Sunday, May 13, 2018
Wednesday, March 21, 2018
Learn Geez Through WhatsApp Group
በአውደ ጥናት ዘግእዝ የሚሰጡ የግእዝ ቋንቋ የትምህርት ደረጃዎችና ይዘታቸው
አውደ ጥናት ዘግእዝ ክፍል ፩ዱ ለወጣንያን(ለጀማሪ)
1.
ፊደልና ስለ ፊደላት አከፋፈል - ድምጽ- ከግእዝ እስከ ሣብዕ በደንብ ግንዛቤን መስጠት
2.
አጫጭር ዐ/ነገራትን
በሚከተሉት አርእስት መሠረት የሰላምታ ቃላትና አጠቃቀማቸው
3.
ደቂቅ አገባቦችን
ትርጉማቸውና እና በዐ/ነገር እያስገቡ ማሳየት
4.
የመጠየቂያ
ቃላትንና አጠቃቀማቸውን በአጫጭር ዐ/ነገር
5. የሁለት ቃላትን አነባበብ ለምሳሌ (ሙያንና ባለ ሙያን በማያያዝ የአንድን ሰው ችሎታ ወይም ሙያ መናገር መምህር (ባለ ሙያ) ግእዝ (ሙያ)
6. አሥሩ መራሕያን እና
አጠቃቀማቸው
7. የግሥ ርባታ ከአቢይ
አንቀጽ እስከ ንዑስ አንቀጽ
8. ቁጥር ከ1 እስከ
19 ያሉ የግእዝን ቁጥሮች
9. የልምምድ ውይይት በተማሪዎች መካከል
አውደ ጥናት ዘግእዝ ለማዕከላውያን(ለመካከለኛ)፡
1.
ስምንቱ የንግግር ክፍሎች
2.
ግሥና የግሥ አወራረድ ከንኡስ አንቀጽ እስከ መጨረሻው
3.
ግልጽ የሆኑ(ግልጠ ዘ) ቅጽሎች
4.
ተውላጠ ግሥ
5.
ከግሥ የሚወጡ ዘሮች
6.
ባለቤት፤ ማሠሪያ አንቀ፤ ቅጽል፤ እና ተውሳከ ግሥ ያላቸው ዐ/ነገራትን መፍጠር
7.
የዐ/ነገራትን አካላትና ሙያ ማወቅ
8.
ደቂቅ አገባቦችን ማወቅ
9.
የልምምድ ውይይት በተማሪዎች መካከል
አውደ ጥናት ዘግእዝ ለፍፁማን(ለከፍተኛ)፡
1. አገባቦችና አጠቃቀማችው
2. 8ቱ መራኁት
3. 8ቱ አርእስት
4. 50ው ሠራዊት
5. 4ቱ አዕማድ
6. 4ቱ አሥራው
7. 4ቱ ፀዋትው
8. ጽሁፎችን ከግእዝ ወደ አማርኛ መተርጎም እና የሥነ ጽሁፍ ልምምድ
9. የልምምድ ውይይት በተማሪዎች መካከል
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
መ/ር መላኩ ነኝ ከአውደ ጥናት ዘግእዝ ነው
ስለ ትምህርት አሰጣጡና አጠቃላይ ማብራርያ የሚከተለውን ቪድዮ ያዳምጡ
ተጨማሪ ማብራርያ
ሰላም ጤና ይስጥልኝ ከአውደ ጥናት ዘግእዝ ነው
ልዑል እግዚአብሔር
ለዚች ቅጽበት በሰላም ጠብቆ ስላደረሰን የተመሰገነ ይሁን።
የግእዝ ቋንቋ ተከታታይ
ትምህርታችን ታህሣስ አንድ ቀን (ታህሣስ 10 በፈረንጆች) ይጀመራል። ስለዚህ ከዚያ በፊት ምዝገባና ክፍያችሁን ማጠናቀቅ አለባችሁ።
ክፍያውን እስከ ህዳር 30 (ታህሣስ 9 በፈረንጆች) ትከፍሉና ክፍያው የሚያዝላችሁ ግን ከጥር 1 ቀን በፈረንጆች ጀምሮ ለአንድ
