፡ እግዚኦ ፡ ወንትአመነከ ። ንገኒ ፡ ለከ ፡ እግዚኦ ፡ ወንትቀነይ ፡ ለስምከ ፡ ቅዱስ ። ንሰግድ ፡ ለከ ፡ ኦ ፡ ዘለከ ፡ ይሰግድ ፡ ኵሉ ፡ ብርክ ፡ ወለከ ፡ ይትቀነይ ፡ ኵሉ ፡ ልሳን ። አንተ ፡ ውእቱ ፡ አምላከ ፡ አማልክት ፡ ወእግዚአ ፡ አጋዕዝት ፡ ወንጉሠ ፡ ነገሥት ፡ አምላክ ፡ አንተ ፡ ለኵሉ ዘሥጋ ፡ ወለኵላ ፡ ዘነፍስ ፡ ወንጼውዐከ ፡ (ንሕነ ፡) በከመ ፡ መሐረነ ፡ቅዱስወልድከ ፡ እንዘ ፡ ይብል ፡ አንትሙሰ ፡ ሶበ ፡ ትጼልዩ ፡ ከመዝ ፡ በሉ  ::        
                                             

Sunday, February 2, 2020

አስተርዕዮታ ለማርያም ድንግል

አስተርዕዮታ ለማርያም ድንግል


በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ

አምላካችን እግዚአብሔር በሰላም እና በጤና ጠብቆ ከዕድሜያችን ተጨማሪ የሆነችውን ይህችን ልዩ ዕለት ያለ ምንም ዋጋ በነፃ በመስጠት የእናቱን እና የእናታችንን የቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያም የዕረፍቷን መታሰቢያ በአል እንድናከብር ስለፈቀደ የተመሰገነ ነው። አሁንም በተለመደው ቸርነቱ የንስሐ ዕድሜን ጨምሮልን ለሚቀጥለው ዓመት በሕይወት አቆይቶን ይህንን በአል ለማሰብ እና ለማክበር ያብቃን አሜን።


በመግቢያችን እንዳየነው አስተርዕዮታ ለማርያም እያልን በየዓመቱ ጥር 21 ቀን የምናስበው በአል የእመቤታችን የቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያም የዕረፍት ወይም ከዚህ ዓለም በሞተ ሥጋ የተለየችበትን በአል ነው።

አዎ! በሥነ ፍጥረት ታሪክ አቻ ወይም አምሳያ ያልተገኘላት፥ ከምድራውያን ሰዎችም ሆነ ከሰማያውያን መላእክት የሚመስላት የሌለ፣ በፍጡር ሕሊና ሊመረመር በማይችል ምሥጢር ሰማይና ምድር የማይወስኑትን ሕያው አምላክ ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን ፀንሣ የወለደች፣ ያሳደገችም ልዩ ፍጥረት እንደ ማነኛውም ፍጡር በሞተ ሥጋ ተለየች ማለት ለሰዎች አእምሮ ይከብዳል። ለዚህም ነው ታላቁ የዜማ ደራሲ ቅዱስ ያሬድ በሁኔታው እየተደነቀ “ሞትሰ ለመዋቲ ይደሉ ሞታ ለማርያም ያአጽብ ለኵሉ”

= ለሚሞት ሞት ይገባል፤ ነገር ግን የማርያም ሞት ሁሉን ያስደንቃል(ያስገርማል)  በማለት ለማነኛውም ሰብአዊ ታሪክ ላለው፣ ሞት ያለ፤ የነበረና የሚኖር ስለሆነ ተገቢ ነው፤ ነገር ግን የተለየና በተፈጥሮ ታሪክ ሊፈጸም የማይችል ታሪክ ለተሰጣት ለእመቤታችን የሆነው ሞት አስደናቂ የሆነበት።

ምክንያቱም፡ ለእመቤታችን የተሰጠው ለማንም ፍጡር አልተሰጠም፤ የእሷን ዓይነት ምርጫ የተመረጠ የለም፤ ዓለም ከመፈጠሩ በፊት ታሪክ ያላት፤ ዓለም ከተፈጠረም በኋላ ከመወለዷ በፊት ምርጫዋ የተሰበከላት፤ ስለ እርሷ ያልተነበየ ነቢይ የሌለ፤ ለሰብአዊ ፍጡር ሁሉ ለአምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመናት የሕሊና ተስፋ የሆነች፤ አሁንም በአማላጅነቷ ዓለም የሚማፀናት ልዩ ፍጥረት፤
ዓለምን ለማዳን ኃያሉን አምላክ በድንግልና ጸንሣ በድንግልና እንደምትወልድ አዲስ እና ለዓለም እንግዳ የሆነ፣ በሥነ ተፈጥሮ ታይቶም ተሰምቶም የማይታወቅ፣ የተፈጥሮን ሕግ የጣሰ ታሪክ በነቢያትና በመላእክት የተነገረላት፤
የትንቢቱ ፍጻሜ በተቃረበ ጊዜ በቀጥታ ከእግዚአብሔር የሚያበሥር መልአክ ወደሷ የተላከላት፤ ዓለም የሚጠባበቀው የድኅነት ሥራ በእርሷ እናትነት እንደሚፈጸም በግልጽ ያበሠራት።

ታዲያ ሁሉን ማድረግ የሚቻለው፣ የሚሆነውን እንዳይሆን፣ የማይሆነውን እንዲሆን ወይም የሚቻለውን የማይቻል፤ የማይቻለውን የሚቻል የሚያደርገውን፤ ለሚያደርገው ሁሉ ለምን በማለት ማንም የማይጠይቀውን ሁሉን ቻይ አምላክ ለወለደች እናት እንዴት ሞት ተገባት? ሲል ነበር ቅዱስ ያሬድ “ያስደንቃል፤ያስገርማል” በማለት የገለጸው። እውነትም ያስገርማል!

በሰብአዊ ባሕል ሰው ከዚህ ዓለም በሞት ሲለይ ከኀዘን ቀጥሎ የሚደረግለት ነገር ቢኖር ከልደት እስከ ሕልፈት ያሳለፈውን ምድራዊ ታሪክ መተረክ ነው። ታዲያ የእመቤታችን የዕረፍት ታሪክ ከልደቷ ወይስ ከወላጆቿ  ከቅዱስ ኢያቄምና ከቅድስት ሐና ልደት! ከየት ነው መጀመር ያለብን?
ምክንያቱም፣ የእመቤታችን ታሪክ ከታሪክ በፊት ነው። ዓለም ከመፈጠሩ፣ ጊዜ ከመቆጠሩ በፊት፤ ዓለም የራሱን ታሪክ ከመጀመሩ በፊት እመቤታችን አስደናቂ ታሪክ ነበራት፤ ታዲያ ከየት ይጀመር? ያዐፅብ ለኵሉ” እውነትም ያስደንቃል።

ታሪኳ ልዩ፣ ምርጫዋ አስደናቂ፣ ከፍጡራን ሕሊና በላይ ቢሆንም “እስመ አልቦ ነገር ዘይሰአኖ” ብለን በማለፍ የእኛ ሕሊና በሚችለው መጠን በሚገባን እና በገባን ደረጃ መጻሕፍት የሚነግሩንን ታሪክ መናገራችን ግድ ነው። ለዚህም ነው ቅዱሳን አባቶች ለእመቤታችን ሰብእና ምሳሌ ስላጡለት “በመኑ ወበአምሳለ መኑ ናስተማስለኪ” = በማን እና በምንስ እንመስልሻለን” በማለት የሚናገሩ።

ስለዚህ የእመቤታችንን ታሪክ ግልጽና ቀላል ለማድረግ በ 3 ዐበይት ክፍሎች ከፋፍየ ባጭሩ ለማስረዳት እሞክራለሁ ። ምክንያቱም ረጅሙን የእመቤታችንን ታሪክ ተርኮ መጨረስ የሚችል ማንም የለም፣ ቅዱሳንም አልጨረሱትም። በመሆኑም እኔም አልሞክረውም።

የመጀመሪያውን የታሪክ ክፍል

“እግዝእትነ ማርያም ነበረት እምቅድመ ዓለም በሕሊና አምላክ” የሚለው ዐረፍተ ነገር ይገልጸዋል ይህ ጽሁፍ በተለያዩ የቤተ ክርስቲያናችን ቅዱሳት መጻሕፍት ተጽፎ ይገኛል። ቃሉ ወደ አማርኛ ሲተረጎም እመቤታችን ከዓለም በፊት በአምላክ ሕሊና ወይም ሐሳብ ውስጥ ነበረች ማለት ነው።