ዓመት ነው፤ ስለዚህ ከጥር በፊት ያለው አንድ ወር ነጻ ነው ማለት ነው።
በትምህርቱ የተመዘገባችሁት
አብዛኛዎቻችሁ ሁላችሁም ማለት ይቻላል “በጀማሪ” ደረጃ ነው። ስለዚህ ሁለት ሰዎች ቢሆኑ ነው በመካከለኛ ደረጃ ያሉት፤ በከፍተኛ
ያለ ግን የለም።
የራሴን አስተያየት
ለመስጠት ያህል ከመጀመሪያው መጀመሩ በጣም የተሻለ ነው። ምክንያቱም መሠረቱን ማጥበቁ ወሳኝ ነው። ስለዚህ ከመጀመሪያው እንጀምራለን፤
መጀመሪያው ደግሞ ፊደል ስለሆነ ከፊደል ነው የምንጀምረው፤ ምን አልባት ፊደል ሁሉም የሚያውቀውና ስለፊደል መማር መደጋገም መስሎ
ሊታየን ይችል ይሆናል፤ ነገር ግን ብዙ የማናውቀውና የጎደለብን ነገር ያለ የማይመስለን ብዙ ሊናውቀው የሚገባ ትምህርት በፊደሎች
ውስጥ አለ። በተለይ ለግእዝ ትምህርት ስለፊደላት ሁለንተና በቃል ጭምር ማወቅና መያዝ በጣም ወሳኝ ነው። ስለዚህ የምናውቀው ነው
ብላችሁ ሳትዘናጉ መከታተል ይኖርባችሁዋል።
ግሩፑን አንድ ግሩፕ
ለጀማሪዎች አድርገን እንጀምረውና እንቀጥላለን ማለትም ክፍል አንድ የሚቀላችሁ ካላችሁ ለመካከለኞች ግሩፕ መክፈት ይቻላል፤ ክፍተኛም
ካለ እንደዚሁ በሂደት ይሆናል። ትምህርቱ ለየት ባለና ጠለቅ ባለመልኩ በያንዳንዱ ንዑስ ርእስ ጭምር የልምምድ ጥያቄዎችን በመሥራት
የሚሰጥና ቀላል፤ግልጽና በቂ ዕውቀትን የሚያስጨብጥ እንዲሆን ከፍተኛ ጥረት አደርጋለሁ።
ከናንተ የሚጠበቀው የሚሰጠውን መመሪያ በጥንቃቄ መተግበር
ነው። ይህ ትምህርት በተለይ የትምህርቱ የማስተማር ስልት በየትም ቦታ ሊታገኙት እንደማትችሉ ምንም አያጠራጥርም። ይህ ማላት ባለሙያዎች
የሉም ማለት ሳይሆን 1ኛ ያለውን ትንሺም ሆነ ብዙ ለሌሎች የማስተላለፉ ዘዴና ችሎታ የያንዳንዱ ሰብአዊ ፍጡር የየግል ልዩ ስጦታ
ነው። 2ኛው ደግሞ የቦታ፤የጊዜ፤ እና የዘመናዊ መሣሪያዎች አመች ሆነው መገኘታቸውም ሌላው ምክንያት ነው። ስለዚህ እነዚህን ሁሉ
እግዚአብሔር ስላመቻቸልን እድሉን መጠቀም የያንዳንዳችን ድርሻ ነው።
የሚሰጠው የትምህርት
ንድፍ የሚከተለውን ይመስላል
ለአንድ ዓመት ሰፋ
ባለመልኩ የሚሰጡት አበይት የትምህርት ዓይነቶች በዘጠኝ ንዑሳን ክፍሎች የተከፈሉ ሲሆኑ የሚከተሉት ናቸው። (በጣም ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ ቃላትና ትምህርቶች/ዐ/ነገራት የበለጠ ግልጽ እንዲሆንላችሁና
ተጨማሪ ዕውቀትንም ታገኙ ዘንድ ዓለም አቀፍ በሆነው በእንግሊዘኛም እንዴት እንደሚተረጎሙ እንነጋገራለን እንማራለን ይህም እንግሊዘኛን
ለሚማሩ ተጨማሪ ጥቅም ነው)
1.
ፊደልና ስለፊደል በሚለው ንዑስ ርእስ
·
ፊደል ማለት ምን ማለት እንደሆነ
እስከ መነሻው፤ ታሪክን ጨምሮ፤ ፊደል የሚጠራባቸው ልዩ ልዩ ስሞች፤ የግል፤የወል፤የደረጃ፤ ወዘተ ስያሜዎች፤ ዓይነት፤ ድምጽ፤ መኩሸ
ፊደላትና የሚለያዩባቸው፤ የሚዋሃዱባቸው፤
·
ከፊደላት ውስጥ ከፊደልነት ሥራቸው ሌላ አገልግሎትን የሚሰጡ ፊደላትን አዲስ እና ልዩ በሆነ
የአውደ ጥናት ብቻ የማስተማር ዘዴ ለይተን እንማራለን፤(ለበወ) እንዲሁም ሌሎች ከፊደላት ጋር የተያያዙ ዕውቀቶች በጥልቀት ይተነተናሉ።
·
በያንዳንዱ ንዑስ ርእስ የግንዛቤ ጥያቄ ዎች ይሰጣሉ
2.
አጫጭር ዐ/ነገራትን በሚከተሉት አርእስት መሠረት የሰላምታ ቃላትና
አጠቃቀማቸው
·
የሰላምታ ቃላትን መሠረት በማድረግ ልዩ ልዩ ትርጉሞ ያላቸውን ዐ/ነገራት መሥራት
·
ስለራሳችን ማንነት እና ታሪክ ባጭሩ መናገር እና መጻፍ
·
በምንማራቸው ዐ/ነገራት የምንጠቀምባቸውን ቃላት ትርጉም ማወቅ
·
በዐ/ነገራቱ ውስጥ የሚገኙትን ቃላትና የሥራ ድርሻቸውን ማወቅ
3.
ደቂቅ አገባቦችን ትርጉማቸውና እና በዐ/ነገር እያስገቡ ማሳየት
·
ደቂቅ አገባብ ምን ማለት እንደ ሆነ፤ አገልግሎትና ትርጉም
·
መቸና እንዴት ደቂቅ አገባቦችን እንደምንጠቀም ልዩ ልዩ ዐ/ነገራትን በመሥራት ልምምድ ማድረግ
4.
የመጠየቂያ ቃላትንና አጠቃቀማቸውን በአጫጭር ዐ/ነገር
·
የመጠየቂያ ቃላትን ትርጉም እና አጠቃቀም በዐ/ነገራት በማስገባት
·
ቦታን የሚመለከት
·
ጊዜን የሚመለከት
·
ርቀትን የሚመለከት
·
ቁጥርን የሚመለከት ወዘተ በመከፋፈል በሰፊው ልምምድ ማድረግ
5. የሁለት ቃላትን አነባበብ ለምሳሌ (ሙያንና ባለ ሙያን በማያያዝ የአንድን ሰው ችሎታ ወይም ሙያ መናገር መምህር (ባለ
ሙያ) ግእዝ (ሙያ)
·
በግእዝ ቁዋንቋ ህግ ሁለት ቃላት እንዴት ይያያዛሉ(ይናበባሉ)፤ ለምን ይናበባሉ፤
·
ሁለት ቃላትን ለማያያዝ የሚጠቅሙን ፊደላት፤
·
ሁለት ቃላትን በማያያዝ የሚገኙ ጥቅሞች
·
ሙያን፤ ባለሙያን፤ ወይም ሐብትን፤ እና ባለሐብትን ወዘተ እንዴት ማወቅ እንደሚቻል
·
ለምሣሌ፤ የክርስትና ስሞችን፤ የትምህርት ዓይነቶችን፤ ወዘተ ምሣሌ በማድረግ
በሰፊው መነጋገር
6. አሥሩ
መራሕያን እና አጠቃቀማቸው
·
መራሕያን ስምና ትርጉም፤ ብዛትና ከሌሎች ቁዋንቁዋዎች
ጋር ንፅጽር
·
አሥሩ መራህያን የሥነ ጽሁፍ ሁሉ መሠረቶች ስለሆኑ
ሙሉ በሙሉ በቃል ጭምር መያዝ አለባቸው። ስለዚህ በግእዝ፤ በአማርኛ፤ እንዲሁም በእንግሊዘኛ ይብራራሉ።
·
ለምን ስሞችን ትተን ተውላጠ ስሞችን እንደምንጠቀም፤ መቸ እንደምንጠቀም፤
በተግባር በዐ/ነገር በሰፊው እናያለን፤
·
በአሥሩም ተውላጠ ስሞች ልዩ ልዩ ምሳሌዎችን መሥራት
7. የግሥ
ርባታ ከአቢይ አንቀጽ እስከ ንዑስ አንቀጽ
·
ግሥ/አንቀጽ ስያሜ፤ ምድብና ሥራ
·
ሐላፊ ግሥ/አንቀጽ
·
ትንቢት ግሥ/አንቀጽ
·
ዘንድ ግሥ/አንቀጽ