ዓለም ማለት ቃሉ ግእዝ ሲሆን በቀጥተኛ አማርኛ ፍጥረት ማለት ነው፤ ስለዚህ ከሥነ ፍጥረት በፊት ማለትም አዳም ተፈጥሮ በድሎ በኃጢአት ከመውደቁ በፊት እመቤታችን በአምላክ ሐሣብ ለድኅነተ  ዓለም ለሥጋዌው ተመርጣ ነበር ማለት ነው።
ይህ ምሥጢር በሰዎች አእምሮ በእኛ አቅም የሚመዘን ከሆነ መቸም ቢሆን ሊገባን አይችልም፤ በመሆኑም የሚመዘነው ሁሉን ማድረግ በሚችለው ለሚያደርገው ሁሉ ለምን? ብሎ ጠያቂ በሌለው ልዑል አምላክ አቅም ብቻ ነው። “እስመ አልቦ ነገር ዘይሰአኖ” የሚሳነው ነገር የለም።

እነ ነቢዩ አርምያስ፣ ኢሳይያስ መጥምቁ ዮሐንስ ሌሎችም ቅዱሳን ገና ሳይወለዱ በእናታቸው ማሕፀን እግዚአብሔር መርጧቸዋል። አንዱን ብቻ ለመጥቀስ ያህል ነቢዩ ኢሳይያስ በ49ኛው ምዕራፍ አምላኩ አስቀድሞ እንዴት እንደመረጠው  “እም ከርሠ እምየ ሰመየኒ ስምየ፣ ወረሰዮ ለአፉየ ከመ መላፂ በልህ፣ ወከደነኒ ታሕተ ጽላሎተ እዴሁ” = በእናቴ ማኅፀን ስሜን ኢሳይያስ ብሎ ሰየመኝ፣ አንደበቴን እንደ ተሳለ ምላጭ አደረገው(አንደበተ ርቱዕ አደረገኝ) በእጁ ጥላ ሥርም ጠበቀኝ ። በማለት ይገልጸዋል።
ታዲያ ከነቢያት የምትበልጥ ከመላእክትም የምትልቅ ቅድስተ ቅዱሳን የአምላክ እናት በፈጠራትና ለታላቅ የሥጋዌው ምሥጢር ባቀዳት በአምላኳ ከዓለም በፊት መመረጧ ምን ያስደንቃል። ምንም የሚያስደንቅ የሚያስገርም ነገር የለም ምክንያቱም በአምላክ እቅድ የተለየ ክብር የተሰጣት የተለየች ፍጡር ናት፤ የተለየ ነገር በእርሷ ብቻ መታየቱ የአምላክ ልዩ ጥበብ ነው።

ሁለተኛው የታሪክ ክፍል

“በሐሙስ ዕለት ወበመንፈቃ ለዕለት እትወለድ እምወለተ ወለትከ ወእትቤዘወከ በመስቀልየ ወበሞትየ” የሚለው ቃል ኪዳን ወይም ዐረፍተ ነገር ይገልጸዋል።  ሁለተኛው የታሪክ ክፍል ዓለም ከተፈጠረ በኋላ  በቅዱሳን ነቢያት አንደበት በሰፊው የተተረከ የታሪክ ክፍል ነው። አዳም በደለ በደሉም የሞት ዋጋን የሚያስከፍል ነበረ፤ የዚህ ዕዳ ተካፋይም አዳም በደሎ ሞት ሳይፈረድበት በፊት በአምላክ ሕሊና ከነበረቺው ከቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያም በስተቀር ሰብአዊ ፍጡር ሁሉ ነበር።

ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ከወላጆቻችን ከአዳምና ከሔዋን ጀምሮ በወላጆቹ በደል የሞተው ዓለም በአምላክ ሕሊና ለድኅነተ ዓለም አምላክ ለሥጋዌው የመረጣትን የቅድስተ ቅዱሳንን መወለድ በተስፋ ይጠባበቅ ነበር።

“አንቲ ውእቱ ተስፋሁ ለአዳም አመ ይሰደድ እምገነት” = በሠራው ኃጢአት ምክንያት ከገነት በተባረረ ጊዜ እንደ ገና ወደ ክብሩ ለመመለስ ተስፋ የሚያደርገው አንቺን ነበር። ምክንያቱም ዓለምን የሚያድነው ሁሉን ማድረግ የሚችለው ኃያሉ አምላክ ቢሆንም ይህንን የድኅነት ሥራ ከእርሷ በመወለድ በፍጹም ተዋሕዶ እንደሆነ አስቀድሞ ስለ ነገረው ነበር።