·
ንዑስ ግሥ/አንቀጽ
·
ከሃላፊ እስከ ንዑስ ያሉትን አናቅጽ በዐ/ነገራት
እያስገባን በምሣሌ ማስረዳት
8. ቁጥር ከ1 እስከ
19 ያሉ የግእዝን ቁጥሮች
·
ቁጥር ትርጉምና ምድብ
·
ከ1 እስከ 10 ያሉ ቁጥሮች
·
ከ11 እስከ 19 ያሉ ቁጥሮች
·
ከዚህ በላይ የተጠቀሱትን መሠረታውያን ቁጥሮች በልምምድ
ማስረዳት
·
ከቁጥር ጋር የተያያዙ አርእስትን ለምሣሌ የሣምንቱ
ቀናትን፤ ከግእዝ እስከ ሳብእ ያሉ ሆሄያትን መዳሰስ
9. የልምምድ ውይይት
በተማሪዎች መካከል
·
ትምህርቱ ከተጀመረ ከ2 ወራት በሁዋላ ተማሪዎች
በውይይት ግሩፕ እርስ በርሳቸው ይወያያሉ፤ ጥያቄ ይጠያየቃሉ፤ መልስ ይሰጣጣሉ፤ መጨረሻ ላይ እኔ አየውና ማስተካከያ እሰጣለሁ።
የትምህርቱ
መተላለፊያ መንገዶች
ትምህርቱ በድምጽ፤በጽሁፍና በቪዲዮም ይሰጣል እስካሁን በአውደ ጥናት ይሰጡ የነበሩት የግእዝ ትምህርቶች በአውደ ጥናት ዘግእዝ
ቻናል ውስጥ ይገኛሉ። እነዚህ ቪዲዮዎች ለሁሉም ሰው ነጻ ናቸው። ከአሁን በኁዋላ የሚለቀቁ ቪዲዮዎችም ግሩፑ እንዳይጨናነቅ የሚለቀቁት
ወደአውደ ጥናት ዘግእዝ ነው። ነገር ግን እየከፈሉ የሚማሩ ተማሪዎች ብቻ ሊንክ እየተላከላቸው የሚገኙ እንጂ ለሁሉም የሚታዩ አይደሉም
(ፕራይቤት ይሆናሉ)፡
(አልፎ አልፎ ነጻ ትምህርቶችም ስለሚኖሩ) ስለዚህ ሁላችሁም እስካሁን የተለቀቁትን በነጻ ለመከታተል አዲስ የሚለቀቁትንም ለማየት በአውደ
ጥናት ዘግእዝ ሰብስክራይብ አድርጉ
ትምህርት የሚለቀቅባቸው ቀናትና የሚለቀቀው ትምህርት፡
ትምህርቱ የሚለቀቅባቸው ቀናት
(አርብና ለቅዳሜና ሰኞ ለማክሰኞ ነው ግን ሰዓቱ እንደየ አገራቱ ይለያያል)
አንድን ትምህርት
በሚገባ ለመማርና እውቀቱን ይዞ ለመውጣት ጊዜ ወሳኝ ነው ማለትም ትምህርቱን ደጋግመን ለማጥናት ጊዜ ማግኘት ግድ ነው። ስለዚህ
አንዱ ትምህርት በሌላው ላይ መደራረብ ሳይኖር አንዱን አሸንፈን ወደ ቀጣዩ መራመድ አለብን በመሆኑም በሳምንት 2 ጊዜ ትምህርት
ይለቀቃል አንዱ ትምህርቱ ነው፣ ሁለተኛው የጥያቄዎች ማብራርያና መልስ ነው። ስለዚህ
·
አንዱ ትምህርቱ ተዘጋጅቶ በድምጽ ይለቀቃል (ተማሪዎች ግን ባላቸው ጊዜያት ሁሉ እየመላለሱ
መስማትና ማጥናት አለባቸው)
·
ሁለተኛ የሚለቀቀው ለሚቀርቡ ጥያቄዎች ማብራርያና
መልስ ነው
·
በግል ማብራርያ የሚፈልግና የበለጠ ርዳታ የሚፈልግ
ማነኛውም ተማሪ በውስጥ መስመር ሊያነጋግረኝ ይችላል፤ ከቻልሁ ወዲያውኑ እመልሳለሁ ካልቻልኩ ግን መልእክታችሁን ወይም ጥያቂያችሁን
ብታስቀምጡ
መልሱን ይዠ አነጋግራችሁዋለሁ። ማንም ተማሪ ትምህርቱ ከብዶት፤አልገባው ብሎ የሚቀር አይኖርም።
ክፍያና የክፍያ ሁኔታ
ክፍያው ከዚህ በፊትም
ደጋግሜ ገልጨዋለሁ።
·
በኢትዮጵያ ለሚኖሩ 2000(ሁለት ሺህ) በዓመት
·
በአረብ አገራት ለሚኖሩ 3000(ሦስት ሺህ ብር ወይም 125 ዶላር) ባመት
·