በመቀጠልም ብዙ ነቢያት በልዩ ልዩ ምሳሌ ስለ እመቤታችን ቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያም ተነበዩ በ4800 ዓ/ዓ አካባቢ ነቢዩ ኢሳይያስ በግልጽ “ናሁ ድንግል ትፀንስ ወትወልድ ወልደ ወትሰምዮ ስሞ አማኑኤል ዘበትርጓሜሁ እግዚአብሔር ምስሌነ” = እንሆ ድንግል ትፀንሳለች ወንድ ልጅም ትወልዳለች ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች፤ አማኑኤል ማለትም እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ማለት ነው። በማለት በማያሻማ መልኩ ተናገረ። ታዲያ ይህ የነቢዩ ትንቢት እመቤታችን ከመወለድዋ ማለትም ከ5486 ዓመተ ዓለም 700 ዓመታትን ቀድሞ የተነገረ ትንቢት ስለሆነ እመቤታችን ከዓለም በፊት በአምላክ ሕሊና የተሟላ ታሪክ ነበራት የሚለውን እውነት ያረጋግጥልናል። ምክንያቱም ነቢዩ ሲተነብይም እመቤታችን አልነበረችም ወላጆቿም አልተወለዱም።

ይህ የነቢዩ የኢሳይያስ ቃል “ድንግል” አለ እንጂ ድንግል ማርያም ስለማይል በምን እናውቃለን ለምትሉና በትክክል ለእመቤታችን ለቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያም መነገሩን ማረጋገጥ ለምትፈልጉ ወንጌላዊው ማቴዎስ በምዕራፍ 1፡ ቍጥር 20 ጀምሮ
“ወዝ ኵሉ ዘኮነ ከመ ይትፈጸም ዘተብህለ እምኀበ እግዚአብሔር በነቢይ እንዘ ይብል። “ናሁ ድንግል ትፀንስ ወትወልድ ወልደ ወይሰመይ ስሙ አማኑኤል” ዘበትርጓሜሁ እግዚአብሔር ምስሌነ።

= ከእርሷ የተፀነሰው ከመንፈስ ቅዱስ ነውና እጮኛህን ማርያምን ለመውሰድ አትፍራ። ልጅም ትወልዳለች እርሱ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋልና ስሙን ኢየሱስ ትለዋለህ። በነቢይ ከጌታ ዘንድ እንሆ ድንግል ትፀንሳለች ልጅም ትወልዳለች ስሙንም አማኑኤል ይሉታል የተባለው ይፈጸም ዘንድ ይህ ሁሉ ሆኗል፣ ትርጓሜውም እግዚአብሔር ከእኛ ጋር የሚል ነው። በማለት ትንቢተ ኢሳይያስ ም 7 ቍ 14ን ጠቅሶ ይነግረናል።

 ይህ ቃል መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል የተናገረው ወንጌላዊው ቅዱስ ማቴዎስ የጻፈው የማያጠራጥር ምስክርነት ነው።

ሦስተኛው የታሪክ ክፍል

“ወበሳድስ ወርኅ ተፈነወ ገብርኤል መልአክ እምኀበ እግዚአብሔር ኀበ አሐቲ ሀገር ዘገሊላ እንተ ስማ ናዝሬት። ኀበ ድንግል እንተ ተፍኅረት ለብእሲ ዘስሙ ዮሴፍ ዘእም ቤተ ዳዊት ወስማ ለይእቲ ድንግል ማርያም። ወቦአ መልአክ ኀቤሃ ወይቤላ ተፈሥሒ ፍሥሕት ኦ ምልእተ ጸጋ  እግዚአብሔር ምስሌኪ ወቡርክት አንቲ እምአንስት። ወርእያ ደንገፀት እምቃሉ።”

= በስድስተኛውም ወር መልአኩ ገብርኤል ናዝሬት ወደምትባል ወደ ገሊላ ከተማ ከዳዊት ወገን ለሆነው ዮሴፍ ለሚባል ሰው ወደ ታጨች ወደ አንዲት ድንግል ከእግዚአብሔር ዘንድ ተላከ፣ የድንግሊቱም ስም ማርያም ነበረ። መልአኩም ወደ እርሷ ገብቶ ደስ ይበልሽ ጸጋ የመላብሽ ሆይ ጌታ ከአንቺ ጋር ነው፤ አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ አላት።

ይህ ቃል እመቤታችን ቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያም ዓለም ከመፈጠሩ በፊት በአምላክ ሕሊና የመኖሯን አላማ፣ ዓለም ከተፈጠረ በኋላ ሲጠበቅ የነበረውን የሥጋዌ እና የድኅነተ ዓለም ተስፋ የነቢያትን ትንቢት ሁሉ እውን የሚያደርግ፤ በእመቤታችን ቅድመ ታሪክ ሁሉ ሲጠራጠሩ ለነበሩት ተግባራዊ እውነት ነበር።

የእመቤታችን ምርጫ ልዩና የተፈጥሮ ሕግን የጣሰ፣ በሥነ ፍጥረት ታሪክ ውስጥ ታስቦም ተፈጽሞም የማያውቅ በመሆኑ ለራሷ ለእመቤታችን ጭምር ፈጥኖ የሚታመን አልነበረም፤ በመሆኑም እመቤታችን ቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያም ከእግዚአብሔር ዘንድ በቀጥታ ተልኮ ከመጣው ከመላእክት አለቃ ከመልአኩ ከቅዱስ ገብርኤል ጋር ተከራክራ ነበር፤ እንዴት እንደዚህ ይሆናል በማለት ጠይቃ ነበር።

“ወርእያ ደንገፀት እምቃሉ ወኀለየት ወትቤ እፎኑ እንጋ ዘከመዝ አምኃ ይትአምኁ”
“እፎኑ ይከውነኒ ዝንቱ እንዘ ኢየአምር ብእሴ”

= እርሷም ባየቺው ጊዜ ከንግግሩ በጣም ደነገጠችና ይህ እንዴት ያለ ሰላምታ ነው? ብላ አሰበች።

“ወአውሥአ መልአክ ወይቤላ መንፈሰ እግዚአብሔር ቅዱስ ይመጽእ ላዕሌኪ ወኀይለ ልዑል ይጼልለኪ ወዘኒ ይትወለድ እምኔኪ ቅዱስ ውእቱ ወይሰመይ ወልደ እግዚአብሔር ልዑል…”

“እስመ አልቦ ነገር ዘይሰአኖ ለእግዚአብሔር” እመቤታችንን ያሳመናት ቃል ይህ ነበረ። ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለም። አዎ የለም “በከመ ፈቀደ ይገብር ወበከመ ሐለየ ይፌጽም”

እመቤታችን ከፍጥረት ሁሉ የተለየ ጸጋ የተለየ ምርጫ ስላላት ከፍጡራን ሁሉ የተለየ ክብር ተሰጥቷታል፤ ቅድስተ ቅዱሳን ማለትም ከቅዱሳን ሁሉ ይልቅ የተቀደሰች ማለት ነው፤ ከቅዱሳን መላእክትም ሆነ ከቅዱሳን ሰዎች እንደ እመቤታችን ያለ ፍጡር አልተገኘም ። ቅዱስ ኤፍሬም በድርሰቱ “የአቢ ክብራ ለማርያም እምኵሎሙ ቅዱሳን፤ ይእቲ ተዐቢ እምኪሩቤል፤ ወትፈደፍድ እምሱራፌል፣ እስመ ኮነት ታቦተ ለአሐዱ ዘእም ቅድስት ሥላሴ” በማለት ስለ እመቤታችን ልዩ ፍጡርነት እና ክብር ይናገራል።

ኪሩቤል እና ሱራፌል የሚባሉት የአምላክን መንበር ተሸክመው ቅዱስ ቅዱስ እያአሉ የሚኖሩ ናቸው አምላክን በዐይናቸው እንኳን ማየት አይችሉም ፤ እመቤታችን ግን ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን በማሕጸኗ ተሸከመቺው። ለዚህም ነው ከሁሉም የምትልቀው። አባ ሕርያቆስም “ነጸረ አብ እምነ ሰማይ ወኢረከበ ዘከማኪ” በማለት እግዚአብሔር ከሰማይ ሆኖ ዓለሙን ሁሉ ተመለከተ አየ እንዳንቺ ያለ አላገኘም የቅድስናሽን ደም ግባትም ወደደ አንድ ልጅንም ወደ አንቺ ላከ። ይላል።

በመግቢያየ እንደ ተናገርኩት ስለ እመቤታችን የተነገረውን ተርኮ የሚጨርስ ባለመኖሩ። እመቤታችን ቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያም የተነገረው የተተነበየው ሁሉ እውን ከሆነ በኋላ፤ ከእግዚአብሔር በቀጥታ የተላከው መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል የተናገረውን አስደናቂ መልእክት፤ ቅድስት ኤልሳቤጥ በመንፈስ ቅዱስ ተመልታ የሰጠቺውን ምስክርነት፤ ከሰማች በኋላ፤ ለመረጣት ለአምላኳና ለልጃ ያቀረበቺውን ምስጋና በመናገርና ከወላጆቿ ከተወለደችባት ቀጽበት ጀምራ እስከ ጥር 21 ቀን 50 ዓ/ም ድረስ የነበራትን ሥጋዊ ዕድሜ ጠቅሼ ትረካየን እገታለሁ።