በአሜሪካና በሌሎች የአውሮፓና እስያ አገሮች 200(ሁለት መቶ ዶላር) ባመት
አከፋፈል
·
በባንክ የቁጠባ ሂሣብ ቀጥታ የሚያስገቡ ሰዎች ወደ ባንክ ያስገቡበትን ደረሰኝ በስልካቸው ፎቶ
አንስተው ለእኔ (በዋትስ
አፕ ይልኩልኛል)ደረሰኙ ሲደርሰኝ መክፈላቸውን እመዘገባለሁ ለነሱም ደረሰኙን መቀበሌን መልሸ እጽፍላቸዋለሁ
·
በዌስተርን ዩኒየን(በኃዋላ) መላክ የሚፈልጉ ቀጥታ በስሜ ስለሚልኩት ከደረሰኝ በሁዋላ ከፍለዋል
ብየ እመዘግባለሁ ለነሱም ገንዘቡን መቀበሌ ወደ ስልካቸው መልእክት እልክላቸዋለሁ።
·
በአካል የሚከፍሉም ከተቀበልኩ በሁዋላ እንዳይረሻ ወደ ስልካቸው ለመክፈላቸው ማረጋገጫ መልእክት
እልክላቸዋለሁ።
የግሩፑ ሕግ
አንድ አስተማሪ
የሚያውቀውን ሁሉ ለተማሪዎች የሚያስተምር ወይም የሚናገር ከሆነ አስተማሪ አይባልም አስተማሪ ማለት መጥኖ፤ ለክቶ፤ በሚያስተምራቸው
ተማሪዎች ደረጃና መጠን እያዘጋጀ ነው ማስተማር ያለበት፤ የሚያውቀውን ሁሉ ከተናገረ፤ ለአንደኛ ክፍል ተማሪዎች የስድስተኛ ክፍል
ትምህርትን ቀላቅሎ የሚናገር ከሆነ ተማሪዎችን ግራ በማጋባት መስመር ያስታቸዋል እንጂ አይጠቅማቸውም።
ስለዚህ በተማሪዎች
መጠን የተዘጋጀውን ትምህርት ብቻ ለማስተማር በአስተማሪው ብቻ የተዘጋጁና የሚዘጋጁ ትምህርቶች ብቻ በአስተማሪው በኩል ይለቀቃሉ:
·
በግሩፑ ውስጥ ከአስተማሪ በስተቀር ማንም ሰው፤ ምንም ነገር፤ መንፈሳዊም፤ ሥጋዊም፤ ስለ ግእዝ
ትምህርትም ቢሆን ወደ ግሩፑ መልቀቅ አይችልም።
በተረፈግን የግእዝን
ትምህርት በሚገባ ማንበብ መጻፍና መናገርም እንድትችሉ የተቻለኝን ሁሉ አደርጋለሁ
ልዑል አምላክ ማስተዋሉን
ያድለን
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
መ/ር መላኩ ነኝ
ከአውደ ጥናት ዘግእዝ ነው
Monday, March 12, 2018
Thursday, August 17, 2017
የእመቤታችን ስሞች
የእመቤታችን ስሞችና የአማርኛ ትርጉማቸው
ሰላም ጤና ይስጥልኝ ከአውደ ጥናት
“ሰላም ለክሙ አርድእተ ልሣነ ግእዝ ኵልክሙ ዮም
እተረጉም ለክሙ ስማ አው አስማቲሃ ለእግዝእትነ ቅድስት ድንግል በክልኤ ማርያም”
በዛሬው ዝግጅታችን ስለ እመቤታችን ቅድስት ድንግል
ማርያም ስሞች በከፊል እንማራለን ። እንደሚታወቀው የተለያዩ የግእዝ ቃላትን ለማጥናት አልፎ አልፎ በማኅበራዊና በመንፈሳዊ ሕይወት
ዙሪያ አርእስትን እየመረጥን እንደ ምንማር ተነጋግረናል፡ ባለፈው በማኅበራዊ ዙሪያ ስለ ተውኔትና ተዋንያን ተመልክተን ነበር ዛሬ
ደግሞ በመንፈሳዊው ዙሪያ እንመለከታለን ማለት ነው። ስለ እመቤታችን ስሞች ዛሬ እንድንማር የመረጥኩበት ምክንያት።
1ኛ የእመቤታችን ስሞች ከግእዝ ቃላት በብዛት
በሁለት ቃላት የተቀነባበሩና ተናባቢ ቃላትን ፤ የምን እና የማን የሚሉትን ባለቤትነትን የሚያመለክቱ ሆሄያትን የምናውቅባቸው ናቸው ስለዚህ ቃላትን ልንማርባቸው ስለምንችል ነው
2ኛው በአሁኑ ወቅት የእመቤታችን የቅድስት ድንግል
ማርያም መታሰቢያ ጾም የሆነው ጾመ ፍልሰታ ስለሆነ በረከትን የምናገኝበት በመሆኑ የእመቤታንን ስሞች መረጥኩ ማለት ነው።
እመቤታችን የምትጠራባቸው ስሞች በጣም ብዙዎች
ስለሆኑ ሁሉንም ማጠቃለል ስለማይቻል የተወሰኑትን ማለትም ተዘውትረው የሚጠሩትን ብቻ ባጭሩ እንመለከታለን። ለወደፊቱ እመቤታችን
ቅድስት ድንግል ማርያምን በተመለከተ ሰፊና ተከታታይ ትምህርት ይኖረናል።
ስም የሚለው ቃል በግእዝም በአማርኛም አንድ ነው።
ሲበዛ ግን አማርኛው፤ “ስሞች” ግእዙ ደግሞ “አስማት” ይሆናል። ስም የአንድ ነገር፤ አካል፤ ሁኔታ፤ ወዘተርፈ መጠሪያ ማለት ነው።
አብዛኛውን ጊዜ በተለይ በመጽሐፍ ቅዱስ በአገራችን
ጭምር ስም እንዲሁ ለመጠሪያ ብቻ አይሰየምም፤ ነገር ግን ስም ሥራን፤ ባሕርይን፤ ዓይነትን፤ ሁኔታን፤ ክስተትን መሰረት በማድረግ
ይሰየማል። በመሆኑም የእመቤታችንም ስሞች ማንነቷን፤ ሥራዋን፤ ምርጫዋን፤ ወዘተ መሠረት ያደረጉና የሚገልጡ ገላጮች ናቸው።
ስም ብቻውን ብዙ ነገገርን ይሠራል። ባለ ስሙ
እንኳን በአካል ሳይኖር ብቻውን ብዙ ጥቅምን ይሰጣል። ለምሣሌ
“በእንተ ስማ ለማርያም” ወይም (ስለ እመ ብርሃን”) ማለት “ስለ ማርያም ስም” ስለ ብርሃን እናት ስም ማለት ነው። “ስለ ማርያም ስም” ማለት ነው
እንጂ ስሟ እንኳን በግልጽ አልተጠቀሰም። ነገር ግን በዚህ ዐ/ነገር
ብቻ አስደናቂ ሥራ ይሠራል። ምክንያቱም የእመቤታችን ስም ተወዳጅ
፤ የሚፈራ፤ የሚከበር፤የሚናፈቅም ስም ስለ ሆነ ነው።
በዚህ ቃል ብቻ ሕይወታቸውን እየመሩ ነው የቤተ
ክርስቲያናችን ሊቃውንት ካህናት፤ የሀገርና የሕዝብ መመኪያዎች መምህራን፤
የአገራችንን ታሪክ ከምንጩ በብራና በእንስሳት ቆዳ በእጃቸው እየጻፉ ጥራቱን እንደ ጠበቀ ለትውልድ እንዲቆይ ያደረጉት።
የዜማ፤የቅኔ፤የመጻሕፍት
ትርጓሜ ሊቃውንት የሚማሩት በዚህ ስም ብቻ ነው። ይህንን ዐ/ነገር በመናገር ብቻ ነው። አስደናቂውንና ለወገን መመኪያ ከአምላክ
ጋር መነናገሪያ መንፈሳዊ ቋንቋ የሆነውን መንፈሳዊ ትምህርት የተማሩት የእመቤታንን ስም በመጥራት ብቻ ነው። በተለይ በኢትዮጵያውያን
መካከል የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ስም ልዩ ኃይል አለው። ማንም የእሷን ስም ጠርቶ ባዶ እጁን አይመለስም ። በገጠሩ
ኅብረተ ሰብ ተማሪ “በእንተ ስማ ለማርያም” ካለ እንጀራ እንኳን ባይኖራቸው ለዘር ተብሎ ተደብቆ ከተቀመጠው እህል ቀንሰው ይሰጣሉ
እንንጅ የለንም አይሉ። እና የእመቤታችን ስም ለተራቡት ምግብን፤ ለታረዙት ልብስን፤ ለተቸገሩት መጽናናትን ይሰጣል።
ከብዙ ዎቹ መካከል ከእመቤታችን ስሞች መካከል
የሚከተሉት ጥቂቶቹ ናቸው እና እነዚህን በ2ቱ የጾመ ፍልሰታ ቀናት ምሣሌ 14ቱን ብቻ እንመለከታለን።
1.