ወትቤ ማርያም/ ማርያምም እንዲህ አለች።

“ታዐብዮ ነፍስየ ለእግዚአብሔር ወትትሐሠይ መንፈስየ በአምላኪየ ወመድኀኒየ፤ እስመ ርእየ ሕማማ ለአመቱ ናሁ እም ይእዜሰ ያስተበፅዑኒ ኵሉ ትውልድ። እስመ ገብረ ሊተ ኀይለ ዐቢያተ ወቅዱስ ስሙ ። ወሣህሉኒ ለትውልደ ትውልድ ለእለ ይፈርህዎ። ወገብረ ኀይለ በመዝራዕቱ ወዘረወሙ ለእለ ያዐብዩ ኀሊና ልቦሙ። ወነሠቶሙ ለኀያላን እመናብርቲሆሙ አዕበዮሙ ለትሑታን። ወአጽገቦሙ እምበረከቱ ለርኁባን ወፈነዎሙ  ዕራቆሙ ለብዑላን። ወተወክፎ ለእስራኤል ቍልዔሁ ወተዘከረ ሣህሎ። ዘይቤሎሙ ለአበዊነ ለአብርሃም ወለዘርዑ እስከ ለዓለም።” ሉቃስ 1፡47

ነፍሴ ጌታን ታከብረዋለች፥
መንፈሴም በአምላኬ በመድኃኒቴ ሐሴት ታደርጋለች፤
የባሪያይቱን ውርደት ተመልክቶአልና።
እነሆም፥ ከዛሬ ጀምሮ ትውልድ ሁሉ ብፅዕት ይሉኛል፤
ብርቱ የሆነ እርሱ በእኔ ታላቅ ሥራ አድርጎአልና፤
ስሙም ቅዱስ ነው።
ምሕረቱም ለሚፈሩት እስከ ትውልድና ትውልድ ይኖራል።
በክንዱ ኃይል አድርጎአል፤
ትዕቢተኞችን በልባቸው አሳብ በትኖአል፤ 
ገዥዎችን ከዙፋናቸው አዋርዶአል፤
ትሑታንንም ከፍ አድርጎአል፤
የተራቡትን በበጎ ነገር አጥግቦአል፤
ባለ ጠጎችንም ባዶአቸውን ሰዶአቸዋል።
ለአባቶቻችን እንደ ተናገረ፥
ለአብርሃምና ለዘሩ ለዘላለም ምሕረቱ ትዝ እያለው እስራኤልን ብላቴናውን ረድቶአል።

እመቤታችን ቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያም
·        ነሐሴ 7 ቀን በ5486 ዓ/ዓ ከአባቷ ከቅዱስ ኢያቄምና ከእናቷ ከቅድስት ሐና ተፀነሰች
·        ግንቦት 1 ቀን 5486 ዓ/ዓ ተወለደች
·        ለ 3 ዓመታት በአባት በእናቷ ቤት ከቆየች በኋላ የሥዕለት ልጅ በመሆኗ በ3 ዓመቷ
ታሕሣስ 3 ቀን በ5489 ዓ/ዓ በሥዕለት ልጅነት ለቤተ መቅደስ ተሰጠች
·        ለ12 ዓመታት በቤተ መቅደስ ኖረች
·        3 ዓመት ከ 9 ወር ከ 5 ቀን በጠባቂዋ በቅዱስ ዮሴፍ ቤት፤ ከዮሴፍና ከሰሎሜ ጋር የግብፅ ስደትን ጨምሮ ኖረች
·        30 ዓመት ከ 2 ወር ከቅዱሳን ሐዋርያት ጋር ኖረች
·        15 ዓመታት ከጌታ ስቅለት በኋላ በወንጌላዊው በዮሐንስ ቤት ኖራ ጥር 21 ቀን በ50 ዓ/ም ከዚህ ዓለም በሞተ ሥጋ ተለየች።

ልመናዋ ክብሯም በእውነት ይደርብን
ይሁን ይደረግ አሜን

ከአውደ ጥናት ዘግእዝ