ማርያም (ማር+ያም=) (ማ=ማኅደረ
መለኮት፤ ር= ርግብ፤ ያ=ያንቅአዱ ኀቤኪ፤ ም= ምስአል ወምስጋድ፤)
2.
ድንግል (ቅጽል) (አምላክን
ከመውለዷ በፊት፤ በወለደች ጊዜ፤ ከወለደችውም በኋላ) በሐሣቧ፤በሥራዋም ድንግል ናት
3.
ቅድስተ ቅዱሳን(ቀደሰ)(ቅጽል)
4.
እመ ብርሃን
5.
እመ አምላክ
6.
እመ ክርስቶስ
7.
ርኅርኅተ(ቅጽል) ልብ
8.
ሰአሊተ(ቅጽል) ምሕረት(ሰአለ)
9.
ጽንሰታ(ስም) ለማርያም (ጸንሰ)
10.
ልደታ(ስም) ለማርያም(ወለደ)
11.
በዓታ (ስም) ለማርያም(ቦአ)
12.
አስተርእዮታ(ንዑስ አንቀጽ)
ለማርያም(አስተርአየ)
13.
ፍልሰታ ለማርያም (ፍልሰተ
ሥጋሃ ለማርያም
14.
ትንሣኤሃ(ስም/ጥሬ ዘር) ለማርያም(ተንሥአ) ዕርገታ (ስም/ሳቢ ዘር) ለማርያም(አርገ)
ልዑል አምላክ ማስተዋሉን ያድለን
ከአውደ ጥናት ዘግእዝ
በመ/ር መላኩ አስማማው ቢሰጠኝ
Sunday, August 13, 2017
መልስ ለትርጉም ጥያቄዎች
መልስ
የትርጉም ጥያቄ አንድ
|
ወደ አማርጛ ይቀይሩ
|
"ወሀሎ አሐዱ ብእሲ ዘስሙ መላኩ አስማማው ዘይነብር
በብሔረ አሜሪካ ወውእቱ ይሜህር ልሳነ ግእዝ በውስተ አውደ ጥናት "
|
ትርጉም1፡ =
|
በአሜሪካን አገር የሚኖር ስሙ መላኩ አስማማው የሚባል አንድ ሰው አለ፤
እሱም በአውደ ጥናት የግእዝ ቋንቋን ያስተምራል።
|
ወይም ትርጉም 2፡=
|
አንድ በአሜሪካን አገር የሚኖር ስሙ መላኩ አስማማው የሚባል
አንድ ሰው አለ፤ እሱም የግእዝ ቋንቋን በአውደ ጥናት ውስጥ ያስተምራል (እያስተማረ ነው)።
|
የትርጉም ጥያቄ ሁለት
ወደ አማርኛ ይቀይሩ
“ዛቲ ጦማረ መልእክት ትብጻህ ኀበ አርድእተ
ልሣነ ግእዝ ዘመጽሐፈ ገጽ
እምነ መምህረ ልሣነ ግእዝ”
ትርጉም አንድ፡=
ይህች የመልእክት ደብዳቤ በፌስ ቡክ
የግእዝ ቋንቋ ተማሪዎች ወደ ሆኑት ትድረስ።
ከግእዝ ቋንቋ አስተማሪ(መምህር)
ወይም ትርጉም ሁለት፡=
ይች የሰላምታ ደብዳቤ ከግእዝ ቋንቋ አስተማሪ(መምህር) በፌስ ቡክ የግእዝ ቋንቋን ወደ ሚማሩ ተማሪዎች ትድረስ።
የግእዝን ሥነ ጽሁፍ በተለያየ ዓይነት
መልኩ በተለይ የቃላትን ቅደም ተከተል በመቀያየር ሊተረጎም ይችላል፤ ነገር ግን አንዳንድ መታለፍ የሌለባቸው ሕጎች አሉ።
ለምሣሌ
“ይሜህር ልሣነ ግእዝ ቢል”
1.
የግእዝን ቋንቋ ያስተምራል
2.
የግእዝ ቋንቋን
ያስተምራል
3.
ግእዝን ያስተምራል
እነዚህ ሦስቱም ለሰሚ በትክክል ሊረዱ
ይችላሉ ማለትም ተናጋሪው ምን ማለት እንደ ፈለገ ማወቅ ይቻላል። በሰዋስው ህግ ግን ትክክለኛው አፈታት ወይም ትርጉም ሁለተኛው(2ኛው ) ነው። ምክንያቱም “ን”
የሚለውን ተሳቢ ወይም (Direct Object) ለማምጣት የቃሉ የመጨረሻ ሆሄ
“ግእዝ” “ራብዕ” “ሐምስ” ወይም “ሣብዕ” መሆን አለበት ስለዚህ “የግእዝን ቋንቋ” ማለት አይቻልም ለምን “ግእዝ” የሚጨርሰው በ”ሳድስ” ልሣነ ግእዝ ሲል
“ልሣነ” የሚለው በ”ግእዝ” ስለሚጨርስ ተሳቢ መሆን ይችላል።
ይህ አገላለጽ ለአሁኑ ሊከብዳችሁ ስለሚችል።
ሌላ ጊዜ ስለ “ገቢርና ተገብሮ” ስንማር ቪዲዮ ስላለ በደንብ ይገባችኋል። አሁን ግን አትጨነቁ።
የተወሰናችሁት ሠርታችሁታል፤ በተለይ
ትርጉሙን ምን ለማለት እንደተፈለገ በደንብ ሁላችሁም ታውቁታላችሁ። የሰጣችሁትም ትርጉም ለሁሉም ሰው ያለምንም ችግር ሊገባ ወይም
ሊረዳ የሚችል ነው። ብቻ የቃላትን አገባብ ወይም ግራመር የሚያውቁ ሰዎች ብቻ ናቸው የሰዋስው ስህተት መኖሩን ሊያውቁ የሚችሉት።
እና በጣም ጥሩ እየተራመዳችሁ ነው በርቱ።
የቤት ሥራ!!
አሁን የሚከተለውን ሥነ ጽሁፍ ማለትም የተረጎማችሁትን ወደ የራሳችሁ ወይም በራሳችሁ ስም ጻፉ(ቀይሩት) በሚከተለው ዓይነት ቃላቱ እንደየ ጾታችሁና የምትኖሩበት አገር ትቀይራላችሁ።
"ወሀሎ አሐዱ ብእሲ
ዘስሙ መላኩ አስማማው ዘይነብር
በብሔረ አሜሪካ ወውእቱ ይሜህር ልሳነ ግእዝ በውስተ አውደ ጥናት ።"
----- ----- ----- ----- የራሳችሁን
ስም ---- የምትኖሩበት አገር -----
----- ልሣነ ግእዝ --- የምትኖሩበት
አገር
ምን አልባት ቃላቱ እንዳይከብዳችሁ የሚከተሉትን
ቃላት ተጠቀሙ።
ሀለወት =ለሴት አለች ወይም ነበረች
አሐቲ= ለሴት አንዲት
ብእሲት= ሴት
ዘስማ= ለሴት ስሟ
ዘትነብር= ለሴት የምትኖር
ወይእቲ= ለሴት እሷም
ትሜህር= ለሴት ታስተምራለች
ካልገባችሁ ከመሥራታችሁ በፊት ጠይቁ
መልካም ሥራ
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
እምነ አውደ ጥናት ዘግእዝ
Subscribe to:
Posts (Atom)



